በትምህርት ቤት ከሚሰጡ የትምህርት ዘርፎች ውስጥ አንደኛውና ዋናው በክፍል ውስጥ የሚሰጠው መደበኛ ትምህርት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከክፍል ውጪ በክበባት በመደራጀት በተጓዳኝ የሚሰጠው ትምህርት ነው።
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በአገራችን ትምህርት ቤቶች ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ለመረዳት በአዲስ አበባ በተወሰኑ ትምህርት ቤቶች ተዘዋውረን ከሚመለከታቸውም አካላት ጋር ቆይታ አድርገናል።
በዳግማዊ ምኒልክ አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአደረጃጀትና ትምህርት ፕሮግራሞች ክትትል ምክትል ርእሰ መምህርት ወይዘሮ ቅርስነሽ የማነ እንደነገሩን በትምህርት ቤቱ ውስጥ የተጓዳኝ ትምህርት እንቅስቃሴና የተማሪዎች ተሳትፎ በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል።
«በተለያዩ ዘርፎች የተጓዳኝ ትምህርት ተግባራት ይከናወናሉ። በአጠቃላይ ዘጠኝ ክበባት በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል በጤና፣ በኪነጥበብና በበጎ አድራጎት ክበባት ከፍተኛ የመምህራንና ተማሪዎች ተሳትፎ እንዳለ ይናገራሉ።
በመመሪያው መሠረት እያንዳንዱ ትምህርት ቤት አስራ ሁለት ክበባት ሊኖሩት ይገባል የሚሉት ምክትል ርእሰ መምህሯ ሆኖም ሦስቱ ማለትም የትራፊክ ደህንነትና ማኔጅመንት፣ የትራንስፖርትና የሰብአዊ መብት ክበቦች ለተማሪዎች ሥልጠና ባለመስጠታቸው እስካሁን ተግባራዊ አለመሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ወይዘሮ ቅርስነሽ እንደሚናገሩት ከሆነ በትምህርት ቤቱ እየተከናወኑ የሚገኙ የተጓዳኝ ትምህርት እንቅስቃሴዎች የተማሪዎችን የተደበቁ እውነተኛ ፍላጎቶችና ችሎታዎች የሚገለጡበት ሲሆን ሲሳተፉ የነበሩ ተማሪዎችም ለፍሬ በቅተዋል። ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት በተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች ላይ የሚሳተፉ፣ የሙዚቃ አልበም ያወጡና ሌሎችም አሉ። አሁን ያሉትም በሙሉ ፈቃደኝነትና በከፍተኛ ስሜት ነው የሚሳተፉት። በተለያየ የሙያ ዘርፍ ስኬታማ ለመሆን አቅደውና አልመው እየተሳተፉ ያሉ ተማሪዎች በርካቶች ናቸው።
የልዩ ፍላጎት መምህርትና የሥርዓተፆታ ክበብ አስተባባሪ ወይዘሮ አምሳለ ገብረማርያምም ተመሳሳይ ሃሳብ አላቸው። መምህርቷ እንደሚሉት የተጓዳኝ ትምህርት ያለው ሚና ቀላል አይደለም፤ የቀለም ትምህርቱ አጋዥ ነው። የተማሪዎችን ሥነ-ምግባርን ከማነፅም፣ ግንዛቤን ከማስጨበጥም ሆነ ችሎታቸውን ከማጎልበት አኳያ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። በመሆኑም በትምህርት ቤቶች የሚካሄደው የተጓዳኝ ትምህርት ፕሮግራም በሚገባ ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል።
ሌላው ያነጋገርነው የ8ኛ ክፍል ተማሪና በኪነጥበብ ክበብ በስእል ዘርፍ እየተሳተፈ የሚገኘውን ተማሪ አዶናይ ፍሰሐን ሲሆን በክበቡ ውስጥ በሙሉ ፍቃደኝነት፣ በከፍተኛ ፍላጎትና ፍቅር እንደሚንቀሳቀስ ነግሮናል።
ተማሪ አዶናይ እንደሚናገረው ከሆነ የስእል ፍቅር ከልጅነቱ ጀምሮ በውስጡ የነበረ ሲሆን ይህንን ፍላጎቱንም ወደ ተግባር ለመቀየር ያገኘው ቦታ ቢኖር ይህ የኪነጥበብ ክበብ ነው። በመሆኑም በክበቡ በመሳተፍ በትምህርት ቤቱ ውስጥ የተቀመጡ በርካታ ስእሎች አሉት።
«እቤቴ መጥታችሁ ብታዩልኝ ደስ ይለኛል» የሚለውና ችሎታው የአባይ ግድብን እስከመሳል ድረስ መሄዱ በአስተባባሪዎቹ የሚነገርለት ተማሪ አዶናይ በሥራው አስተባባሪዎችና የት/ቤቱ እገዛ እንዳልተለየውም ይናገራል። ሁሉም ተማሪ በተጓዳኝ ክበባት እንደየፍላጎቱ በመግባት ሊሳተፍ እንደሚገባም ይመክራል።
አጠቃላይ የመስተዳድሩ ትምህርት ቢሮን አሠራር፣ ክትትልና ግምገማን በተመለከተም በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የሥርዓተ-ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ የሥራ ሂደት ተገኝተን አነጋግረናል።
የሥራ ሂደቱ ተወካይ አቶ አስራት ሽፈራው ጉዳዩን በተመለከተ እንደነገሩን በአሁኑ ሰዓት በትምህርት ቢሮ ደረጃ የክበባት ማንዋል ተዘጋጅቶና ለሁሉም ትምህርት ቤቶች ታድሎ በእሱ መሠረት እየተሰራ ይገኛል። በአጠቃላይም አስራ ሁለት የተጓዳኝ ትምህርት ክበባት ያሉ ሲሆን ተማሪዎችም በእነዚሁ ክበባት እየተሳተፉ ይገኛሉ።
በአሁኑ ሰዓት በርካታ የ«ክበብ ይቋቋምልን» ጥያቄዎች ከየመስሪያ ቤቶች ይመጣሉ የሚሉት አቶ አስራት እነዚህን ሁሉ ለማስተናገድ አስቸጋሪ ቢሆንም በተቻለን አቅም ካሉት ክበባት ወደሚቀርባቸው በመመደብ መስተንግዶ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ይናገራሉ።
አቶ አስራት ሽፈራው እንደሚሉት ክበባት የትምህርቱ አጋዥ ከመሆናቸውም በላይ የተማሪዎችን ተሰጥኦ ለማውጣት ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው።
አቶ አስራትን ሁሉም ክበባት በትምህርት ቤቶች ተቋቁመው ተማሪዎች እየሳተፉ ናቸው ወይ በሚል ላነሳንላቸው ጥያቄም «ይህን ያላደረጉ እንደሚኖሩ ይጠበቃል፤ ሆኖም ግን በቅርቡ ክትትል በማድረግ ያሉ ክፍተቶች ተለይተው የማስተካል ሥራው ይሰራል።» ሲሉ ሃሳባቸውን አጋርተውናል።
አዲስ ዘመን ህዳር 15/2012
ግርማ መንግስቴ