ሙከጡሪ፡- በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ውጫሌ ወረዳ 300 ሚሊዮን ብር በላይ የወጣባቸው የሲሚንቶ፤ ጀብሰም እና ብርጭቆ ፋብሪካዎች ያለ ሥራ መቆማቸው ተገለፀ። ባለሃብቶቹ በወሰዱት ፈቃድ ከመስራት ይልቅ ሌላ አማራጮች ላይ ማማተር መጀመራቸውም ተጠቁሟል።
የዋጫሌ ወረዳ ኢንቨስትመንት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ድሪባ ነጌ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፤ ፋብሪካዎቹ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠሩ ቢሆንም በታቀደው ልክ ሥራ ማከናወን አልቻሉም፤ የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድም ደካማ ናቸው ሲሉ ወቅሰዋል። በተለይም በሙከጡሪ ከተማ የተገነቡ የሲሚንቶ፣ ብርጭቆ እና ጅብሰም ፋብሪካዎች በታቀደላቸው መርሐ ግብር ሥራ መስራት አለመቻላቸውን አብራርተዋል። በርካቶቹም ሠራተኞቻቸውን የበተኑ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ምርት ማቆማቸውን አረጋግጠዋል።
እንደ አቶ ድሪባ ገለፃ፤ ፋብሪካዎቹ በአማካይ ከ10 እስከ15 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሲሆን ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ የወጣባቸው ናቸው። ሆኖም ለአገር ማስገኘት ከሚገባቸው ጥቅም አኳያ ወደ ኋላ መቅረታቸውን ገልፀዋል። ችግሮቻቸውን አቃልለው ወደ ሥራቸው እንዲገቡም የተለያዩ ድጋፎች ቢደረጉም ስኬታማ እንዳልሆኑ አብራርተዋል።
የዋጫሌ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ወልደዮሐንስ አበራ በበኩላቸው፤ የፋብሪካዎቹ ግንባታ ሲጀመር በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ደስታ ተፈጥሮ የቆየ ሲሆን ለአካባቢው ማህበረሰብም ሥራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ ትልቅ ተስፋ ተጥሎባቸው እንደነበር አስታውሰዋል። ይሁንና ፋብሪካዎቹ ለዓመታት ያለ ሥራ መቆማቸውን ነው የጠቆሙት። በተለይም ‹‹ጀማ ሲሚንት›› የሚል መጠሪያ ያለው ፋብሪካ ሥራው አዋጭ ስላልሆነ የሥራ ዘርፍ ለመቀየር ፍላጎት ማሳየታቸውንና ወተት ማቀነባበሪያ የማድረግ ጥያቄ አቅርበው ውድቅ መደረጉን ጠቁመዋል።
ምናልባትም ዘርፍ መቀየር ከፈለጉም ወደ ብረታ ብረት ዘርፍ ማዛወር እንደሚችሉ በባለሙያ ምክር መሰጠቱን አስገንዝበው፤ በዚህ ላይ ውይይት ማድረጋቸውን አስታውሰዋል። ይሁንና የድርጅቱ ባለቤቶች ወደ ተግባር መግባት አለመቻላቸውንና በወረዳው ላይ ጫና መፈጠሩን ገልፀዋል። በህዝቡ ዘንድም የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ ቅሬታ እየቀረበበት መሆኑን አስገንዝበዋል።
እንደ አቶ ወልደዮሐንስ ከሆነ፤ ፋብሪካዎቹ የጥሬ ዕቃ እና አስፈላጊ ግብዓቶች ዋጋ መጨመር በሥራቸው ላይ ተወዳዳሪ እንዳንሆን አድርጎናል የሚል ቅሬታ ያቀረቡ ሲሆን፤ ሌሎች አማራጮች ላይ እያማተሩ መሆኑን አስረድተዋል። ይሁንና ፋብሪካዎቹን ወደ ሌላ ዘርፍ የመቀየር ፍላጎት ያሳዩ እንጂ በተግባር ብዙም እየተንቀሳቀሱ አይደለም ብለዋል።
በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ አስቴር ዘውዴ እንዳሉት፤ ችግሩ በትክክል መኖሩን ጠቁመው ፋብሪካዎቹ ከታለመላቸው እቅድ ውጭ ያለሥራ መቀመጣቸው አሳዛኝ መሆኑን አብራርተዋል። ችግሮቻቸውን አቃለው ወደ ሥራ እንዲገቡ በተደጋጋሚ ከክልል እስከ ወረዳ ድረስ አቅጣጫዎች መቀመጣቸውንና ድጋፎች እየተደረጉ ቢሆንም የታሰበው ሊሆን እንዳቻለ አስረድተዋል። በቀጣይም ድጋፍ የሚስፈልግበት ቦታ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅነቱ መኖሩን ጠቁመው፤ በዚህ ሂደት ውስጥ ወደ ሥራ የማይገቡትን ግን እንደማይታገስ አስገንዝበዋል።
በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ ያሉት የየፋብሪካዎቹ የጥበቃ ሠራተኞች በበኩላቸው፤ የድርጅቱ ባለቤቶችን በውል እንደማያውቁና በየጊዜው የተለያዩ ሰዎች ወደ ግቢው እየመጡ ምልከታ አድርገው እንደሚሄዱ አስታውቀዋል። በተለያዩ ወቅቶችም ‹‹ኃላፊ እኔ ነኝ›› በሚል ሰዎች መምጣታቸውን እንጂ ማንነታቸውን እንደማያውቁ ጠቁመዋል። የደመወዝ ጭማሪ ሆነ ሌሎች ጥቅማጥቅሞችም እንደማይከበርላቸው አስረድተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ደመወዛቸውን በአካውንታቸው መግባቱን እንጂ የሚከፍላቸው አካል በትክክል እንደማያውቁ አስረድተዋል። በየፋብሪካዎቹ ውስጥ ያሉ ሠራተኞችም ከመበተናቸው ውጭ በቀጣይ ምን እንደታሰበላቸው እንደማያውቁ ለዝግጅት ክፍላችን ጠቁመዋል። በየፋብሪካው ውስጥ ያሉ የተለያዩ ንብረቶችም በዝናብና ፀሐይ ፍርቅርቆሽ እየተበላሹ መሆኑን አስረድተዋል።
አዲስ ዘመን ኅዳር 13/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር