ስድስት ሰዎችን በማካተት እ.ኤ.አ በ2016/17 የተጀመረውና በቁጠባና ኢንቨስትመንት ላይ ያተኮረ ሀገር አቀፍ ጥናት በቅርቡ ተጠነቋል።ጥናቱ እ.ኤ.አ በ2010/11 አጠቃላይ ሀገራዊ ምርትን እንደመለኪያ በመውሰድ የአገሪቱ የቁጠባ መጠን 9 ነጥብ 5 ከመቶ መድረሱን አመላክቷል።እ.ኤ.አ በ2014/15 ደግሞ የቁጠባ መጠኑ 22 ነጥብ 5 ከመቶ መድረሱን ጠቁሟል። በነዚህ ዓመታት ውስጥ የቁጠባ እድገት 136 ከመቶ ጭማሪ ማሳየቱንም አመልክቷል።
በጥናቱ መነሻነት ቁጠባ በመጠን ሲታይ እ.ኤ.አ በ2013/14 በቁጠባ 205 ቢሊዮን ብር ያህል ተቆጥቧል፤እ.ኤ.አ በ2018 ደግሞ 638 ቢሊዮን ብር ተቆጥቧል። ይህም የቁጠባ መጠኑ በሶስት እጥፍ ማደጉን ያሳያል።
የቁጠባ አንዱ አላማ ለኢንቨስትመንት የሚሆን ሀብት ማሰባሰብ መሆኑ ይታወቃል።የቁጠባው እድገት ግን ኢንቨስትመንቱ ከሚፈልገው አንጻር ሲታይ ብዙ የሚቀረው እንዳለ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ጥናቱም ይህንኑ አመልክቷል።በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ወቅት እ.ኤ.አ በ2013/14 የቁጠባ መጠን 22 ነጥብ 5 ከመቶ ቢደርስም ፣የኢንቨስትመንት ፍላጎቱ ግን ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት 40 ነጥብ 3 በመቶ ሆኖ ነው የተገኘው። ይህም በአገራዊ የቁጠባ መጠንና በኢንቨስትመንት መካከል 18 በመቶ ያህል ክፍተት መኖሩን ይጠቁማል።
ጥናቱ በዋናነት ይህንን ክፍተት ለማጥበብና ቁጠባን የበለጠ ለማንቀሳቀስ ምን አይነት መንገዶችን መከተል እንደሚገባም አመልክቷል።አዲስ ዘመን ጋዜጣም የማክሮ ኢኮኖሚ ዘርፍ ተመራማሪ ከሆኑት አቶ መሃመድ በሽር ጋር የቁጠባ አማራጮችን በማሳደግ ከኢንቨስትመንት ጋር ያለውን ክፍተት ማጥበብ በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ያደረገውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
የቁጠባ ባህል ያለበት ደረጃ
ሰዎች በቀጣይ ሊመጣ የሚችለውን አደጋ በመፍራትና አደጋውን ለመቀነስ በማሰብ፣ ነገን የተሻለ ለማድረግና አዲስ ሥራ ለመፍጠር ሲሉ ቁጠባን ሊጀምሩ ይችላሉ።በኢትዮጵያ ገንዘብ በሚቆጥቡና በማይቆጥቡ ሰዎች መካከል ያለው የቁጥር ልዩነት እጅግ ጠባብ ነው ማለት ይቻላል።ከዚህ ጋር በተያያዘ የተካሄዱ ጥናቶችም በሀገሪቱ 56 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች ገንዘባቸው የሚቆጥቡ ሲሆኑ፤ 44 በመቶ ያህሉ ደግሞ የማይቆጥቡ መሆናቸውን ያመለክታሉ።ይህም ቁጠባ በተለያየ መንገድ የሚስፋፋበትና የሚንቀሳቀስበት መንገድ ቢጠናከር የቁጠባ ባህልን ከማሳደግ አኳያ ትልቅ አቅም እንዳለ ይጠቁማል።
ሰዎች ገንዘብ የማይቆጥቡት ለምንድን ነው?
