የዛሬው እንግዳችን ፕሮፌሰር ፍሰሀጽዮን መንግስቱ ይባላሉ። ኤርትራ ውስጥ በ1939 ዓ.ም ነው የተወለዱት። ከኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ጋር አንድ ትምህርት ቤት በወቅቱ ልዑል መኮንን የተሰኘው ትምህርት ቤት ነው የተማሩት። 12ኛ ክፍልን ሲያጠናቅቁ ወደአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማቅናት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በህግ ትምህርትይዘዋል። በእንግሊዝ ሊድስ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ለሶስተ ዓመታት ተከታትለዋል። ከዚያም ወደ ሆላንድ በመሄድ ለ33 ዓመታት በማስተማር እና በመማር ጊዜያቸውን አሳልፈዋል።ሶስተኛ ዲግሪያቸውንም ከአምስተርዳም የኒቨርሲቲ ተቀብለዋል ፡፡ ትዳርም የመሰረቱት በርካታ ዓመታትን ባሳለፉበት ሆላንድ ውስጥ ነው።
በሆላንድ የኢትዮጵያውያን ማህበርን ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በማቋቋም የተለያዩ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ሲሳተፉ ነበር። ከእነ ኮሎኔል ጎሹ ጋር በመሆን መድህን የተሰኘውን ፓርቲ በአውሮፓ እና በአሜሪካ መስርተው ሲታገሉ ቆይተዋል። የድርጅቱም ምክትል ፕሬዝዳንት ከመሆን ባሻገር የአውሮፓ ዋና ተጠሪና ኃላፊ ሆነው ሰርተዋል። በታክስና ኢንቨስትመንት ፋይናንስና የዓለም አቀፍ ሕግ ላይ ደግሞ ለረጅም ዓመታት የዘለቀ ልምድ አካብተዋል።
በውጭ ሀገር እና በሀገር ውስጥ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በሙያቸው አስተምረዋል። በኢኮኖሚ እና ፖሊሲዎች ላይ ያተኮሩ በርካታ መጽሃፍትን እና የጥናት ወረቀቶችን አሳትመዋል። የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም ከእኒሁ አንጋፋ ምሁርና የፖለቲካ ሰው ጋር ቆይታ አድርጓል ፤ መልካም ንባብ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ስለሃገር ወዳድነት ብዙ ጊዜ ሲያወሩ ይደመጣል። ሀገር ወዳድ ነኝ ብለው ያስባሉ?
ፕሮፌሰር ፍሰሀጽዮን፡- ላለፉት 50 ዓመታት በታክስ፣ ኢንቨስትመንትና ፋይናንስ እንዲሁም በህግ ዙርያ ሳስተምር እና ስማር የቆየሁ ሰው ነኝ። በአፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ደግሞ የገንዘብ ሚኒስቴር የታክስና ኢንቨስትመንት ጉዳዮች ላይ በማማከር ሰርቻለሁ። በውጭ አገር በኮሙኒኬሽን እና በተለያዩ መስኮች ሳስተምር ቆይቻለሁ። በሀገሬ ጉዳይ ላይ የማልደራደር እና ስታገል የቆየው ሰው ነኝ። በሀገር ቤት ደግሞ በሰባት ዩኒቨርሲቲዎች በማስተማር ስሰራ የቆየሁ ሀገር ወዳድ ዜጋ ነኝ ብዬ አፌን ሞልቼ እናገራለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የጥቁር ህዝቦች አለኝታ ነች የሚል ሃሳብ በተለያዩ ጊዜያት ሲያነሱ ተደምጠዋል ይህ ከምን የተነሳ ነው?
