በአንዳንድ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን ማዕከል በማድረግ በሚስተዋለው ሁከትና ብጥብጥ ህይወት እስከ መጥፋት ደርሷል። የትምህርት ተቋማቱ ከፖለቲካ ነፃ ሆነው የእውቀት ሽግግር እንዲያከናውኑ የሚጠበቅ ቢሆንም ከሚፈለገው ዓላማቸው እንዲያፈነግጡና የፖለቲካ ጥቅም ማራመጃ ማድረጉ ትርፉ ምን ይሆን? የችግሩንስ ደረጃ ምን ያህል ተረዳነው? የመፍትሄ አማራጮች ምን መሆን አለባቸው በሚለው ዙሪያ ምሁራን ይናገራሉ።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ለፖለቲካ አጀንዳቸው ማስፈጸሚያ ለማዋልና ተቋማቱን የችግሮች መነሻና ማባባሽያ ለማድረግ የሚንቀሳቀሱ አካላት እንዳሉ መንግሥት ቀድሞ የተገነዘበው ጉዳይ እንደሆነ ይገልፃሉ። መንግስት ችግሩ መቼና የት ቦታ እንደሚፈጸም አያውቅም ነበር ይላሉ። በትምህርት ተቋማት ውስጥ ያሉ ተማሪዎችን ማዕከል አድርገው የሚንቀሳሱ አካላት በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ወጣቶችን በአንድ ማዕከል ማግኘት በመቻላቸው፣ ከሌላው ሰው በተሻለ ማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ማህበረሰብ መኖሩ ለዓላማቸው መሳካት ምቹ ሁኔታ ስላለው የተዛቡና ሀሰተኛ መረጃዎችን በተማሪዎቹ አማካኝነት ህዝብንም ሀገርንም ያውካል የሚል መነሻ እንዳለው አስታውቀዋል።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ማብራሪያ፣ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ቁጥሩ 500 ሺ የሚልቅ ተማሪ ይገኛል። በአንዳንድ ተቋማት እስከ 20 ሺ የሚደርስ ተማሪና ከአምስት በላይ የትምህርት ክፍሎች ያሏቸው ናቸው። ይህን ሰፊ ማህበረሰብና ተቋማቱን ለአጀንዳቸው ማስፈፀሚያ ይጠቀሙባቸዋል ብለዋል። ይሁን እንጂ እነዚህን ተቋማት ለትርምስ በመምረጥ የሚንቀሳቀሱ አካላት ከተማሪው ቁጥር በላይ አይደሉም ባይ ናቸው፤ ዶክተር ሳሙኤል። የተፈጠረው ችግር የሁኔታውን ግነትና ሀቁን ባለመለየት መጠቀሚያ መሆኑ ነው የከፋው ችግር ብለዋል።
ዓላማቸውን ለመፈጸም የሚንቀሳቀሱ አካላት የተማሪዎች ጥያቄ አስመስለው ጉዳዮችን አጀንዳ ማድረግ አንዱ ተግባራቸው ነው። እነዚህ ሰዎች ተጠርጥረው ሲያዙም ‹‹ድምጻችን ታፈነ›› በሚል ተጨማሪ ሁከት ለማስነሳትም ጭምር የተዘጋጁ እንደሆኑ ጠቁመዋል። በዚህ ልክ ትርምስ የሚፈጥሩትን አካላት በቁጥጥር ሥር ለማዋል ጥንቃቄ ሲደረግ ደግሞ አጋጣሚውን ወደ ሌላ አጀንዳ ለመጠቀም የሚሰራ ስራ ፈተና እንደሆነ ሚኒስትር ዴኤታው ያስገነዝባሉ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃናም በበኩላቸው አክቲቪስቶችና የፖለቲካ ድርጅቶች በስሜት የሚነዳላቸውን ማዕከል እንደሚያደርጉና ለዚህ ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተጋላጭ እንደሆኑ ይናገራሉ። ቀደም ባሉት ዓመታትም በትምህርት ተቋማት ውስጥ እንቅስቃሴ ቢኖርም ጉዳቱ የከፋ አለመሆኑን በማነፃፀር የሚገልጹት ፕሬዚዳንቱ አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች ተማሪዎቹ የማህበራዊ ሚዲያ ተደራሽ መሆን ለዓላማቸው ማሳኪያ ጠቅሟቸዋል ብለዋል። በትምህርት ተቋማት አካባቢ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችም በመካከላቸው ያለውን አጥፊ አጋልጠው አለመስጠታቸው፣ አለመቃወማቸውና ድጋፍ ማድረጋቸው እኩይ ተግባር የሚፈጽሙትን አግዟቸዋል። መንግሥትም በሚጠበቅበት ደረጃ ልክ ኃላፊነቱን አለመወጣቱ ለችግሩ መባባስ ቁልፍ ምክንያቶች ናቸው ሲሉ ይወቅሳሉ።
በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ ተባባሪ ፕሮፌሰር ውሂብእግዜር ፈረደ፣ የትምህርት ተቋማት የፖለቲካ አጀንዳቸውን ለሚያራምዱ ምቹ መሆናቸው ችግሩን እንደሚያባብሰው ይገልጻሉ። በየተቋማቱ ያሉ የትምህርት አመራሮች የፖለቲካ ጥቅም ተጋሪ ወይንም ሹመኞች መሆናቸው፣ ተማሪዎቹም የትምህርት የሥነ ልቦና ዝግጅት ሳይሆን ሌላ ተልዕኮ ይዘው መግባታቸው፣ የትምህርት ተቋማትን ማዕከል ያደረገ ደህንነት የሚያስጠብቅ ሥርዓት አለመዘርጋቱ፣ ከፖለቲካው ጫና ጋር ትኩስ ኃይልነቱ ተደምሮ አሁን በተቋማቱ እየተፈጠረ ላለው ችግር በመንስኤነት ያነሳሉ።
የተለያዩ የፖለቲካ ተዋናዮች የትምህርት ተቋማትን እንደ አንድ የፖለቲካ ማራመጃ ወይም መጠቀሚያ አድርገው መንቀሳቀስ ከጀመሩ ውለው አድረዋል የሚሉት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ በዓለም አቀፍ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ታሪክ ተማሪዎች የአንድ ፓርቲ ወይም ብሄርን አጀንዳና ተልዕኮ ማራመድ ሳይሆን፣ የጋራ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ ድምጽ ይኖራቸዋል ተብሎ ይታመናል፤ ተገቢም ነው። ከዚህ እሳቤ ባፈነገጠ በኢትዮጵያ ታሪክም አሁን የሚታየው አይነት ተከስቶ አያውቅም ሲሉ ይወቅሳሉ። አሁን በሀገሪቷ ባሉ የትምህርት ተቋማት የሚንፀባረቁት ተግባራት ግን ተማሪውም መምህሩም ነፃ እውቀት የመስጠት ሳይሆን የየራሱን አመለካከት በሌላው ላይ ለመጫን የሚደረገው ሩጫ ይበዛል ሲሉ ሁኔታውን ይገልፃሉ።
ዶክተር ሳሙኤል እንዳሉት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማርና የመመራመር ተልዕኮ እንጂ የጦር ካምፕ ሊሆኑ አይችሉም። በመሆኑም ጦር ቆሞላቸው የሚማሩ ተማሪዎችን ማፍራት ሳይሆን ችግሮችን በውይይት በመፍታት የተማረ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ማፍራት ነው የሚፈለገው፤ የሚገባውም ብለዋል። ለዚህ ደግሞ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የድርሻውን መወጣት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል።
‹‹የትምህርት ገበታን ትቶ መውጣት ዕውቀት ቆመ ማለት ነው›› የሚሉት ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው፣ ከሌላው የተሻለ ንቃተ ሕሊና አለው በሚባል የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ችግሮችን በውይይት መፍታት እንጂ ተሸንፎና የትምህርት ገበታውን ለቆ መሄድ የሚጠበቅ ተግባር አይደለም፤ የመፍትሄውም አካል ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም ሲሉ አፅንኦት ይሰጣሉ።
ምሁራኑ እንዳሉት ትምህርት ተቋማቱ የሥጋት ቀጣና እንዲሆኑ የሚንቀሳቀሱ አካላት ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ ባለመሆናቸው የተከሰተው ችግር ዘለቄታ የለውም። ተማሪዎቹን ከማረጋጋት ጎን ለጎን አጥፊዎችን ለህግ የማቅረቡ ተግባር በተማሪዎች፣ በአቅራቢያው ባሉ የማህበረሰብ ክፍሎች እና ከከተማው አስተዳደሮች ጋር በሚፈጠር ቅንጅታዊ ስራ ከተጠናከረ የመማር ማስተማሩን ሂደት ወደ ነበረበት ለመመለስ ጊዜ የሚፈጅ አይሆንም።
አዲስ ዘመን ህዳር 11/2012
ለምለም መንግሥቱ