አዲስ አበባ፡- ወጣቶች ከመበታተንና ከጥላቻ ይልቅ አንድ መሆንና ፍቅርን እንዲያስቀድሙ የአማራና ኦሮሚያ የሃይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎችና የአገር ሽማግሌዎች ጥሪ አቀረቡ።
የኢትዮጵያን ህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችል የሃይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎች ፣የአገር ሽማግሌዎችና ታዋቂ ግለሰቦች የተዘጋጀ የአማራና የኦሮሚያ የሰላም ምክክር ጉባኤ ትናንት በአዲስ አበባ ተካሂዷል። በጉባኤው ወቅታዊ የአገሪቱ የሰላም ሁኔታ የተዳሰሰ ሲሆን፤ የህግ የበላይትን ማስከበር እና ግጭቶችን ማስቆምን በሚመለከት ውይይት ተካሂዷል። ልዩነቶችን በማጥበብ የህዝብ ለህዝብ ትስስር በማጠናከር ሰላም የሰፈነባት ኢትዮጵያን እውን ማድረግ እንደሚያስፈልግ በውይይቱ ላይ የተጠቆመ ሲሆን፤ ወጣቶችን ከማረምና ከማስተማር አንፃር ሊሰሩ ስለሚገባቸው ስራዎች እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይም ሰፊ ውይይት ተደርጓል።
በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተስተዋለው ግጭት እየተባባሰ ሄዶ ተቋማቱን ለመዝጋት እስከማሰብ የተደረሰው ወላጆችና የሚመለከታቸው አካላት ስራቸውን ባለመስራታቸው መሆኑ ተጠቁሞ፤ መንግስት ዝምታን መምረጡም መንስኤ መሆኑን በጉባኤው የተሳተፉት ቄስ አድማሱ ቢተው ተናግረዋል።
ቄስ አድማሱ በንግግራቸው የአማራና ኦሮሞ ህዝብ መቼም ተጣልቶ እንደማያውቅ ያስረዱ ሲሆን፤ ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል የተጠነሰሰ ሴራ መሆኑንም ጠቁመዋል። ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ወላጆች ልጆቻቸውን መምከር፣ መንግስት የህግ የበላይነትን ማስከበር፣ የፀጥታ አካላትና መገናኛ ብዙሃንም የተሰጣቸውን የህዝብ አደራ በአግባቡ ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
ወጣቶች ችግሮችን በመነጋገር የመፍታት እና ከመበታተንና ጥላቻ ይልቅ አንድ መሆንና ፍቅርን ማስቀደም እንዳለባቸው ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ ዜጎች ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ የማይሰጉባትና የተረጋጋች አገር እንድትሆን ያስችላል ያሉት ደግሞ ሀጂ ቢርካ አወል ናቸው።
‹‹ግልፅነትና መግባባት ችግርን ከስር መሰረቱ ለመፍታት ያስችላል። ለዚህም ወጣቶች በተለይም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ትኩረት ሊሰጡ ይገባል›› ያሉት ሀጂ ቢርካ የሁለቱ ህዝቦች የቆየ ትስስር ይበልጥ እንዲጠናከር ጉባኤው ትልቅ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል።
ወላጆች ልጆቻቸውን፣ ታላላቆች ታናናሾቻቸውን በመቆጣት አሁን በሀገራችን እየተስተዋለ ያለውን የሰላም እጦት ችግር መቅረፍ እንደሚቻል የተናሩገት ጉባኤውን ያዘጋጀው አገር አቀፍ የሰላም ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ብርሀን ተድላ ናቸው። ወጣቶች ከጥላቻና ግጭት የሚገኝ ምንም ትርፍ አለመኖሩን በመረዳት ሰላማቸውን እንዲጠብቁ፣ መንግስትም ህግ የማስከበሩን ስራ በአግባቡ እንዲወጣ አሳስበዋል።
እነዚህ አካላት ከጉባኤው ያገኙትን ሀሳብ ወደ አካባቢያቸው በመውሰድ ከመንግስትና ማህበረሰቡ ጋር በመተባበር ፀጥታን ወደነበረበት በመመለስ የተጋጩትን ማስታረቅ፣ መቆጣት፣ መገሰፅ እና ትምህርት የተቋረጠባቸውን ተቋማት የማስከፈት ስራ እንደሚሰሩ አቶ ብርሀን ገልፀዋል።
ዐቢይ ኮሚቴው በሁሉም ክልሎች በመዘዋወር የሰላም ጥሪ ለማስተላፍ ያቀደ ሲሆን፤ እርቅ እና ሰላም የማስፈን ሥራ እንደሚሰራ ተናግረዋል። በቅርብ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና ዲፕሎማቶች በሚገኙበት አገራዊ የሰላም ኮንፈረንስ ለማዘጋጀት ውጥን መያዙን ሰምተናል። ጉባኤው ባለስድስት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 12/2012
ድልነሳ ምንውየለት
ፎቶ፡- ፀሀይ ንጉሴ