አዲስ አበባ:- የኢህአዴግን ውህደት በተመለከተ የሰባት ሀገራት ተሞክሮ መወሰዱን የውህደቱን ጥናት ካከናወኑ ባለሙያዎች መካከል አንዱ የሆኑት ዶክተር ሙሉ ነጋ ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት እና ስነባህሪ ጥናት ኮሌጅ መምህር እና የኢህአዴግ ውህደት ጥናት አባል ዶክተር ሙሉ ነጋ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ የኢህአዴግን ውህደት በተመለከተ የ28 ሀገራትን ተሞክሮ ለማየት ተሞክሯል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ የቤልጂየም፣ ስዊዘርላንድ ፤ ናይጀሪያን ከመሳሰሉ ሰባት ሀገራት የፌዴራሊዝም የፓርቲ አሰራት ላይ ጥናት ተደርጎ ልምዶች ተቀስመዋል።
እንደ ዶክተር ሙሉ ከሆነ፤ በ ውህደት ጥናቱ ላይ የተሳተፉ ባለሙያዎች በመጀመሪያ ስድስት ቢሆኑም ሁለቱ በሹመት በተለያየ ስራ ላይ በመመደባቸው አራት ባለሙያዎች ጥናቱን አከናውነው ጨርሰዋል። ሙያዊ አሰራሩን ተከትሎ በገለልተኛ ባለሙያዎች የተጠናውን የውህደት ጥናት ኢህአዴግ ወስዶ ለውይይት አቅርቦታል። በዚህም መሰረት ሀገራዊ አስተሳሰብ ያለው እና ሁሉንም ዜጎች ያሳተፈ አካሄድ ያላቸው የአውሮፓ፤ አሜሪካ እና አፍሪካ አገራት ተሞክሮ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።
ጥናቱ የተካተቱ ሀገራት የፖለቲካ አካሄድ ልዩነት ቢኖረውም አብዛኛዎቹ በሀገራዊ ጥንካሬ ላይ ተመስርተው እንደሚሰሩ መታየቱን የጠቆሙት ዶክተር ሙሉ፣ ለአብነት በቤልጂየም ሶስት ፓርቲዎች በጥምር መንግስት በመመስረት ስለቤልጂየም ሀገራዊ ጥንካሬ አላማ አድርገው እንደሚሰሩ እና ተሳትፎአቸውም በብዝሃነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን አስረድተዋል።
ይህም አካታችነት፣ ማህበራዊ ፍትህ እና ዴሞክራሲ ላይ የበለጠ እንዲሰሩ እንዳደረጋቸው በጥናቱ መታየቱን ተናግረፈዋል። ኢትዮጵያ ግን ስከአሁን የነበረው አካሄድ አራት ብሔራዊ ድርጅቶች ብቻ ወሳኝ ቦታ ላይ በመቀመጥ አጋር የተባሉ ፓርቲዎችን አግልሎ የቆየ ሲሆን አሁን ኢህአዴግ ወደ ውህደት በማምራቱ ችግሩን ይፈታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
እንደ አቶ ሙሉ ከሆነ፤ፓርቲው አጋር ድርጅቶችን አስገብቶ አካታች የሆነ ውህድ ፓርቲ ለመመስረት በሚደረገው ጥረት ህወሃት ከውህደት ቢወጣም የሚያሳስብ ጉዳይ አይደለም። ምክንያቱም ኢህአዴግ ሀገራዊ እይታ ያለው ፓርቲ ሆኖ ትክክለኛ የዜጎች ተሳትፎን ያረጋገጠ ስርዓት መመስረት ከቻለ ነገሮች አስቸጋሪ አይሆኑም።
ከ1997 ምርጫ በኋላ ቅንጅት ፓርቲ አዲስ አበባን ለማስተዳደር ጫፍ ደረሶ የነበረበት አካሄድ ለዚህ ማሳያ መሆን ይችላል የሚሉት ዶክተር ሙሉ፤ ተግባራዊ ባይደረግም ቅንጅት ከኢህአዴግ ጋር አብሮ ሳይሰራ ከተማዋን እያስተዳደረ መስራት እንደሚችል ግን ሁኔታው ማሳያ እንደነበረ አስታውሰዋል። በመሆኑም ህወሃት ከፓርቲ ውህደቱ ውጪ ቢሆንም ከፌዴራል መንግስት ጋር ተጣጥሞ ለመስራት አስቸጋሪ ነው ብሎ ስጋት ውስጥ መግባት እንደማያስፈልግ ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ኅዳር 13/2012
ጌትነት ተሳፋማርያም