– የሱዳን ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን የሦስት ቀናት ጉብኝት እያካሄደ ነው
አዲስ አበባ፡- በታንዛንያና የመን ለችግሮች ተጋልጠው የነበሩ 1403 ዜጎች ከአለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት/አይ.ኦ.ኤም/ ጋር በመተባበር ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።የሱዳን ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ከትናንት ጀምሮ የሦስት ቀናት ጉብኝት እያካሄደ ነው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው በወቅታዊ ጉዳዩች ላይ ትናንት በሰጡት መግለጫ፤ በየመን ለችግር ተጋልጠው የነበሩ 103፣ከታንዛኒያ ደግሞ 1300 ዜጎችን በድምሩ 1403 ዜጎች ወደ ሃገራቸው ለመመለስ በሂደት ላይ መሆናቸው ገልጸዋል።
በህገ ወጥ ደላሎች ተታልለው ሱዳን ውስጥ ለተለያዩ ችግሮች ተጋልጠው የነበሩ 100 ሴቶች በመተማ በኩል አቋርጠው ወደ አገራቸው እንዲገቡ መደረጉን ጠቁመዋል።
በሳዑዲ አረቢያ የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው ዜጎች ጥሪ በማቅረባቸው ኤምባሲው መረጃው እንደደረሰው ወኪሎችን በመላክ እስር ቤት ድረስ በመሄድ ዜጎቹን እንደጎበኛቸው ተናግረዋል። ፍርዱ ከመፈጸሙ በፊት ጠበቃ በማቆም የተቻለውን ለማድረግ የቅርብ ክትትል እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
በሱዳን ህዝቦች ዓለም አቀፍ ወዳጅነት ምክር ቤት ሴክሬታሪ ጀነራል ሳልዋ ሞሃመድ ማህጎብ የተመራው የሱዳን የህዝብ ለህዝብ ዲፕሎማሲ የሦስት ቀናት ጉብኝት እያካሄደ መሆኑን ጠቅሰው፣ ጉብኝቱ በሁለቱ ህዝቦች መካከል ያለውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማጠናከርን ዓላማው ማድረጉን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በሱዳን ሰላም እንዲሰፍን ላበረከተችው አስተዋጽኦ የልዑካን ቡድኑ ምስጋና ማቅረቡም ተገልጽዋል ።
ቡድኑ በኢትዮጵያ ቆይታው የአንድነት ብሄራዊ ፓርክ፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሙዚየምና የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክንም ይጎበኛል።
የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድንም በቅርቡ ለጉብኝት ወደ ኡጋንዳ ይጓዛል ያሉት ቃል አቀባዩ፤ ጉብኝቱ የሁለቱን አገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በማጠናከር ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ለማሳደግ እንዳለመም አመልክተዋል።የልዑካን ቡድኑ ከፕሬዚዳንቱ ዮዌሪ ሙሰቬኒ፣ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ከኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲና ከሌሎች አካላት ጋር ይወያያል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተመለከተ ሱዳን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክትን ከጅምሩ እየደገፈችው እንደምትገኝና በቀጣይ በግድቡ ዙሪያ ሦስት የቴክኒክ ስብሰባዎች እንደሚካሄዱ አቶ ነብያት ገልጸዋል። በቴክኒክ ቡድንም ሆነ በመሪዎች ደረጃ በሚደረገው ውይይት ሱዳን ፕሮጀክቱን ከጅምሩ እየደገፈችው እንደምትገኝም ገልጸዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከአውሮፓ ህብረት አባል አገራት አምባሳደሮች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን የገለጹት አቶ ነብያት፤ በውይይቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ሃላፊነት ከመጡ በኋላ ከጎረቤት አገሮች ጋር እየተደረገ ስላለው ስኬታማ ግንኙነትና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ለመፍጠር እየተሰሩ ስላሉ ስራዎች ማብራሪያ መሰጠቱን አመልክተዋል።
ኢኮኖሚያዊ ትስስሩን ለማፋጠን የምስራቅ አፍሪካ በየነ መንግስት (በኢጋድ) በኩል እየተከናወኑ ስላሉ ስራዎችና በአባይ ወንዝ ላይ ኢትዮጵያ እየገነባችው ስላለው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ወቅታዊ ጉዳዩች ዙሪያ፣ በግንቦት ወር የሚካሄደውን አገራዊ ምርጫና የምርጫ ተቋማትን የማጠናከር አጠቃላይ ተግባሮችና በሲዳማ የተካሄደውን ህዝበ ውሳኔ አስመልክቶ አቶ ገዱ ለአምባሳደሮቹ ማብራሪያ መስጠታቸውንም አመልክተዋል።
አዲስ ዘመን ኅዳር 13/2012
ዘላለም ግዛው