ፕሮፌሰር ፍሰሀጽዮን፡- በአንድ በኩል ጸረ ቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ስላለኝ ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ለጥቁሮች አለኝታ መሆኗን አምናለሁ። በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው ረገድ ለጥቁሮች አለኝታ መሆን ትችላለች ብዬ ስለማስብ ነው።
እኔ ቀደም ባለው ጊዜ ስማር ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት 60 ዓመታት ውስጥ እራሷን መግባ ጎረቤቶቿን እና የአረቡን ፔንሲዌላን ትመግባለች እየተባልዕኩ ነው ያደግኩት። አሁን ላይ ሲታይ ይህ አልሆነም። አለመሳካቱ ደግሞ በእጅጉ ያስቆጣል፣ ያማል። ይሁንና እኔ ኢትዮጵያ የጥቁር ህዝብ አለኝታ እንድትሆን እና በአንድነቷ እንድትቀጥል ነው በግሌ ስታገል የቆየሁት። ሀገሬ ልክ እንደቻይና ጠንካራ ሀገር ሆና፤ በቴክኖሎጂው አድጋ፤ በኢኮኖሚው በልጽጋ እያንዷንዱ የዳቦ ጥያቄ ሳይኖረው የተስተካከለ ነገር ተሰርቶ ኢትዮጵያ የጥቁር ህዝቦች አለኝታ እንድትሆን ምኞቴ ነው፤ ለዚህም ታግያለሁ።
የኤርትራንም መገንጠል የምቃወመው በዚህ ምክንያት ነው። ኢትዮጵያ ሲባል ኤርትራንም ጨምሮ ነው እንደትልቅ ሀገር ሆኖ ጠንካራ ኢኮኖሚ በመመስረት ለአፍሪካም የሚተርፍ ስራ ማከናወን የሚቻለው ብዬ ነው የማምነው። እናም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ብቻ ሳይሆን የጥቁር ህዝቦች አለኝታ እንድትሆን የሚያስችላትን አንድነትን እና ህብረትን እደግፋለሁ።
አዲስ ዘመን፡- በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን፣ በደርግ ብሎም እስከ ኢህአዴግ ዘመን ያለውን የኢኮኖሚና የፖለቲካ አካሄድ ታዝበዋልና እያንዳንዱ ላይ ምን አይነት ጥንካሬና ችግር አይተዋል?
ፕሮፌሰር ፍሰሀጽዮን፡- በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን ኢኮኖሚው ሰሚ ፊውዳል ሰሚ ካፒታሊስት ነበር። አብዛኛው ሰው ድህነት ውስጥ የነበረበት በመሆኑ ካፒታሊስት ስርዓቱ ሊስፋፋ አልቻለም። በርካቶች ድሃ በመሆናቸው ደግሞ የመሬት ሪፎርም እንደሚያስፈልገው ተማሪ በነበርንበት ጊዜ ታዝበናል። ይሁንና ድህነት የበዛበት ቢሆንም የመንግስት ባለስልጣናት ሀገር ወዳድ ናቸው፡፡ ወጣቱም የሚያስበውም ሆነ ለሀገሩ የሚመኘው በጎ ነገር ነበር ፡፡ በተጨማሪ የተሰሩ ጠንካራ ስራዎች ነበሩ። አሁን ላይ በጠንካራነታቸው የሚመረጡት እንደ አየር መንገድ እና ንግድ ባንክ እና ባህር ትራንስፖርት ማየት ቢቻል የተቋቋሙት በዚህ ወቅት ነው።
በደርግ ዘመን ደግሞ መሰረታዊው የህዝቡ ፍላጎት ማሟላት ቢቻልም አብዛኛው ጊዜ በጦርነት ነው ያለፈው። አንድ ሶስተኛው ተማሪ በደርግ አብዮት ጊዜ ሞቷል። መሪዎቹ አረመኔያዊ ድርጊት ቢፈጽሙም ግን በሙስና ደግሞ አይታሙም፤ ሁሉም ባለስልጣን ሀገር ወዳድ ነበር። ይሁንና በሶሻሊስት ስርዓቱ ሁሉ ነገር ከላይ ወደታች ነበር የሚመጣው። ህብረተሰቡን ያሳተፈ ስራ አልነበረም። የመጻፍና የመናገር መብቱም አልነበረም። ከታች ወደላይ ከህብረተሰቡ የሚሄድ ተሳትፎ ስላልነበረ እና የጦርነቱ መብዛት የደርግን ዘመን ፈታኝ አድርጎታል እንጂ የመሰረታዊ ፍጆታ ችግር አልነበረም።
አዲስ ዘመን፡- በኢህአዴግ ጊዜ የኢኮኖሚውን አካሄድ ምን ጥንካሬና ስህተት አይተውበታል?
