ማህበረሰቡ ባህላዊ እሴቶቹን ተጠቅሞ አንድነቱን እንዲያጠናክር ለማድረግ ዕድል አልተሰጠም።ባህላዊ እሴቶች ቦታ አለመሰጠታቸውና አልፎ አልፎም በፖለቲከኞች እንዲተገበሩ መሆኑ ተአማኒነታቸውም ሆነ ተቀባይነታቸው ከውጤታማነት አርቋል ሲሉ ምሁራን ይገልጻሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው እንደሚናገሩት፤ የባህል እሴቶች ማንም ተነስቶ ውሳኔ የሚሰጥባቸውና የሚያዳብራቸው አይደሉም።ማህበረሰቡ በራሱ ውስጥ አንጾ የሚያጎለብታቸው ናቸው።በሕግ፤ በፖሊሲ፤ በፖለቲካ ፓርቲ የሚዳብሩ ሳይሆኑ ኅብረተሰቡ ራሱ ፈጥሮ ራሱ የሚማርባቸውና በተግባር የሚያውላቸው ናቸው።ነገር ግን አሁን ከማህበረሰቡ ወጥተው ፖለቲከኛው እንደፈለገው የሚመራቸው ሆነው ተአማኒነታቸው ቀንሶታል።
በባህላዊ እሴት የተገነባ አንድነት እንዳይፈጠር የሆነው ፖለቲካው ጣልቃ ገብቶ ሰው በገነባው እሴት ሳይሆን በብሔርና ቋንቋው እንዲያስብ አድርጎታል የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ ባህላዊ እሴቶች አንድነትን ማጠናከር ሳይሆን ማንነት ብቻ አቀንቃኝ፤ የራሴ ነው የሚለውን ብቻ ይዞ ተጓዥ ሆኗል።የሌላን መንከባከብና ማክበርም ትቷል።በተለይ በራሱ ማንነት ውስጥ ያሉ እሴቶችን እንኳን አለማክበሩ ችግሩ የት እንደደረሰ የሚያሳይ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
ከማህበረሰቡ እኩል የሚያሳትፈውን ትቶ “እኔኮ እንደዚህ ነኝ” እያለ የመምጣቱ ምስጢር ፖለቲካው ባህላዊ እሴቶችን ተክቶ ለራስ ብቻ መኖርን እያሰረጸ መሆኑን ያመለክታል።ይህም አንድነት የሚባል ነገር እንዳይታሰብ አድርጎታል ይላሉ።ባህልና እሴትን የሚገነቡ የማህበረሰብ ክፍሎች በፖለቲካው ሹማምንት ተተክቷል።መድረኮችም ላይ ተዋናዩ ፖለቲከኛውና ካድሬው ነው።ስለዚህ በምን መልኩ ውጤታማ ሊሆኑ ይችላሉ ሲሉ ይጠይቃሉ።
እንደ ረዳት ፕሮፌሰር አበባው ገለጻ፤ የባህል እሴት ገንቢ አባቶች ቦታቸውን መነጠቃቸው የአባቶችን ምክር ሰምቶ ወደ ተግባር የሚገባ ወጣት እንዳይኖር በር ዘግቷል።ስለዚህ ባህላዊ እሴቶች አንድነትን በማጠናከር ውጤት እንዳያሳዩ ሆኗል።
በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የቋንቋና ሥነጽሑፍ መምህሯ ወይዘሮ ሕይወት አበሩ በበኩላቸው፤ ባህላዊ እሴቶች በአግባቡ ለሚፈለገው አላማ አለመዋላቸው ችግሩ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል። ኢትዮጵያ ውስጥ ከ80 በላይ የሚሆኑ ብሔረሰቦች አሉ።እነርሱም አንድነትን ሊያጠናክሩ የሚችሉ ባህላዊ እሴቶች አሏቸው።ሆኖም ግን ይህንን በአግባቡ እንዲጠቀሙበት፣ እንዲያድጉ አልተደረገም።
የመንግሥት መዋቅር ከመምጣቱ በፊት ማህበረሰቡ በባህላዊ እሴቶቹ ችግሮቹን ሲፈታ መቆየቱን መምህርት ሕይወት ያስታውሳሉ፤ ሕግና የባህላዊ እሴቶች ትግበራ የተቃረነ መሆኑም ፈተና እንደነበር ይገልጻሉ።
