አዲስ አበባ:- ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብና ተባይ የደረሱ ምርቶች ላይ ውድመት እንዳይከሰት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ምርት ለመሰብሰብ እንዲተባበር የግብርና ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ።
በሚኒስቴሩ የግብርና ኤክስቴንሽን ዳይሬክተር ጄነራል አቶ ገርማሜ ገርማ ትናንት በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ በተያዘው የምርት ዘመን 13 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር በማልማት 382 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ታቅዶ 12 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሄክታሩን በሰብል ለመሸፈን ተችሏል። እስከ ቅርብ ጊዜ የነበረው የዝናብ ስርጭትም በቂ በመሆኑ ሰብሉ በጥሩ ቁመና ላይ ይገኛል። ከደረሰው ሰብል ውስጥም አርባ በመቶ የሚሆነውን ለመሰብሰብ ተችሏል።
ነገር ግን ከሜትሪዎሎጂ በተገኘው መረጃ መሰረት ሰሞኑን ያልተሰበሰበውን የደረሰ ሰብል ሊያበላሽ የሚችል ዝናብ እንደሚጥል በመተንበዩ፤ በወቅቱ መሰብሰብ ካልተቻለ ትልቅ የሰብል ውድመት ሊያጋጥም ስለሚችል ከወዲሁ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት አመልክተዋል። በመሆኑም ምርቱን ለመሰብሰብ የሚያስችል በቂ ኮምባይነር ባለመኖሩና አርሶ አደሩ በግሉ ሊሰራው የማይችል በመሆኑ ተማሪዎች፤ የመከላለከያ ሠራዊት አባላትና የመንግስት ሰራተኞች እንዲሁም መላው የማህበረሰብ ክፍል ርብርብ ሊያደርግ ይገባል። በተለይም ከፍተኛ ምርት በሚመረትባቸው ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብና ትግራይ ክልሎች ከፌዴራል እስከ ቀበሌ የተቋቋመ ግብረ ሀይል በመኖሩ ህብረተሰቡ ከእነሱ ጋር በትብበር ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
በሌላ በኩል በተለያዩ ቦታዎች ያልደረሰ ምርት ለመሰብሰብ የሚደረግ ሙከራና መገኛቸው ያልታወቀ ጸረ ተባይ መድሃኒቶች የመጠቀም እንቅስቃሴ እየታየ ነው ያሉት አቶ ገርማሜ፤ ይህንን ማድረግ የበለጠ የምርት ብክነትና ኪሳራ የሚያስከትል በመሆኑ ህብረተሰቡ ይህንን ከማድረግ እንዲቆጠብና በባለሙያዎች ብቻ በመመራት ምርቱን መሰብሰብ እንዳለበት አሳስበዋል።
በተመሳሳይ በሚኒስቴሩ የእጽዋት ጤናና ጥራት ቁጥጥር ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ወልደሃዋርያት ተስፋአብ በበኩላቸው፤ ከየመንንና ከሶማሌ ላንድ የሚመጣው የአንበጣ መንጋ ጉዳት እንዳያደርስ በአምስት ክልሎችና በአንድ ከተማ መስተዳድር በስልሳ ሁለት ወረዳዎች የመከላከል ስራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል። ነገር ግን አሁንም የሚመጣው የአንበጣ መንጋ ካለመቋረጡ ባሻገር በተወሰኑ ቦታዎች የሚቀጥል መሆኑ ታውቋል።
በአንዳንድ አካባቢዎች ምርት አውዳሚ የሆነ የግሪሳ ወፍ ክስተት እንደሚኖር ይጠበቃል፤ በመሆኑ የጉዳቱን መጠን ለመቀነስ የደረሰውን ሰብል በወቅቱ መሰብሰብ እንደሚገባ አመልክተዋል። በዘመናዊም ሆነ በባህላዊ መንገድ በመጠቀም ህብረተሰቡ የደረሰውን ምርት በርብርብ ለመሰብሰብ መሳተፍ እንዳለበት አስገንዝበዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 12/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