ፕሮፌሰር ፍሰሀጽዮን፡- በኢህአዴግ ዘመን ደግሞ ካፒታሊስ ባልተስፋፋበት እና ጥቂት ባለሃብቶች በነበሩበት እንደ ኢትዮጵያ ባለ ሃገር ልማታዊ መንግስት መሆኑ ችግር አልነበረውም። የግል ዘርፉ ጠንካራ ካፒታል የሌለው እና ዘላቂነት ያልነበረው በመሆኑ መንግስት ጣልቃ በሚገባበት ወቅት አካሄዱ ብልሃትና እና ጥንካሬ /Smart and Intelligent / የተሞላበት አልነበረም። በየትኞቹ ዘርፎች ላይ ብገባ ውጤታማ ሆኜ ለህብረተሰቡ ምን ማውቅረብ እችላለሁ የሚል ጥናት ተግባራዊ አልተደረገም።
በመሰረታዊ ፍጆታዎች ላይ ግን ቁጥጥር መደረግ ነበረበት። በደርግ ዘመን የነበሩት 400 የመንግስት ሰፋፊ እርሻዎች ቢኖሩ እኮ ለነጋዴው እና ለህብረት አማራጭ ስለሚሆኑ በምግብ በኩል ያለው የዋጋ ግሽበት አይኖርም ነበር። ነጋዴውም እንደፈለገ ሲሸጥ ቁጥጥር አይደረግም፤ መንግስትም እንደፈለገ ታክስ ያስከፍላል። አሁን ያለው የካፒታሊስት ኢኮኖሚ በነጻ ገበያ ስም ያለ ነጻ ብዝበዛ ነው።
በሌላ በኩል ሀገር ወዳድነቱ ስለጠፋ ሙስና ውስጥ የገቡ ባለስልጣናት በርካታ ናቸው። ይህ ችግር ለመቅረፍ ቁጥጥሩን ማጠናከር ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በጎዳ መልኩ ባለስልጣናት በፈጸሙት ሙስና ምክንያት በቢሊዮን ብሮች ባክኗል። ይህን ገንዘብ ኢኮኖሚው ውስጥ ዳግም ለማንቀሳቀስ ምን አይነት አሰራር ያስፈልጋል ይላሉ?
ፕሮፌሰር ፍሰሀጽዮን፡- በመጀመሪያ ደረጃ በሙስናው ምክንያት የጠፋውን ገንዘብ ለማስመለስ ቆራጥ መንግስት ያስፈልጋል። እራሱ ከሙሰኝነት ጸድቶ ቁጥጥር ውስጥ የሚያስገባ እና ያለአግባብ ያከማቹትን ገንዘብ ወደህብረተሰቡ ጥቅም ማዞር የሚችል ቆራጥ መንግስት ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- ይህ ቆራጥነት የሚሉት አካሄድ እስከምን እርምጃ ድረስ ይሄዳል?
ፕሮፌሰር ፍሰሀጽዮን፡- አንዳንዶቹ የህዝብንና የመንግስትን ንብረት ዘርፈው ሲያበቁ ህብረተሰቡን ከድህነት እናወጣለን ብለው መልቲ ቢሊየነር ሆነዋል። እኔ ብሆን የነዚህን ሰዎች ሃብት እንዲወረስ አድርጌ ለህብረተሰቡ ጥቅም አውለዋለሁ።
ሙስና የፈጸሙትን ግለሰቦችም ቻይና እንደምታደርገው እርምጃ ሁሉ በኢትዮጵያ ደግሞ
ለማስተማሪያ ያክል የተወሰኑት ላይ እርምጃ ያስፈልጋል። ይህ ማለት ግን <<አናርኪዝም>> ወይም ጭካኔ የተሞላበት አገዛዝ አይደለም። ሁሉም ነገር ስርዓትና ገደብ ስላለው ነው። አሁን ግን ይህ ምንም አይታይም። ይልቁንም ሁሉም እንደፈለገ ያደርጋል።
ሙስና የሚያስፋፉ እና አገርን የሚበታትኑ ሰዎች ካሉ በተመሳሳይ ቅጣት ያስፈልጋቸዋል። እኔም የህግ ልዕልናን የማውቅ የህግ ሰው ብሆንም አንድ ሰው የራሱን መብት አስከብሮ የሌላውን ካላከበረ መቀጣት እንዳለበት አምናለሁ። ካጠፋ ትንሹን አሳ ሳይሆን ትልቁን በመያዝ መቅጣት ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ ችግር ከታየበት ወንድም ይሁን ጓደኛ አሊያም የእኔ ጎሳ እና ሐይማኖት ይሁን ወንጀል ከሰራ በህጉ መሰረት መቀጣት አለበት።
አዲስ ዘመን፡- በፋይናንስ ዘርፉ ለወጣቱ ስራ ፈጠራ ተብሎ በርካታ ቢሊዮን ብሮች ቢመደብም የታለመለትን ያክል ውጤት ማምጣት ግን አልተቻለም ተብሎ ይተቻል ፡፡ የዚህ ችግር ዋነኛ መንስኤ ምንድን ነው?
