አዲስ አበባ፦ በሕገ መንግሥቱና በተለያዩ ሕጎች የተቀመጡ ድንጋጌዎችን ወደ ተግባር በመቀየርና ሕጎችን በድጋሚ በማሻሻል የዳኝነት ነፃነትን ለማስፈን እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ፡፡
የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ከዳኞች እና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ትናንት በኢንተርኮንቴንታል ሆቴል ምክክር ባደረጉበት ወቅት የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንትና የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ቃል አቀባይ አቶ ተስፋዬ ንዋይ እንደገለፁት፤ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትና በሌሎች ተያያዥ ሕጎች ላይ የዳኝነት ነፃነት እንዲኖር ድንጋጌዎች ቢኖርም በሚፈለገው አግባብ ወደ ተግባር ለመቀየር እንዳይቻል ብዙ ችግሮች ሲያጋጥሙ ቆይተዋል።
ይህን ለማስተካከል የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ 25/88 በድጋሚ የማሻሻል ሥራ እየተሰራ ነው።በተመሳሳይ የዳኝነት ረቂቅ አዋጅ ላይ ዳኞች ውይይት እንዲያደርጉ መድረክ መፈጠሩን ገልጸው እነዚህ ሥራዎች የዳኝነት ነፃነት እና ተጠያቂነት ሚዛኑን በጠበቀ መንገድ እንዲኖር ያስችላል ብለዋል፡፡
እንደ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ገለፃ፤ ከቅርብ ጊዜያቶች ወዲህ ዳኞች ሕግን ብቻ መነሻ በማድረግ ያለማንም ጣልቃ ገብነት ጉዳዮችን በመመልከት የመወሰን አዝማሚያዎችን እያሳዩ ነው።ሆኖም ይህ ሂደት በጅምር ደረጃ ያለ በመሆኑ ቀሪ ሥራዎች መሰራት አለበት።ዳኞች በራስ መተማመኑና ነፃነቱ እንዲኖራቸው ለማስቻል በሦስቱም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የተለያዩ ስልጠናዎችና ውይይቶች እየተደረገ ነው፡፡
‹‹የዳኝነት ነፃነት ለፍትህ፣ ለሕግ የበላይነት ብሎም ለሰብአዊ መብት መረጋገጥ ወሳኝ ነው›› የሚሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ ዳኞች ይህንን ተረድተው እንዲሰሩ በመደረግ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።የተሰሩ ጥናቶች ላይ ግኝቶች እንደሚያመለክቱት በሁሉም ዳኞች፣ በተገልጋዩና በአስፈፃሚ አካላት ‹‹በዳኝነት ነፃነት›› ላይ ተመሳሳይ ግንዛቤ የላቸውም።እነዚህ ችግሮች ላይ ውይይት በማድረግም ማሻሻያዎችን ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 14/2012
ዳግም ከበደ