“ይህቺን ቀን ለማየት ጓደኞቼንና የቅርብ ዘመዶቼን ገብሬበታለሁ። በተለይም በ1994 ዓ.ም የነበረው እጅግ አሳዛኝ ነበር። ሃሳባቸውን ለመግለጽ የወጡ ተማሪዎች ላይ ጭካኔ የተሞላበት ዕርምጃ ተወሰደ። በዚህ ዕለት የቅርብ ጓደኛዬንና ዘመዴን አጥቻለሁ። ጓደኛዬ ከእኔ ጋር እያለ ነበር በጥይት ተመትቶ የተገደለው። እነሱ በከፈሉት መስዋዕትነት ዛሬ እኔ በነፃነት ድምፄን ስሰጥ የሚከብድ ስሜት እየተሰማኝ ነው።” የሚሉት በሸባዲኖ አቤላ ወረዳ ሊዳ ቀበሌ የምርጫ ጣቢያ ለሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ህዝበ ውሳኔ ድምፅ ሲሰጡ ያገኘናቸው ወይዘሮ አስቴር ሀለሶ ናቸው።
ለዚህ ዕለት በመብቃታቸው ፈጣሪያቸውን ሲያመሰግኑ ወይዘሮ አስቴር የሎቄን ሰቆቃ በመዘከር ነው። ‹‹ዛሬ ድምፅ በሰላም ሲሰጥ የተለየ ስሜት ሰውነቴን ተሰማኝ። በሰላማዊ መንገድ እድልሽን ምረጪ ብሎ መንግሽት ዕድሉን በማመቻቸቱ ደስተኛ ነኝ። የህይወት ዘመኔ ስኬት ነው ብል ማጋነን አይሆንብኝም›› ይላሉ።
በሚሊየን የሚቆጠረው የሲዳማ ህዝብ ልክ እንደ ወይዘሮ አስቴር ሁሉ የሲዳማን በክልልነት የመደራጀት ህዝበ ውሳኔ የህይወት ዘመን ስኬት አድርጎ ይመለከተዋል። ይህንንም የሲዳማ ህዝብ ትናንት አሳይቷል። ወጣት ሽማግሌ፣ የተማረ ያልተማረ ሳይለይ ሁሉም በሃዋሳ ከተማና በአጠቃላይ በዞኑ በሚገኙ በአብዛኞቹ የምርጫ ጣቢያዎች ረጃጅም ሰልፎች ታይተዋል። ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ ድምፅ መስጠት የተጀመረ ሲሆን ህዝቡ ድምፅ ለመስጠት የነበረውን ጉጉት ለመግለጽ የሚከብድ ነው። የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ እጅግ ሰላማዊ ነበር።
ወይዘሪት ዳርምየለሽ ዳዊትም በሊዳ የምርጫ ጣቢያ ድምፅ ስትሰጥ ነው ያገኘናት። ‹‹ሲዳማ በድምፁ ዕድሉን በሚወስንበት ዘመን ላይ በመገኘቴ ዕድለኛ ነኝ። የህዝበ ውሳኔው ውጤት ምንም ይሁን ምን ለመቀበልም ዝግጁ ነኝ›› ስትል ትናገራለች።
በህዝበ ውሳኔው ሲዳማ ክልል የመሆን ጥያቄው ምላሽ አግኝቶ ክልል የሚሆን ከሆነ እንደ ከዚህ ቀደም ሁሉንም የሚያቅፍ፣ ሁሉም የሚበለጽግባትና ሰላማዊት ሲዳማን እውን ሆና ማየት እንደምትሻ ተናግራለች።
በሊዳ ቁጥር የምርጫ ጣቢያ የሻፌታ ብሄር ተወካይ አቶ ከበደ ለገሰ የድምፅ አሰጣጡ እጅግ ሰላማዊና ፍትሐዊ መሆኑን ተናግረዋል። ያለ አንዳች ጫና መራጮች ድምፅ እየሰጡ ነው ብለዋል። የድምፅ አሰጣጥ ሂደትም እጅግ ሰላማዊ መሆኑን ይናገራሉ። መንግሥት ህዝበ ውሳኔውን በማስተባበር ላደረገው አስተዋጽኦም አመስግነዋል።
ከአዳማ ከተማ በመምጣት ሸበዲኖ አቤላ ወረዳ ሊዳ ቀበሌ ቁጥር 1 ምርጫ የሚያስፈፅሙት አቶ አየለ ገብሩ በበኩላቸው የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ አጠቃላይ ሂደቱ እጅግ ሰላማዊና አስደሳች እንደነበር ያነሳሉ። በጣቢያው 1 ሺህ 801 መራጮች መመዝገባቸውን አቶ አየለ ተናግረዋል። የምርጫ ጣቢያዎቹ 12 ሰዓት ላይ የተከፈቱ ሲሆን መራጮቹ ግን ከሌሊቱ 7፡00 ጀምሮ በጣቢያው ፊት ለፊት ተሰልፈው እንደነበር ይናገራሉ። የህዝቡ ብዛትና ጉጉት እጅግ የሚያስደንቅ ነው ብለዋል።
የመራጮቹ ስነ ምግባር እጅግ የሚያስደስት ነው የሚሉት አስፈጻሚው፤ በምናስተባብርበት ወቅት የምንሰጣቸውን ትዕዛዝ ተቀብለው በመፈፀም የድምፅ አሰጣጡ ስኬታማ እንዲሆን እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ የሚያስመሰግናቸው ነው።
በሃዋሳ ከተማ መናኸሪያ ሰፈር በባህልና ቱሪዝም የምርጫ ጣቢያ ውስጥ ድምፅ ሲሰጡ ያገኘናቸው አቶ አብዱ ጉደታ በበኩላቸው፤ ምርጫው እጅግ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ እንደሆነ ተናግረዋል። በነፃነት ድምፃቸውን መስጠታቸውንም ተናግረዋል።
መናኸሪያ ክፍለ ከተማ 04 ነዋሪ አቶ አደፍርስ ማሞ በጤና እክል ምክንያት በልጆቻቸው ደጋፊነት ነው ድምፅ ለመስጠት የመጡት። በነገ ዕጣ ፋንታቸው ላይ የግድ ድምፅ መስጠት እንዳለባቸው ስለተሰማቸው በሰው ድጋፍ ድምፅ ለመስጠት ወደ ጣቢያው መምጣታቸውን ተናግረዋል። ወረፋ ሳይጠብቁ ድምፅ እንዲሰጡ ተፈቅዶላቸው በነፃነት ድምፅ መስጠታቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ታዛቢዎች ቡድን እኩለ ቀን ላይ በሰጠው መግለጫ እስከ ግማሽ ቀን የነበረው የድምፅ አሰጣጥ ሂደት ሰላማዊ ነበር። 128 ታዛቢዎችን በምርጫ ጣቢያዎች በማሰማራት ጥምረቱ የድምፅ አሰጣጡን እየታዘበ መሆኑን የተናገሩት የቡድኑ መሪ ወይዘሮ ብሌን አስራት የመራጮች ቁጥር በመብዛቱ በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች አካባቢ መጨናነቆች መስታዋላቸውንና መጨናነቁም የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ በመጠኑም ቢሆን እንዲስተጓጎል ማድረጉን ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 11/2012
መላኩ ኤሮሴ