ፕሮፌሰር ፍሰሀጽዮን፡- ተጠያቂነት እና ግልጽነት ያለው አሰራር የለም። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በነበሩበት ወቅት 10 ቢሊዮን ብር ለወጣቶች ፈንድ ተብሎ ተመድቦ ነበር። እናም ወጣቱ ይህ ገንዘብ የት ደረሰ ብሎ መጠየቅ መቻል አለበት። እንደመንግስት ግን ይህንን ገንዘብ መቆጣጠር የሚችል ተቋም መኖር ነበረበት። የተሳሳቱ ሪፖርቶች ሲቀርቡ ዝም ይባላል። ሳይሰሩ ሰርተናል ይባልና የሙስናን መቆጣጠሪያ መንገዱ የላላ ይሆናል።
ነጻና ገለልተኛ አስተሳሰብ ያላቸውን ተቆጣጣሪ ተቋማት በጀት እና ታክስን ጨምሮ የተለያዩ የፋይናንስ ጉዳዮች ላይ የሚገኘውን ገንዘብ የት ደረሰ እና በእርግጥ ለታለመለት አላማ ውሏል ወይ? የሚለውን እያንዳንዱን ሳንቲም መቆጣጠር መቻል አለባቸው። ይህ ችግር ባለበት የሚወጣውንም ፖሊሲ ይሁን ህጉን ተግባራዊ ማድረግ አይቻልም።
ከዚህ በተረፈ ደግሞ ወጣቱም ስለሀገር ወዳድነት እና ስነምግባር ማስተማር ያስፈልጋል። ይህ ካልሆነ ተስፋ በመቁረጥ ውስጥ ስለሚገባ ችግር ይበረታል። በመሆኑም ከቤት ጀምሮ እስከ ሃይማኖት አባቶች እና ህብረተሰቡ ወጣቱን ስለሀገር ወዳድነት እና ሃቀኝነት ሊያስተምሩት ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ከወጣቱ ባለፈ የመንግስት ሰራተኛው ከደመወዙ ላይ በአግባቡ ግብሩን እየከፈለ ቢኖርም የኑሮ ውድነቱን አልቻልኩትም እያለ ቅሬታ ያነሳል ፤ በሌላ በኩል የመንግስት ሰራተኛው ተገቢውን አገልግሎት መስጠት አልቻለም የሚሉ ወቀሳዎች አሉ፤ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?
ፕሮፌሰር ፍሰሀጽዮ፡- እኔ ከመንግስት ሰራተኞች በርካታ ሰዎችን አውቃለሁ፤ አንዳንድ ሙሰኞች ካልሆኑ በስተቀር በአብዛኛው በድህነት ላይ ነው የሚገኘው። መንግስት የእራሱን ሰራተኞች ችግራቸውን አውቆ በአግባቡ ችግራቸውን አልፈታም ብዬ አምናለሁ።
የሲቪል ሰርቫንቱን ስራ ያሻሽላሉ የተባሉ ሪፎርሞች ተግባራዊ ቢደረጉም ሊያዋጡን አልቻሉም። ምክንያቱም የሌላውን ሀገር አሰራር ሙሉውን ኮፒ አድርገን ነው የምናመጣው። የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ተብሎ ይቀርባል ነገር ግን ከኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ጋር መጣጣም ነበረበት።
የሀገሪቷን ታሪክ፣ ባህል፣ አኗኗር ወቅታዊ ሁኔታ እና ሌሎችንም ጉዳዮች አካቶ የቀረበ የመፍትሄ ሃሳብ ማምጣት እንጂ የቻይናን ኮፒ አድርገው ቢያመጡት እኛ ኢትዮጵያዊያን ነንና ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እያመዘነብን መጥቷል።
አዲስ ዘመን፡- መንግስት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ አካሄድ በመቀየር በሀገር በቀል የኢኮኖሚ መርህ ለመምራ ስራዎችን ጀምሯል። ጉዳይ ላይ መንግስት ምን አካሄድ ቢከተል ጥሩ ነው ይላሉ?
