ቢሾፍቱ፡- በውሃ ምትክ አጓትን በመጠቀም በምግብ ንጥረ ይዘቱ የበለጸገ ዳቦና የፍራፍሬ ጭማቂ ለማምረት የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ሥራ መጠናቀቁ ተገለጸ።
የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለሥልጣንና የኢትዮጵያ ስጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በጋራ ከኅዳር 11 እስከ 12 ለዘርፉ ሙያተኞች በቢሾፍቱ ከተማ በተሰጠው ተግባር ተኮር ሥልጠና ላይ ዳቦና የፍራፍሬ ጭማቂ በማምረት ላይ የተሰማሩ 12 ኢንተርፕራይዞች፣ አራት የሆቴልና ምግብ ዝግጅት የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና መምህራንና 10 የዘርፉ አስፈጻሚ አካላት ተሳትፈዋል።
በፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለሥልጣንና የአግሮ ፕሮሰሲንግ ዳይሬክተር አቶ የጠራወርቅ አያኔ ብዙ የወተት ፋብሪካዎች በተረፈ ምርትነት የሚያስወግዱት አጓት በፕሮቲን ይዘቱ ከፍተኛ ጠቀሜታ ስላለው ዳቦና የፍራፍሬ ጭማቂዎችን ለማምረት የምንጠቀምበትን ውሃ በመተካት የሚይዙትን ንጥረ ነገር ማበልጸግ እንደሚቻል በምርምር ተረጋግጦ ወደተግባር መገባቱን ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ ሦስት ጠቀሜታዎች አሉት የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ አንደኛ ፋብሪካዎች በተረፈ ምርትነት እየደፉት ከሚገኙት አጓት ተጨማሪ ገቢ ያገኛሉ ፤ ሁለት ለኢንተርፕራይዞቹ ተጨማሪ የሥራ ዕድል ይፈጥራል በሦስተኛነት ደግሞ ለኅብረተሰቡ በምግብ ይዘቱ የበለጸገ ዳቦና የፍራፍሬ ጭማቂ እንዲያገኝ ያደርጋል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ስጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አቶ መኮንን ጋሹ በበኩላቸው የኢንስቲትዩቱ አንዱ ሥራ በስጋና ወተት ምርቶች ላይ ምርምር ማድረግ መሆኑን አስታውሰው፣ ትኩረቱን አጓት ላይ ያደረገው ምርምር ከሌሎች የምርምር ማዕከላት ጋር በጋራ የተሰራ ነው ብለዋል።
ዳይሬክተሩ እንደገለጹት አጓት ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ልምድ በብዙ የወተት ተዋጽኦ አምራች ድርጅቶች መደፋቱ ኢኮኖሚያዊ ጉዳትና አካባቢያዊ ብክለት ያስከትላል።በተጨማሪም ኢትዮጵያ ከዘርፉ ማግኘት የነበረባትን ገቢ እንዳታገኝ ፤ ዜጎቿም ለምግብነት ቢያውሉት ሊያገኙ የሚችሉትን ጥቅም እንዳያገኙ ያደርጋል።የተለያዩ የአገር ውስጥ ተመራማሪዎች ይህን ችግር ለመቅረፍ አጓትን ጥቅም ላይ ማዋል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ጥናቶችን አድርገዋል።ሥልጠናው በምርምር የተገኘውን ውጤት ወደመሬት ለማውረድ የሚያስችል መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
ሽመልስ መስፍንና ጓደኞቹ የተባለውን ዳቦ አምራች ኢንተርፕራይዝ ወክለው በሥልጠናው የተሳተፉት ወይዘሮ እመቤት ዘነበ ሥልጠናው ዓይን ከፋች ነው ብለዋል።አክለውም በወሰዱት ሥልጠና መሠረት ወተት ፋብሪካዎች የሚያስወግዱትን ተረፈ ምርት በአነስተኛ ዋጋ በመግዛት የበለጸገ የምግብ ይዘት ያለው ዳቦ ለማምረት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአጓት የተሰሩ የፍራፍሬ ጭማቂዎችንና ብስኩቶችን ከፍ ባለ የውጭ ምንዛሬ ወደ አገር ውስጥ እንደምታስገባም ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 14/2012
የትናየት ፈሩ