ዛሬ የኢትዮጵያን ድንበር አልፎ በመጣ ወራሪ ጠላት አልተወረርንም:: ይሁን እንጂ በየቀኑ ድንበር አቋርጠው የሚደርሱን ቀላልና ከባድ የነፍስ ወከፍ የጦር መሳሪያዎች ጠላት ልንከላከልበት ከወዳጅ አገራት የሚቸረን ዕርዳታ ይመስላል፡፡ አገራችን በወራሪ ተደፍራ ይህን መሰሉ ድጋፍ ቢደረግልን እጅግ ደስ የምንሰኝበት ሁኔታ ይኖር ነበር:: ዳሩ ግን ለእርስ በእርስ መተላለቂያችን መሆኑ የሚልኩልንን አካላት እንድንታዘባቸው፤ ተቀብለው የሚያደርሱልንንም በጨካኝነትና በከሀዲነት እንድንመለከታቸው ያደረገ ጉዳይ ሆኗል፡፡
በ2012 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) በምክር ቤት ተገኝተው ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ በሰጡበት ወቅት ‹‹ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ከመበራከቱ የተነሳ ኢትዮጵያ ካላት የህዝብ ቁጥር የሚበልጥ የጦር መሳሪያ ያላት ሃገር ሆናለች ፤ አርሶ አደሩ የጦር መሳሪያ ካልያዝኩ ራሴን መከላከል አልችልም ብሎ ስለሚያምን መሬት ሸጦ መሳሪያ ይገዛል፡፡ በተለይ አሁን ላይ የጦር መሳሪያን ሸጦ ገንዘብ ማትረፍን እንደ ሥራ የወሰደው ኃይል አለ፤ ለዚህም ሲባል መሬት ተሸጦና ከባንክ ብድር ተወስዶ የሚሠራ ንግድ ሆኗል›› በማለት ተናግረዋል፡፡
በ2011 ዓ.ም ብቻ በጉሙሩክና መከላከያ የተያዙ መሳሪያዎች ብዛት 2020 ሽጉጦች፣ 62 ክላሽንኮቭ ጠመንጃ፣ አራት መትረየሶች መሆኑናቸውን ከገቢዎችና ጉምሩክ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡ በዚሁ ዓመት 917 የመትረየስ ፣ 2ሺህ 983 የክላሽንኮቭ፣ 15 ሺህ 717 የብሬንና 80 ሺህ 764 የሽጉጥ ጥይቶች መያዛቸው ተጠቅሷል።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን መረጃ እንደሚያመለክተው ደግሞ በ2012 ዓ.ም የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 190 የጦር መሳሪያዎች ፣62 ሺ 183 ጥይቶች ተይዘዋል፡፡ የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ በሩብ ዓመቱ 74 ልዩ ልዩ ጠመንጃዎች፣115 ሽጉጦችና አንድ ቦንብ በድምሩ 190 የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን፤ በቁጥጥር ስር ከዋሉት 62ሺ183 ጥይቶች መካከል አንድ ሺ 570 የብሬንና ስምንት ሺ 484 የኤም 14 ጥይቶች ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ 52 ሺ 129 ደግሞ ልዩ ልዩ ጥይቶች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
እነዚህ የጦር መሳሪያዎች ለሃገር ሰላምና ደህንነት ስጋት ናቸው:: በየአካባቢው በሚፈጠረው የሰላም መደፍረስ፣ ለሰው ሕይወት መጥፋት፣ለዘረፋና ለተለያዩ ወንጀሎች ምክንያት መሆናቸው እሙን ነው:: ስለሆነም መንግሥትና ህዝቡ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎችን በመቆጣጠር ረገድ ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው፡፡
ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ፣ የማዘዋወሪያ ስልቱንም እየቀያየረ ፣ በብዛትም በዓይነትም እየጨመረ በመሆኑ፤ ይህም ለሃገርና ለህዝብ ደህንነት ስጋት ስለሚደቅን መንግሥትና ህዝብ በጋራ በመሆን ቁጥጥሩን ሊያጠናክሩት ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 10/2012