ፕሮፌሰር ፍሰሀጽዮን፡- መንግስት ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ስርዓት ያስፈልገኛል ካለ በመጀመሪያ ሀገር ወዳድ ምሁራንን ማቅረብ መቻል አለበት። የሀገሩን ምሁራን በመሳብ ችግሩ ላይ መፍትሄ ለማምጣት መስራት ይኖርበታል። በቅርቡ ሀገር በቀል ኢኮኖሚ አካሄድ መከተልን የሚያስተዋውቀውን እና በመንግስት በኩል የቀረበውን ጽሁፍ አይቼዋለሁ። ይሁንና ጽሁፉ ዝርዝር ጉዳዮችን የያዘ ባለመሆኑ እንዴት ይፈጸማል? የሚለውን የካተተ አይደለም።
ሀገር በቀል ከሆነ ምን ያክል በእርሻው፣ በታክስና ኢንቨስትመንት እና በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ምን ያክል መስራት ይቻላል? የሚለውን እና ምን አይነት የሀገር ውስጥ ምሁራንን አካቷል? የሚለው መታወቅ ነበረበት። እኛ ሀገር የውጭ ሰዎችን የማቅረብ እንጂ በሀገር ሰው የመጠቀም ችግር አለ። በቅድሚያ ሀገር ውስጥ ያሉ ምሁራንን ዕውቀት መንግስት ሊጠቀምበት ይገባል።
በተረፈ ግን ለምን ሀገር በቀል እንደተባለ እራሱ አይገባኝም፤ እንደውም ከመንግስት ነው ስለአዲሱ የኢኮኖሚ አማራጭ ማብራሪያ የምፈልገው።
አዲስ ዘመን፡- የዶክተር አብይ የአንድነት አስተሳሰብ ሰፋ ያለ በመሆኑ ከኢትዮጵያም አልፎ በምስራቅ አፍሪካም ጭምር ስላለው የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ዕይታ አለውና ከዚህ አንጻር ምን አይነት አካሄድ ያስፈልጋል?
ፕሮፌሰር ፍሰሀጽዮን፡- በመጀመሪያ ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት ካስፈለገ የሀገር አንድነትን በማጠናከር ብሔርን ሳይሆን ኢትዮጵያዊነትን እያቀነቀኑ እና ህብረተሰቡን እያሳተፉ ነው መስራት የሚያስፈልገው። ከዚህ ባለፈ ግን ምርትን በከፍተኛ ሁኔታ በማሳደግ ህዝቡ ዳቦ ጠግቦ እንዲያድር በቅድሚያ መስራት ያስፈልጋል። ይህን ሳናደርግ ወደ ሌላ ጨረቃ መሄድን ማሰብ አያስፈልግም።
አሁን እኮ ሱፐር ማርኬት ቢኬድ የሚገኘው አብዛኛው ምርት ከቻይና የመጣ ነው። በኮንስትራክሽን ዘርፉም ቢኬድ ቻይናዎች ናቸው የበላይነት የወሰዱት። አገር ደግሞ የሚያድገው በእራሱ ዜጋ ላይ ሲመሰረት ነው፡፡ በውጪ ዜጎች ስራ ብቻ ሀገር የሚፈለገውን ያክል ማደግ እንደማትችል የብራዚልን እና የአርጀንቲና ተሞክሮ ማየት ይቻላል።
ከኢትዮጵያ አልፈን ለመወዳደር የሚያስችሉን ሁኔታዎችን ቀድመን ስለማመቻቸት ማሰብ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ እውነተኛ ሀገር በቀል ባለሃብቶችን በመደገፍ ተወዳዳሪ ስራ እንዲያከናውኑ ማድረግ ይገባል። የግል ሴክተሩ በኢትዮጵያ በቂ ገንዘብ እና ዕውቀት ስለሌለው የአቅም ግንባታ እያከናወኑ ማጠናከር ያስፈልጋል። አቅምን በማሳደግ በገንዘቡ ብቻ ሳይሆን በትምህርት ጥራትም ላይ በመስራት ከሌላው ዓለም ጋር የሚወዳደሩ ምርቶችን ለገበያ ማቅረብ እና ከኢኮኖሚውም ተጠቃሚ መሆን ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- ቀጠናዊ የኢኮኖሚ አካሄዱን ስንቃኝ በተለይ ከኤርትራ ጋር የተፈጠረውን ሰላም አስታኮ የተጀመረ የኢኮኖሚ ግንኙነት ምን ያህል አዋጭ ነው ይላሉ?