ለዚህም አብነት የሚያደርጉት በባህላዊ መንገድ እርቅ ተፈጽሞ ካበቃ በኋላ በሕግ መቀጣቱ አንድነትን ፈጥሮ እንዳይኖር እንቅፋት ሆኗል።ባህላዊ እሴቶች ባሉበት ደረጃ በተግባር ቢተረጎሙም መልሶ የሚያከስማቸው አሠራር ስላለ አንድነትን በማምጣት ዙሪያ ውጤታቸው ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ እንዳደረገው ይናገራሉ።
እንደ መምህርት ሕይወት ገለጻ፤ ባህላዊ እሴቶችን ያወቀ፤ በእነርሱም የሚኮራና በተግባር የሚያውል ትውልድ አለመፈጠሩም አንድነትን ከማጠናከር አንጻር ውጤታማ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል።አሁን ችግር የሚፈጥሩት አዛውንቶች ሳይሆኑ ወጣቶች ናቸው።ወጣቱ ላይ የአንድነት መንፈስ አለመፈጠሩና በባህላቸው እንዲኮሩ አለመደረጉ ለችግሩ እልባት ለመስጠት አዳጋች ሆኗል።
የሥርዓተ ትምህርቱ የአገሪቱን ባህላዊ እሴት ያላካተተ መሆኑም ሌላው ፈተና መሆኑን የሚያነሱት መምህርቷ፤ ወጣቱ በባህልና እሴቱ ታንፆ እንዳይሰራ ገድቦታል።
መፍትሄው በእያንዳንዱ ፖሊሲ፤ ሕግና መመሪያዎች እንዲሁም የትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ባህላዊ እሴቶችን የሚያበለጽጉና ለአንድነት መጠናከር የሚበጁ አድርጎ ማካተት እንደሚገባ የሚናገሩት መምህርት ሕይወት፤ ውጤቱ በአንድ ጊዜ ይመጣል ብሎ ማሰብ ከባድ ነው።ሆኖም ግን ትናንት የዘራነውን ዛሬ እያጨድን መሆኑን አምኖ ለነገው መስራት ያስፈልጋል።የባህል አስፈላጊነት የሚቀነቀንለት ሊሆን እንደሚገባ ያሳስባሉ።
ፖለቲካን የሁሉም መለኪያ ያለማድረግ ችግሩን ይፈተዋል የሚሉት ደግሞ ረዳት ፕሮፌሰር አበባው ሲሆኑ፤ ፖለቲካ የሚያልቅበትን የራሱን አውድ ማየትና በዚያ እንዲያበቃ መወሰን ያስፈልጋል።ፖለቲካውን ለፖለቲከኛው ብቻ መተውም ተገቢ ነው።በባህል መንገድ የሚሰራውን ማጠልሸት ማቆም እንደሚያስፈልግም ይናገራሉ።
«ኅብረተሰቡ ያለማንም ጣልቃገብነት በነፃነት ያሉትን እሴቶች እንዲያወጣ መፍቀድ የመንግሥት ትልቁ ኃላፊነት መሆን ይገባዋል» ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ ለማህበረሰቡ ተብለው የሚከናወኑ የምክክር መድረኮች በራሱ በማህበረሰቡ መመራት አለባቸው።ፖለቲከኛው ባህል ላይ እንደሕዝብ ተሳታፊ ከመሆን ውጪ ተግባር አይኑረው ይላሉ።
ባህላዊ እሴቶች ውጤታማ፣ በኅብረተሰቡም ተቀባይነት ያላቸው መሆኑን በሀገራችን ከአንድ ዓመት በፊት ተከስቶ በነበረው ግጭት ወቅት የጋሞ አባቶች እርጥብ ይዘው ሊደርስ የነበረውን የበቀል እርምጃ ማስቆም ችለዋል። ይሄ የሚያሳየው ባህላዊ እሴቶች ዕድሉን ካገኙ ለአገራዊ አንድነት ትልቅ ጥቅም እንዳላቸው ነው።
ይህ በዚህ ከቀጠለ ደግሞ ስለራሱ እንጂ ስለ አገሩ የሚያስብ እንዳይኖር ይሆናል።አገር አንድነት ታጣለች።አገሪቱ ብቻ ሳትሆን ሌሎች አገራትም የሚኮሩበት ባህላዊ እሴት ይጠፋል።እርስ በእርስ መተማመን፤ መከባበርና ለአንድ አላማ መቆምም ያከትማል።በዚህም አገር እንደ አገር የመቀጠሏ ሁኔታ ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል።
አዲስ ዘመን ህዳር 14/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው