እስኪ መላ በዪ መላ ከአንች ይገኛል፤ እኔማ ወንድ ነኝ ይደናገረኛል የሚል የአገር ቤት ዘፈን አለ። ‹‹ሴት መለኛ ናት›› የሚለው አባባልም ተደጋግሞ ይነገራል። አባባሉን ብዙ ሰዎች ሴቶች ተረጋግቶ የማሰብና መላ የመፍጠር አቅም እንዳላቸው ለመግለጽ ይጠቀሙታል። ‹‹ሴት የላከው ሞት አይፈራም›› የሚለው አባባል ደግሞ የሴቶች ትዕዛዝ ተቀባይነትና ተፈፃሚነት እንዳለው ለመግለጽ ይነገራል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ትናንት በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን አዳራሽ ‹‹ሴቶችና ሳይንስ›› በሚል ርዕስ የውይይት መድረክ አካሂዷል። በውይይቱም፤ ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናትን ጨምሮ ከተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተውጣጡ እና በሳይንስ ምርምር ያደረጉ ሴቶች ተሳትፈዋል።
በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም እና በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ ንግግሮች የተጀመረው ውይይት ዋና ጉዳዩን በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እየተከሰተ ባለው ግጭት ላይ አተኩሯል። በውይይቱ መክፈቻ ላይ የተገለጸው ሴቶች በሳይንስ ምርምር ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ እና በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ለሚከሰተው ግጭት ሴቶች ያላቸውን የሰላም ሚና የሚመለከት ቢሆንም የብዙ አስተያየት ሰጪዎች ሀሳብ ያተኮረው በዩኒቨርሲቲዎች ወቅታዊ ችግር በሆነው በሰላም ዙሪያ ሆኗል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኮሜርስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ የሆኑት ዶክተር አበበች አማረ እንደሚሉት፤ በዩኒቨርሲቲዎች እያጋጠመ ላለው ችግር ምክንያት ራሳቸው ወላጆች ናቸው። አሁን ያለው ልጅ የማሳደግ ባህል በፊት እንደነበረው አይደለም። ራሳቸውን ምሳሌ አድርገው ሲናገሩም፤ ‹‹እኔ ልጆቼን እያሳደኩ ያለሁት ወላጆቼ እኔን ባሳደጉብኝ መንገድ አይደለም›› ይላሉ። ቀደም ሲል የነበሩ ወላጆች ልጆቻቸውን ሲያሳድጉ ኃላፊነት መቀበልን እያለማመዱ ነበር፤ አሁን ላይ ለልጆች ኃላፊነትን ማለማመድ እየቀረ ነው።
ልጆች የጠየቁትን ሁሉ መስጠት ሳይሆን ምክንያታዊ የሆነ መከልከልም መኖር እንዳለበት ነው ዶክተር አበባ የሚናገሩት። ከልክ ያለፈ ለልጆች መብት መስጠት ኃላፊነት እንዳያውቁ ያደርጋል። በሌላ በኩል የስነ ምግባር ቀረጻ ላይም ወላጆች ላይ ችግር አለ፤ ከራሳቸው አስተዳደግ ጋር ሲያነፃፅሩትም፤ ባደጉበት አካባቢ አንድ ልጅ ከጎረቤት ልጅ ጋር ከተጣላ የሚቆጡት ሁሉም ወላጆች ናቸው፤ አሁን ግን በልጆች ጠብ ወላጆች ራሳቸው ሊጣሉ ይችላሉ። ወላጆች ቀድሞ የነበሩ የማስታረቅ ባህሎችንና የስነ ምግባር ቀረጻ ሊያጠናክሩ እንደሚገባም ያሳስባሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላም ማህበረሰብ አካዳሚክ ፕሮግራምና የምርምር አስተባባሪ ዶክተር ትዕግስት የሽዋስ እንደሚሉት፤ ግጭት ፈጣሪዎቹ ይታወቃሉ። አንዳንዴ ተማሪዎች ናቸው፣ አንዳንዴ ሰራተኞች ናቸው፣ አንዳንዴም ከህብረተሰቡ ውስጥ ነው። በእንዲህ አይነት ድርጊት ውስጥ በሚሳተፉ ሰዎች ላይ እርምጃ መወሰድ አለበት። ጠንከር ያለ መመሪያ ወጥቶ ተፈፃሚ ሊሆን ይገባል።
‹‹ፖለቲካ ከዩኒቨርሲቲ ውስጥ መውጣት አለበት›› የሚሉት ዶክተር ትዕግስት፤ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ካለ ከችግር መላቀቅ እንደማይቻል ይናገራሉ። ጠንካራ ተቋምና ጠንካራ መሪ መኖር አለበት። የሰላም ግንባታ ሥራ ለመሥራት ከላይ ወደታች ሳይሆን ከታች ወደላይ ነው መሰራት ያለበት።
ተማሪዎችን በተለያየ ሥራ ማሳተፍም መፍትሔ እንደሚሆን ዶክተር ትዕግስት ይጠቁማሉ። በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ውስጥ እና በግቢው ውስጥ በተለያዩ ክበባት ማሳተፍ ማህበራዊ መስተጋብራቸው እንዲጨምር ያደርጋል።
ከ እ ን ጅ ባ ራ ዩኒቨርሲቲ የመጡ ወይዘሮ የኔወርቅ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ችግሩ የመንግስት ነው እንደሆነ ይናገራሉ። የማህበራዊ ገጾችና ራሳቸው የህዝብ አገልጋይ የሚባሉ የመንግስት መገናኛ ብዙኃን ባልተጣራ መረጃ ግጭት ሲቆሰቁሱ ምንም እርምጃ አልወሰደም። ግጭቶችን ለማስቆም መንግስት መውሰድ ያለበትን እርምጃ አልወሰደም።
ለሚፈጠሩ ግጭቶች ሥርዓተ ትምህርቱም አጋዥ እንደሆነ ነው ወይዘሮ የኔወርቅ የተናገሩት። ግጭት እየፈጠሩ ያሉት ዝቅተኛ ውጤት እያመጡ ሦስትና አራት ጊዜ የተፈተኑ ተማሪዎች ናቸው። ‹‹ምን አይነት አዲስ ሥርዓተ ትምህርት እንደመጣ አላውቅም፤ ሁለት ነጥብ ያላመጡ ተማሪዎች ድጋሚ ተፈትነው ማለፍ አለባቸው ተባለ፤ ግጭቱን እየፈጠሩ ካሉት ተማሪዎች ውስጥ አንድም ጎበዝ ተማሪ አላየንም›› ያሉት ወይዘሮ የኔወርቅ፤ የትምህርት ሥርዓቱ መስተካከል እንዳለበት ያሳስባሉ።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም እንደገለጹት፤ ሴቶች በተፈጥሮ መላ የመፍጠርና ሰላምን የማምጣት ችሎታ ስላላቸው በእንዲህ አይነት አገራዊ ጉዳዮች ላይ ጠንክረው ሊሰሩ ይገባል። አገራዊ እሴቶችንና ነባር ባህሎችን የመመለስ ሥራ መሰራት አለበት። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ አኩሪ እሴቶች እየተሸረሸሩ መጥተዋል። ሥርዓተ ትምህርቱም ስነ ምግባር ያለው ትውልድ የመቅረጽ ክፍተት ነበረበት።
‹‹የትምህርት ሥርዓቱ በአግባቡ የተግባቦት ክህሎት ያለው፤ አገሩንና ወገኑን የሚያውቅ በስነ ምግባር የታነጸ ትውልድ አልቀረጸም፤ ከራሱ ከአካባቢውና ከክልሉ ቋንቋ ውጭ ከሌላው ጋር የሚግባባበትን ሳይዝ ዩኒቨርሲቲ እንድገባ ተደርጓል። ከተለያየ አካባቢ የሚመጣጡት የጋራ ቋንቋ የሌላቸው ናቸው›› ያሉት ፕሮፌሰር ሂሩት፤ ዩኒቨርሲቲዎች የተቀበሉት ተማሪ እርስበርስ እንዲጠላላ ተደርጎ የተቀረጸ ነው።
በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የመምህራን አቅም ክፍተት እንዳለም ሚኒስትሯ ተናግረዋል። የአመራሮች የብቃት ችግር አለ። በየደረጃው የማስተካከል ሥራ እየተሰራ ቢሆንም በአንድ ጊዜ ሊቀረፍ አይችልም። ከፍኖተ ካርታው በኋላ እነዚህን የማስተካከል ሥራ እየተሰራ ነው። በሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥም ሰላምና ስነ ምግባርን በተመለከተ ብዙ የተቀረጸ ኮርስ አለ።
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ሳህለወርቅ ፕሬዚዳንት እንደገለጹት፤ የሀሳብ ማፍለቂያ የሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች የግጭት መፍለቂያ መሆን የለባቸውም። ብዙ ውስብስብ ጉዳዮች ባሉባት አገር ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎች ከችግሮቻችን የምናመልጥባቸው የዕውቀትና የምርምር ማዕከላት ሊሆኑ ይገባል። ኢትዮጵያ ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ብዙ ትጠብቃለችና።
አዲስ ዘመን ኅዳር 13/2012
ዋለልኝ አየለ