ለጽሁፉ የተጠቀምነው ፎቶ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ካርጎ የዕቃ ማጓጓዣ አውሮፕላንን ይመስላል። ፎቶውን እንደተመለከትን ከመቅጽበት የምንሰጠው ትርጉም የአየር መንገዱ አውሮፕላን አደጋ እንደደረሰበት ሊሆን ይችላል። እውነታው ግን እርሱ አይደለም። የስመ ጥር አየር መንገዳችንን ስም በማጉደፍ የሆነ ጥቅም ለማግኘት የፈለጉ አካላት በፎቶ ሾፕ አቀናብረው ያሰራጩት ሀሰተኛ ምስል ነው። ይህን ለማሳያነት ተጠቀምን እንጂ አሁን አሁን በሀገራችን የሚከሰቱ ግጭቶችን ለማባበስ በፎቶ ሾፕ እየተቀናበሩ የሚሰራጩ ምስሎች ለቁጥር የሚታክቱ ናቸው። ይህም ብቻ ሳይሆን በሌላ ሀገር የተፈጸሙ መጥፎ ድርጊቶች በሀገራችን እንደተፈጸሙ ተደርገው ይሰራጫሉ። እንዴትስ ይቀናበራል ባለሙያዎች እንደሚከተለው ያብራራሉ።
በኢትዮጵያ የአሶሺየትድ ፕሬስ ተወካይ አቶ ኤሊያስ መሰረት እንደሚያስረዱት ‹‹ፎቶ ሾፕ›› አዶቤ በሚባል ኩባንያ የተመረተ ፎቶን ኤዲት ማድረጊያ ሶፍት ዌር ነው። ይህ ቴክኖሎጂ ለህትመትና ለተለያዩ ሥራዎች አጋዥ ቢሆንም አንዳንድ ሰዎች ሀሰተኛ ምስሎችን ኤዲት እያደረጉ በማሰራጨት ለመጥፎ ተግባር እንደሚጠቀሙበት ይናገራሉ። ለምሳሌ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሌላ ሀገር የተፈጸመን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ኢትዮጵያዊ መልክ በማላበስ በሀገራችን ያለውን አለመረጋጋት የሚያባብሱ ምስሎች እንደሚሰራጩ አስታውሰዋል።
አቶ ኤፍሬም ተክሌ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የኢንፎርሚሽን ቴክኖሎጂ አገልግሎት ክፍል ኃላፊ በበኩላቸው አሁን አሁን በሀገራችን በማህበራዊ ሚዲያ ከሚተላለፉ ምስሎች ውስጥ አንዳንዶቹ በፎቶ ሾፕ እየተቀናበሩ የሚሰራጩ ናቸው። ምስሎችን ለሚፈልጉት ዓላማ አቀናብረው የሚያሠራጩ አካላት የመጀመሪያ ተግባራቸው ለሃሳባቸው ማስፈጸሚያ የሚያመቻቸውን ምስል ከ‹‹ጎግል›› ማውጣት ነው።
በፎቶ ሾፕ ጥበብ የአንድ ሰው እውነተኛው የፊት ገጽታ በሌላ ሰው የፊት ገጽታ መቀየር ይቻላል። የደስታ ድባብ የሚታይበትን ቦታ የኀዘን ድባብ አላብሶ ማቀናበር ይቻላል። የአንድን ሀገር ክስተት የሌላ ሀገር አድርጎ ማሳየትም አያስቸግርም። ጉዳዩን የበለጠ አሳማኝ ለማድረግም መጠነኛ ገላጭ ጽሑፍ ከምስሉ ግርጌ መጻፍ ይበቃል።
በተመሳሳይ ተንቀሳቃሽ ምስሎችንም በተለያየ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ቀደም ሲል በነበራቸው እንቅስቃሴ ላይ በመጨመር ወይም በመቀነስ ለሚፈልጉት ዓላማ ማስፈጸሚያነት ኤዲት የማድረግ ሥራ እንደሚሠራባቸው አቶ ኤፍሬም ያስረዳሉ። አንድን መልዕክት በታወቀ ሚዲያ ወይም ተቋም ዌብ ሳይት የተላለፈ በማስመሰል በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች የተዛባ መረጃ እንደሚተላለፍም ተናግረዋል። ምንም እንኳን የታሰበለት ዓላማ ሌላ ቢሆንም የአንድን ሰው ድምፅ በመጠቀም የሚፈለገውን መልዕክት ማስተላለፍ የሚያስችል ቴክኖሎጂም ጥቅም ላይ እንደሚውል አስረድተዋል።
አቶ ኤሊያስ እየተቀናበሩ የሚሰራጩ ሐሰተኛ መረጃዎችን ቴክኖሎጂን በመጠቀም መለየት ይቻላል ይላሉ። አብዛኛው የማህበረሰብ ክፍል የሐሰተኛ መረጃዎችን ለመለየት የሚያስችል የቴክኒክ ዕውቀት አለው ባይባልም ጥርጣሬ የሚፈጥርን አንድ ምስል መልሶ ጎግል ውስጥ በማስገባት ትክክለኛውን ምስል ማግኘት ይቻላል ይላሉ። ከዚህም በተጨማሪ አጠራጣሪውን ምስል እንደ አንድሮይድ ባሉ ‹‹አፕልኬሽኖች›› በመታገዝ መለየት እንደሚቻል ያስረዳሉ። በዘርፉ ዕውቀት ያላቸው ሰዎች ሀገርን ለማፈራረስ ሆን ተብለው የሚሰራጩ ሐሰተኛ መረጃዎች እውነተኛ ገጽታቸው ምን እንደሚመስል ለህብረተሰቡ በማሳየት ግንዛቤ ማስጨበጥ እንደሚገባቸው ይመክራሉ።
እንደአስተያየት ሰጪዎቹ ህብረ ተሰቡ አንድ መጥፎ መልዕክት የሚያስተላልፍን ምስል ወይም ጹሑፍ ለሌሎች ከማጋራቱ በፊት የመረጃው ምንጩ ማን ሊሆን ይችላል? ብሎ እራሱን መጠየቅ ይኖርበታል። በማህበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉትን ነገሮች በሙሉ እውነት ናቸው ብሎ ከመቀበል በፊት ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ የጉዳዩን እውነተኝነት ማረጋገጥ ያስፈልጋልም ብለዋል። መረጃውን ማነው ያሰራጨው? ለምን ዓላማ የተሰራጨ ነው? ሌሎች ሚዲያዎች ስለዚህ ጉዳይ ምን ብለው ዘግበዋል? የሚሉትን መረዳት ይኖርበታል። እነዚህን ሁኔታዎች ከመጣራታቸው በፊት መረጃውን ለሌላ ሰው ማጋራት ግን ተገቢ አለመሆኑን አስረድተዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 11/2012
ኢያሱ መሰለ