ሰዎች በአብዛኛው የሚቆጥቡት የገንዘባቸውን ደህንነት ለመጠበቅ ሲሉ እንጂ ወለድ አገኛለሁ በሚል ምክንያት አይደለም።የገንዘብ ተቋማትን የማግኘት እድል ቢኖራቸውም የሚቆጥቡት በቂ ገንዘብ ስለማያገኙም ገንዘባቸውን በባንክ አያስቀምጡም። በቁጠባ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ከሚያሳድሩ ዋነኛ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ የሰዎች የገቢ መጠን አንዱ ሲሆን፣ግለሰቦች ወጪያቸው ከሚያገኙት ገቢ ጋር ተመጣጣኝ ሳይሆን ሲቀር ለቁጠባ የሚተርፍ ገንዘብ ሊኖራቸው አይችልም።
የቁጠባን ጠቀሜታ በሚገባ አለመረዳትም ሰዎች ገንዘብ እንዳይቆጥቡ የራሱን ሚና ይጫወታል። ይህም በዋናነት በገጠር አካባቢ ያለውን ሁኔታ ያንፀባርቃል። በቁጠባ ዘዴዎች ፍላጎት ማጣት በተለይም የፋይናንስ ተቋማት ሁሉን አቀፍ የቁጠባ ዘዴዎችን ለተጠቃሚዎች ይዞ አለመቅረብም ቁጠባ እንዳያድግ እንቅፋት ሆኗል።
በተመሳሳይም ባንኮችም የተለያዩ የቁጠባ አማራጮችን ለደምበኞቻቸው ይዘው ቢቀርቡም በትክክል ህብረተሰቡ የሚፈልጋቸውን የቁጠባ ዘዴዎችና መንገዶችን ይዘው መምጣት አልቻሉም። ከቁጠባ የሚገኘው ውጤት ዝቅተኛ መሆንም ሰዎች ገንዘባቸውን እንዳይቆጥቡ ተጨማሪ ምክንያት ነው።
ቁጠባን እንዴት ማሳደግና ከኢንቨስትመንት ጋር ያለውን ልዩነት ማጥበብ ይቻላል?
ቁጠባን ለማሳደግና በቁጠባና ኢንቨስትመንት መካከል ያለውን ክፍተት ለመሙላት በመንግሥት በኩል የማክሮ ኢኮኖሚውን ማረጋጋት ወይም የዋጋ ንረቱን መቀነስ ያስፈልጋል።ቁጠባን የሚወስነው በዋናነት የሰዎች ገቢ እንደመሆኑ ለሥራ አጦች የሥራ እድል በመፍጠር ገቢያቸውን ማሳደግ ይገባል።
የገንዘብ ዋጋ ከቁጠባ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው በመሆኑ በተዘዋዋሪ የሚገኘውን ገንዘብ የመግዛት አቅም መከላከል ያስፈልጋል።በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥት መሰረታዊ የፋይናንስ እውቀትን ለህብረተሰቡ ማስተላለፍ ይኖርበታል።ይህም ሰዎች የፋይናንስ እውቀት ኖሯቸው በፈለጉት የቁጠባ ዘዴ በመሳተፍ ተጠቃሚ ለመሆን ያስችላቸዋል።
የተለያዩ የቁጠባ ፕሮግራሞችን ማስተዋወቅም ቁጠባን በማሳደግ ረገድ ቁልፍ ሚና ይጫወታል። ለአብነትም ቀደም ሲል በመንግሥት ደረጃ የተጀመሩ የቤቶች ቁጠባ፣ የህዳሴ ግድብ ቦንድ ግዢና መሰል ፕሮግራሞች የሰዎችን የቁጠባ ባህል አሳድገዋል።በቀጣይም እነዚህንና መሰል የቁጠባ ፕሮግራሞችን ማስተዋወቅ ቢቻል ቁጠባን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ይቻላል።
ባንኮችም የቁጠባ ዘዴዎቻቸውንና አማራ ጫቸውን መጨመር ይጠበቅባቸዋል። በተለይም በቅርቡ መንግሥት የጀመራቸው ኢስላማዊ ባንኮች የባንኮችን ሁሉን አቀፍ የቁጠባ አማራጮችን የሚያሳድጉ ናቸው። በተጨማሪም ባንኮች አዋጭነት ላይ ተመስርተው መስፋፋት ይኖርባቸዋል። ይህም ቁጠባን በተሻለ ሁኔታ ለማሳደግ ያስችላል።
ግለሰቦች ከወጪያቸው የሚተርፈውን ገንዘብ በባንክ እንዲያስቀምጡ ባንኮች ወጪና ገቢን ለማመጣጠን የሚረዱ ወረቀቶችን ለደምበ ኞቻቸው ቢሰጡ ቁጠባን ለማሳደግ አንዱ መንገድ ይሆናል።ለጡረታ የሚሰበሰበውን ገንዘብ በኢንቨስትመንት ላይ ማዋልና ተጨማሪ ትርፍ ማግኘት የሚቻል ከሆነም የቁጠባን አቅም የበለጠ ማሳደግ ይቻላል።
አዲስ ዘመን ህዳር 16 ቀን 2012 ዓ.ም
አስናቀ ፀጋዬ