•406 ሚሊዮን ኩንታል የሰብል ምርት ይጠበቃል
•ምርት በፍጥነት እንዲሰበሰብ ጥሪ ቀርቧል
•በበጋ መስኖ የቆላ ስንዴ ልማት አቅምና ተሞክሮ ተገኝቷል
አዲስ አበባ፡- የ2011/2012 የምርት ዘመን የመኸር ግብርና ሥራ በተሻለ የምርት ግብአት በመታገዝ በተለያዩ ሰብሎች ከተሸፈነው 13 ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት 406 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የደረሱ ሰብሎችን የመሰብሰብ ሂደት ባልተጠበቀ የአየር መዛባትና በሌሎችም ችግሮች እንዳይስተጓጎል አርሶአደሩ ከሚደረግለት የተለያየ ድጋፍ በተጨማሪ የራሱንም አማራጮች በመጠቀም ምርቱን እንዲሰበስብ ሚኒስቴሩ ጥሪ አቅርቧል። በተያያዘም የስንዴ ምርት በማይታወቅባቸው ሦስት የተፋሰስ አካባቢዎች በበጋ መስኖ የቆላ ስንዴ የማምረት ሥራ በመከናወኑ አቅምና ተሞክሮ መገኘቱ ተጠቁሟል።
በሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ተወካይ አቶ ዳንኤል ዴንታሞ፣የምርት ዘመኑን አጠቃላይ እንቅስቃሴ አስመልክተው ሰሞኑን ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ማዳበሪያ በወቅቱ በማቅረብ፣በመስመር መዝራት፣ በገበያ ተኮር ኩታ ገጠም የእርሻ ሥራ ማከናወን፣ በአጠቃላይ በምርት ዘመኑ በቴክኖሎጂና በግብአት አቅርቦት የተሻለ ሥራ ተከናውኗል። በተለይም ስንዴ፣በቆሎ፣ገብስ፣ሰሊጥ በሚመረትባቸው አካባቢዎች ገበያ መር በሆነ ኩታ ገጠም በተከናወነው የእርሻ ሥራ ወደ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በሰብሎቹ ለመሸፈን መቻሉን አመልክተዋል። በመሆኑም በምርት ዘመኑ 406 ሚሊየን ኩንታል ምርት ይጠበቃል ብለዋል።
አጠቃላይ የመኸር ግብርና ሥራው ግምገማ ጥሩ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ዳንኤል መስከረም ላይ ያጋጠመው የአንበጣ መንጋንም በሰብሉ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ከፍተኛ ርብርብ መደረጉንና በተወሰነ ደረጃ ጉዳት ቢኖርም ጉዳቱ በአጠቃላይ ምርት ላይ ተጽዕኖ እንደማይኖረው አመልክተዋል።
ምርት የመሰብሰቡ ሂደትም በአርሶ አደሩ ጉልበት፣ የአካባቢ ባለሀብቶችን በማስተባበር በእህል መሰብሰቢያ መሣሪያ (ኮምባይነር) በመታገዝ በመከናወን ላይ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ዳንኤል ሚኒስቴሩ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት መዋቅሮችን፣ የህብረት ሥራ ኤጀንሲዎች፣ዩኒየኖች፣ማህበራት፣በግብርና ዘርፍ የሚንቀሳቀሱትን ሁሉ በማስተባበር ምርት የማሰባሰቡ ሥራ እንዲቀላጠፍ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል። ኢትዮጵያ 32 የሚደርስ ስነ-ምህዳር እንዳላትና የዘር ወቅቱም እንደ አካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ የተለያየ መሆኑን ጠቁመዋል። የዘር አሰባሰቡም በዚሁ መሰረት እንደሚከናወንናእስከ ጥር ወር ድረስ እንደሚዘልቅ አስታውቀዋል። እስከአሁን በስምጥ ሸለቆ ደቡብና ሰሜን፣በኦሞና አባይ ሸለቆ፣በቆላማው የሀገሪቱ አካባቢዎች የመሰብሰቡ ሂደት በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።
የምርት ዘመኑ የሚያሳየው ግምገማ ጥሩ ቢሆንም ምርቱ ከማሳ ላይ ተሰብስቦ ጎተራ እስካልገባ ድረስ እርግጠኛ መሆን እንደሚያስቸግር ያመለከቱት አቶ ዳንኤል፣የምርት መሰብሰቡ ሂደት ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እና በሌሎችም ችግሮች ሊስተጓጎል ስለሚችል መዘናጋት እንደማያስፈልግ አሳስበዋል።
አርሶአደሩ ከሚደረግለት ድጋፍ በተጨማሪ የቤተሰቡን ጉልበት በማስተባበር ምርት በመሰብሰቡ ረገድ ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል። በምርት መሰብሰብ ወቅትም ብክነትና የጥራት መጓደል እንዳያጋጥም ጥንቃቄ እንዲደረግ አስገንዝበዋል።
በሌላ በኩልም ስንዴ ተመርቶ በማይታወቅባቸው በአዋሽ ተፋሰስ በኦሮሚያና አፋር፣ በሸበሌ ተፋሰስ ደግሞ በሶማሌ ክልል ጎዴ አካባቢ እንዲሁም በኦሞ ተፋሰስ የተለያዩ አካባቢዎች በግልና በአርብቶ አደር ማሳዎች ላይ በቅንጅት የቆላ ስንዴ በበጋ መስኖ ልማት በመከናወን ላይ መሆኑን አመልክተዋል። 600 ሄክታር ማሳ ላይ ለማልማት ከተያዘው ዕቅድ 550 ሄክታር መሬቱ በስንዴ ተሸፍኗል፤ 40 ቀናት የሆነው ስንዴም መድረሰንም ገልጸዋል።
በባለሀብቶችና በአርብቶ አደሮች ቅንጅት በመከናወን ላይ ያለው የቆላ ስንዴ ልማት በተሰጠ ምክረ ሃሳብና ስልጠና እንዲሁም መንግሥት ምርጥ ዘርን በማቅረብና በሌሎችም ድጋፎች መከናወኑንና ውጤት እንደተገኘ አመልክተው፤ ሰሞኑን በተደረገ የመስክ ጉብኝትም ባለሀብቱ አመራጭ የገበያ ዕድል እንደሚፈጥርላቸው፣አርብቶ አደሮቹም ተጠቃሚ መሆናቸው እንዳስደሰታቸው መናገራቸውን አስታውሰዋል። በቆላማ አካባቢ ለሙከራ የተጀመረው ሥራ አቅምና ተሞክሮ መፍጠር ያስቻለ ነው ብለዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 11/2012
ለምለም መንግሥቱ