ወሊሶ፡- በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን የደረሱ የሰብል አይነቶች በዝናብ እንዳይበላሹ አርሶ አደሩና ተማሪዎች በጋራ አዝመራ የመሰብሰብ ሥራ ላይ መሰማራታቸው ተገለጸ።
በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ምክትል ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ለሜሳ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ግብርናው ውጤታማ እንዲሆን በዝግጅት፣ በክንውንና ማጠቃለያ ምዕራፎች ተከፍሎ ወደ ሥራ የተገባ ሲሆን፤ እየተሰጠ ያለውን የሜትሮሎጂ ትንበያን መነሻ በማድረግም ሰብሎችን ለመሰበሰብ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው። ከወረዳ እስከ ቀበሌ የዘለቀ ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ሰብሎች የመሰብሰብ ሥራ እየተሰራ ይገኛል።
ከማሳ የእርሻ ዝግጅት ጀምሮ በርካታ የክትትል ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ያስታወቁት ምክትል ኃላፊው፤ በአሁኑ ወቅት እንደ ጤፍ፣ ስንዴና በቆሎ ባሉ ምርቶች ጥሩ ውጤት ማሳየት መቻሉን ጠቁመዋል። በደቡብ ምዕራብ ሸዋ በሚገኙ 11 ወረዳዎች በ152 ቀበሌዎች ህብረተሰቡ በጋራ ሰብሎችን እየሰበሰበ መሆኑንና በተለይ የስንዴ ምርት በአብዛኛው መሰብሰቡን ገልጸዋል።
በሰብል አሰባሰብ ሂደቱም ከአርሶ አደሮቹ በተጨማሪ ትምህርት ቤቶች ለአንድ ሳምንት ዝግ በመሆን ተማሪዎች በሥራው ላይ እንዲሳተፉ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል። የዘንድሮው ምርት አስቀድሞ ከፍተኛ የዝናብ መጠን አግኝቶ እንደነበር፤ ይህም በተለይ በጤፍ ምርት ላይ መጠነኛ ተጽእኖ ማስከተሉንና ይገኛል ተብሎ ከታሰበው ምርት አንጻር የ2 በመቶ ቅናሽ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
ግብርናውን ለማዘመን የሚያስችሉ ግብአቶችን በመጠቀም አርሶ አደሩ ከተለምዷዊ የአስተራረስ ስልት እንዲወጣና ቴክኖሎጂው የሚፈልገውን ዘመ ናዊ መንገድ እንዲከተል አስቀድሞ መሰራቱንም ተናግረዋል። በዞኑ ሽንብራና ጓያን ጨምሮ 329 ሺህ ሄክታር መሬት በሰብል ተሸፍኗል።
አዲስ ዘመን ህዳር 12/2012
አዲሱ ገረመው