– 98 ነጥብ 51 በመቶ መራጭ ሲዳማን በክልልነት መርጧል
– ሂደቱ ሰላማዊና ተዓማኒ ነው
ሀዋሳ፡- በሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ድምጽ ከሰጠው መራጭ 98 ነጥብ 51 በመቶ የሲዳማን በክልልነት መደራጀት መምረጡን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ። የሕዝበ ውሳኔው ሂደት ሰላማዊና ተዓማኒ እንዲሁም ከፍተኛ የሕዝብ ተሳትፎ የታየበት መሆኑም ተጠቅሷል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ጊዜያዊ ውጤትን አስመልክቶ ትናንት በሀዋሳ ከተማ በሚገኘው ኃይሌ ሪዞርት መግለጫ በሰጠበት ወቅት እንደገለጸው፤ በሕዝበ ውሳኔው ድምጽ ለመስጠት ከተመዘገበው 2 ሚሊዮን 280 ሺህ 147 መራጭ 2 ሚሊዮን 277 ሺህ 63 ሰው ድምጹን ሰጥቷል። ድምጻቸውን ከሰጡት ውስጥ 2 ሚሊዮን 225 ሺህ 249 መራጭ የሲዳማ በክልልነት መደራጀትን የመረጠ ሲሆን 33 ሺህ 463 ድምጽ ሰጪ ደግሞ ሲዳማ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ውስጥ እንዲሆን መርጧል።
ይህም ማለት ሲዳማ በክልልነት መደራጀትን የመረጠው 98 ነጥብ 51 በመቶ ሲሆን፤ በነባሩ ክልል እንዲቀጥል የመረጠው 1 ነጥብ 48 በመቶ ነው። በሂደቱ 18ሺህ 351 ድምጽ ዋጋ አልባ መሆኑ በመግለጫው ተመላክቷል።
የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 47 /2/ እና /3/ ማንኛውም ብሔር ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ የራሱን ክልል የማቋቋም መብት አለው በማለት በሚደነግገው መሠረት የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ሕጋዊና ሰላማዊ ሆኖ ተፈጽሟል ያለው የቦርዱ መግለጫ፤ የዞኑ ነዋሪዎች በነፃ ፈቃዳቸው በሰጡት ውሳኔ መሠረት ሲዳማ ክልል ሆኖ መደራጀት የሚያስችለውን ድምጽ ማግኘቱን አብራርቷል።
እንደ ቦርዱ መግለጫ፤ የሕዝበ ውሳኔው ሂደት ሰላማዊና ተዓማኒ እንዲሁም ከፍተኛ የሕዝብ ተሳትፎ የታየበት ነው። ሕዝበ ውሳኔው ዜጎች መብታቸውን በሰላማዊ መንገድ ተግባራዊ ያደረጉበት እና በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አንድ እርምጃ ተብሎ የሚወሰድ ነው።
በውጤቱ መሠረትም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47/3/ መ ላይ እንደተጠቀሰው የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤትና በሲዳማ ዞን አስተዳደር የሕዝቡን ድምጽ ባከበረ፣ ሰላማዊ እና ግልጽ በሆነ መልኩ እንዲሁም ሽግግሩን ጊዜን በጠበቀ ሁኔታ በማከናወን የሥልጣን ርክክቡን በአግባቡ እንደሚያከናውኑ እምነት እንዳለው ቦርዱ አስታውቋል።
የሲዳማ በክልልነት የመደራጀት ሕዝበ ውሳኔ በኢትዮጵያ ከነበረው ልምድ የተለየና የመጀመሪያው ቢሆንም ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ ሁኔታ ሊፈጸም መቻሉን የገለጸው ቦርዱ፤ ሕዝበ ውሳኔው ስኬታማ እንዲሆን ድጋፍ ያደረጉ የተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦችን አመስግኗል።
የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ድምጽ የተሰጠው ኅዳር 10 ቀን 2012 እንደነበር ይታወሳል።
አዲስ ዘመን ህዳር 14/2012
መላኩ ኤሮሴ