ባህር ዳር፡- ከግማሽ በላይ የሀገሪቱ የሕብረተሰብ ክፍል መፃፍና ማንበብ በማይችልበትና የንባብ ባህል በሌለበት ሁኔታ ኢትዮጵያን ወደ ብልፅግና ማሸጋገርም ይሁን ሰላምን ማምጣት አስቸጋሪ መሆኑ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጽሐፍት ኤጀንሲ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ‹‹ህዳር ሲታጠን፤ መጽሐፍ ሲተነተን›› በሚል ርዕስ የፓናል ውይይት አዘጋጅቷል። በውይይት መድረክ ላይ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ማረው አለሙ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ እንደገለፁት፤ አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል መፃፍና ማንበብ አይችልም፤እንዲሁም የተማረው የማንበብ ልምድን ባለማዳበሩ ምክንያታዊ የሆነ ትውልድን መፍጠር አልተቻለም።
የንባብ ባህልን ያላዳበረ ትውልድ ለሀገር ግንባታና ለሰላም እጦት ምክንያት ከመሆኑም በላይ ችግሮችን በውይይት የመፍታት አቅም እንደሌለው ጠቅሰው ይህም መሆኑ ማደግ ባለብን ልክ እንዳናድግ አድርጎናል ሲሉ አስረድተዋል።
እንደ ፕሮፌሰሩ ገለፃ፤ የማያነብ ሕብረተሰብ ችግሮች ሲፈጠሩ በውይይት ከመፍታት፣ በጥልቀት ከማሰብና ከመመርመር ይልቅ በስሜታዊነት መመራት ይቀናዋል። ማንበብ የመጠየቅን ፍላጎትን ያሳድጋል፤ ለሀገር እድገትና ለሰላም ከፍተኛ ሚናን ይጫወታል። በተለይ ተማሪዎችና ወጣቶች ንባብን ልምድና አንዱ የሕይወታቸው አካል በማድረግ በጭፍን መረጃ ከመውሰድ ተላቀው አስተዋይና አርቆ አሳቢ መሆን ይጠበቅባቸዋል ሲሉ አሳስበዋል።
ደራሲና መምህር ኃይለመለኮት መዋዕለ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ የተሟላ ሰው ለመሆን ማንበብ ወሳኝነት አለው። ማንበብ የሕይወት ብርሀን ነው። የአንድ ሀገር ትልቅ ሀብት መፅሀፍትና አሰላሳይ አንባቢያን ናቸው። አንባቢ ሕዝብ ካለ ሀገር ትገነባለች፤ የችግሮች ሰለባ አትሆንም።
መጽሐፍትን ማንበብ የእውቀት መነሻና መድረሻ በመሆኑ ወጣቱ ሊያዘወትር ይገባል ያሉት ደራሲው፤ የንባብ ልምድን ባለማዳበራችን ‹‹የአስተሳሰብ ድሀ ከመሆንም በላይ ልዩነታችን ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ የእርስ በእርስ ችግር ውስጥ ገብተናል›› ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጽሐፍት ኤጀንሲ የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ታዩ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ የወጣቱ የንባብ ባህል ባለማደጉ እንደ ሀገር ከፍተኛ ችግር እየደረሰ ነው። ትውልዱ አንባቢ ባለመሆኑ በአስተውሎት ከመመርመር ይልቅ በሀሰተኛ መረጃ እየተመራ ለሀገር አንድነት እንቅፋት እየሆነ ነው። ወጣቱ ባለማንበቡ የእውቀት ባለቤት ካለመሆኑም በላይ እንዳያስብና እንዳይጠይቅ ሆኗል።
“ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን ታይተው የማይታወቁ እኩይ ተግባሮች እየተፈፀሙ ነው” ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ለሀገር ግንባታ ከወጣቱ ብዙ ነገር ይጠበቃል ብለዋል። ወጣቱ ንባብን በማዳበር ስሜታዊነትን ወደ ጎን በመተው ለሀገር ሰላም ዘብ መቆም እንዳለበት አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 14/2012
ሞገስ ፀጋዬ