ፕሮፌሰር ፍሰሀጽዮን፡- በመጀመሪያ ደረጃ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ትልቅ ቤተሰብ ናቸው። በቋንቋም ይሁን በባህልና በታሪክ የተዛመዱ ናቸው። እኔ የሀገራቱን መለያየት አልወደውም። አንድ ጠንካራ ሀገር ሆነው ቢቀጥሉ ነው የተሻለ ተወዳዳሪ የሚሆኑት ብዬ አምናለሁ። በመሆኑም ፍትሃዊ በሆነ ስነስርዓት መሰረት አስተዳደር ለይቶ በጋራ የሚንቀሳቀሱበትን መንገድ መፈለጉ ይሻላል። ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስሩ ተጠናክሮ በጋራ የሚሰሩበት መንገድ ያስፈልጋል።
በግልህ ግን ካልከኝ እኔ የምፈልገው ሀገራቱ በሁለት ባንዲራ ሳይሆን በአንድ ባንዲራ ስር እንዲሆኑ ነው። ምክንያቱም አንድ ኢንቨስተር እንኳን ቢመጣ ጥቂት ሚሊዮን ህዝብ ካለው ሀገር ይልቅ ከ100 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ያላት ኢትዮጵያ ላይ ነው ኢንቨስት በማድረግ ሰፊ ገበያ ማግኘት የሚፈልገው። በርካታ ፋብሪካ ከአውሮፓ ተነስተው ወደቻይና የሄዱት በርካታ ህዝብ ወይም የገበያ አማራጭን ፍለጋ ነው። በመሆኑም ሁለቱ ሀገራት በአንድ በመስራት ኢኮኖሚያዊ ጥንካሬያቸውን ቢያጠናክሩ የተሻለ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት ያለውን የመንግስት የፖለቲካ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አካሄድ እንዴት ይለኩታል?
ፕሮፌሰር ፍሰሀጽዮን፡- የአገርን አንድነት ያስቀደመ ስራ ወሳኝነት አለው የሚለውን መድገም እፈጋለሁ። አሁን ግን አብዛኛው ጉዳይ ላይ ሲታይ ፈር የለቀቀ ሁኔታ አለ። ሁለት መንግስት ያለ የሚያስመስሉ አካሄዶች አሉ፡፡ ይህንን ማስተካከል ይገባል፡፡መንግስት ጠንካራ መሆን ይገባዋል፡፡ እንደእኔ እንደአጠቃላይ ግን ችግሮቹን ለመከላከል የሽግግር መንግስት ያስፈልጋል የሚል እምነት ነው ያለኝ።
አዲስ ዘመን፡- የሽግግር መንግስት ለምን ያስፈልጋል? ዶክተር አብይ ስልጣን ላይ ሆነው እኮ ስለቀጣዩ ምርጫ እያሰቡ ነው?
ፕሮፌሰር ፍሰሀጽዮን፡- ዶክተር አብይ አህመድ እኔ አሸጋግራችኋለው ብለው ነበር፤ ግን ቸግሯቸዋል። እርሳቸው ንግግራቸው ማር ነው ብዙ ሰው ደግሞ የሚለው ተግባሩ የታለ ነው። እኔም እኮ ደግፌያቸው ነበር። ለነገሩ እኮ ዶክተር አብይ በግልጽነታቸው ምክንያት ነው ችግር ውስጥ የገቡት። መተባበርን መርጠው ለመላው ህዝብ አላማ የተነሱ ሰው ናቸው። በእርግጥ አሁን እንደልባችን ለመናገር ችለናል። ህዝቡ ግን ስለዴሞክራሲ አላወቀም ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- በአንድ በኩል የሽግግር መንግስት ያስፈልጋል ብለው ሲተቹ ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በዶክተር አብይ አህመድ ጊዜ በተቋቋመው የድንበር ማንነት እና የእራስ አስተዳደር ኮሚሽን ውስጥ ደግሞ ተካተው እየሰሩ ነው ይህ አይጋጭም?
