ሀዋሳ፡- የሲዳማ በክልልነት የመደራጀት ህዝበ ውሳኔ ሁሉም ሃሳቦች በነጻነት የተስተናገዱበት መሆኑን የሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ተናገሩ።
የሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደስታ ሌደሞ፤ የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ህዝበ ውሳኔ ሂደትን አስመልክተው ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ እንደተናገሩት፤ የክልልነት ጥያቄ ህዝበ ውሳኔው ከቅስቀሳው ጀምሮ እስከ ድምጽ አሰጣጥ የነበረው ሂደት ሁሉንም በነፃነት ያስተናገደ ነበር።
ከቅስቀሳ ወቅት ጀምሮ በአንድ ወገን ሻፌታን ይምረጡ፤ በሌላ ወገን ደግሞ ጎጆ ቤት ይምረጡ የሚሉ ቅስቀሳዎች እንደነበሩ የተናገሩት አቶ ደስታ፤ በድምጽ አሰጣጥ የተለያዩ ድምጾችን የሚሰጡ መራጮች ያለ አንዳች ችግር በመከባበር ድምጻቸውን መስጠታቸውን ተናግረዋል።
እንደ አቶ ደስታ ገለጻ፤ በምዝገባ ወቅትም ሆነ በድምጽ አሰጣጥ ወቅት የነበረው የህዝብ ብዛት ሁኔታ ህዝበ ውሳኔው በጉጉት ሲጠብቅ እንደነበር ማሳያ ነው። በምዝገባ ወቅት በ10 ቀን ይመዘገባል የተባለው ህዝብ በአምስት ቀን መመዝገቡ ለዚህ ጥሩ አመላካች ነው። ድምጽ በሚሰጥበት ዕለትም ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ጀምሮ ወረፋ የሚጠባበቁ ሰዎች በምርጫ ጣቢያዎች አካባቢ መታየታቸው ሌላኛው ማሳያ ነው። የድምጽ አሰጣጥም ሆነ የቆጠራ ሂደቱ ሰላማዊ፣ ግልጽና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ መጠናቀቁ ትልቅ ስኬት ነው።
እንደ ዋና አስተዳዳሪው ማብራሪያ፤ የሲዳማ አካባቢ ከዚህ ቀደምም በርካታ ብሄሮች ተቻችለውና ተከባብረው የሚኖሩበት ነው። አሁንም እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉንም ብሄሮና ብሄረሰቦችን አቃፊ ሆኖ ይቀጥላል።
ዋና አስተዳዳሪው፤ አጠቃላይ የምርጫ ሂደቱ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና፣ ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ መላው ህዝብና የጸጥታ መዋቅሩ ላበረከተው የላቀ አስተዋጽኦ አመስግነዋል። በድህረ ምርጫ ወቅትም የሚከሰት ችግር እንዳይኖር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት እንደሚሰራ አብራርተዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 12/2012
መላኩ ኤሮሴ