ፕሮፌሰር ፍሰሀጽዮን፡- ስለኮሚሽኑ ጠቅላላ ሁኔታ ኮሚሽነሩ ቢያወሩ ይሻላል። በግሌ ግን እንደአባል የተካተትኩት ለ50 ዓመታት ለኢትዮጵያ አንድነት የታገልኩ በመሆኑ እና አሁንም ባለኝ አቅምና ችሎታ ለማበርከት ወደኋላ የማልል በመሆኔ ነው። በርካቶች ፎቅ ሲሰሩ እኮ እኔ ጭንቅላቴን ማበልጸጉ ላይ ነው ያተኮርኩት።
እኔ ሻዕቢያንም ሆነ ኢህአዴግን ብቃወምም ሀገሬን በማውቀው ለመርዳት ግን አንድም ቀን ወደኋላ አልልም። ዶክተር አብይን ስለወደድኩ ብቻ አልነቅፍም ማለት ግን አይደለም። እኔ በኮሚሽኑ ብሰራም የምሰጠው አስተያየት ግን ሀገሪቷ ወደመፍትሄ እንድትሄድ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ከዚህም አልፎ ልማትና አንድነት ላይ መስራት ያስፈልጋል። ይህ እንዴት ይረጋገጥ ከተባለ ደግሞ እያንዳንዱ ዜጋ በቆራጥነት ለሀገሩ ሰላምና ብልጽግና መስራት አለበት፡፡
አሁን ላይ እኮ የውሃ ጉድጓደ ቆፍረው ህዝባቸውን ያላጠጡ ሰዎች ናቸው አክቲቪስት እየተባሉ ችግር የሚፈጥሩት። ዶክተር አብይ እኮ ሌትና ቀን እንደሚሰሩ ይታወቃል። ዋናው ግን ተግባር ነው የሚባለው ደግሞ በፖለቲካው መስክ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚውም ዘርፍ ነው። ለአብነት የአዲስ አበባ ማስዋብ ጥሩ ስራ ቢሆንም ህዝቡ ዳቦ ጠግቦ እንዲያድር ማድረግ ግን የበለጠው ችግር ነው። የእርሳቸውን ራዕይም ታች ቀበሌ ድረስ ብናይ አልወረደም። እናም ሰፊ ስራ በፖለቲካውም ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚውም ማካሄድ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- መልካም በአሁኑ ሰዓት ከኮሚሽኑ ስራ በተጨማሪ በግል ምን አይነት ዘርፍ ላይ ተሰማርተው እየሰሩ ይገኛል?
ፕሮፌሰር ፍሰሀጽዮን፡- እኔ በግሌ የእራሴ የምለው አንድ መኖሪያ ቤት እንኳን ሳይኖረኝ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ሳስተምር የቆየው ሀገር ወዳድ ነኝ። በዚህ ምክንያት ያፈራሁት ቁሳዊ ሃብት የለኝም። አሁን ግን ለ50 ዓመታት ያከማቸሁትን ዕውቀት በመጠቀም መንግስትን እና የግሉን ዘርፍ ለማማከር እና ለመርዳት አንድ ቢሮ እያደራጀሁ ነው።
በአሀኑ ወቅት 10 ከሚሆኑ ሀገር በቀል ምሁራን ጋር በመሆን በኢኮኖሚው መስክ በታክስ፣ ኢንቨስትመንት እና ህግ ጉዳዮች ላይ ለመስራት አፍሮ ግሎባል ኮንሰልታንሲ የተባለ ድርጅት በማቋቋም ላይ እገኛለሁ። በድርጅቱ አማካኝነትም የማማከር ስራ እየሰራሁ ቀሪውን ዕድሜዬን ሀገሬን በሚጠቅሙ ስራዎች ላይ ለማሳለፍ ወስኛለሁ።
አዲስ ዘመን፡- መልካም ለነበረን ቆይታ ከልብ አመሰግናለሁ።
ፕሮፌሰር ፍሰሀጽዮን፡- እኔም ከልብ ነው የማመሰግነው።
አዲስ ዘመን ኅዳር 13/2012
ጌትነት ተስፋማርም