አዲስ አበባ፡- ባለፉት ስድስት ወራት 452 ሚሊዮን 189ሺ264 ብር ግምት ያላቸው የተለያዩ ዕቃዎች በህገ ወጥ መንገድ በኮንትሮባንድ ሲንቀሳቀሱ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽነሩ አቶ ደበሌ ቃበታ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፣ በወጭም ሆነ በገቢ ንግድ ላይ የሚደረገው የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ዋነኛው ምክንያት በህገ ወጥ መንገድ ለመጠቀም ከሚመነጭ ፍላጎት የሚነሳ ሲሆን ለውጡን ለማደናቀፍ ያለመ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በተለይም በህገ ወጥ መንገድ በኮንትሮባንድ የሚደረገው የገንዘብ እና የጦር መሳሪያ ዝውውር አለመረጋጋት ለመፍጠርና በዚህም በአገሪቱ እየተደረገ ያለውን የለውጥ እንቅስቃሴ ለማወክና ወደ ኋላ ለመመለስ አዝማሚያ የሚታይበት መሆኑን ኮሚሽኑ ተናግረዋል፡፡
የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴው በተለይም የገቢ ኮንትሮባንዱ ህጋዊውን የንግድ እንቅስቃሴ ተገን አድርጎ የሚካሄድ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ ህጋዊውን የንግድ እንቅስቃሴ ሽፋን አድርገው ወደ አገር ውስጥ ከሚገቡ ዕቃዎች መካከልም እንደ ቆርቆሮና የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች የመሳሰሉት ይገኙበታል ብለዋል፡፡ ለእርዳታ የተሰጡ የምግብ እህሎችም በዚህ መልክ በኮንትሮባንድ በተለይም ከምስራቅ በድሬዳዋ በኩል ወደ አዲስ አበባና መሃል አገር የሚገቡ መሆናቸውንም ነው የጠቆሙት፡፡
ችግሩን ለመፍታትም የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ሲሆን፣ በተለይም ከመቶ ቀናት ዕቅዱ ጋር ተያይዞ መሰረታዊ ለውጦችን እያደረገ መሆኑንም ኮሚሽኑ ጠቅሰዋል፡፡ በዚህም መላው የተቋሙ አመራርና ሠራተኞች ችግሩንና የችግሩን ምንጭ እንዲያውቁና የመፍትሔው አካል እንዲሆኑ እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
እንደኮሚሽነሩ ገለፃ በሁሉም ኬላዎች አካባቢ ያሉ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ባለ ድርሻ አካላትና ህብረተሰቡም የኮንትሮባንድ መንስኤዎችንና የሚያስከትለውን ችግር ተገንዝቦ በጥንቃቄ ክትትል እንዲያደርግ የሚያስችሉ ሥራዎችም እየተከናወኑ ነው፡፡ በዋነኝነት ግን ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል መሰረታዊ መዋቅራዊ ለውጥ እያከናወነ መሆኑን ነው፡፡ ከዚህ ጋር የተያያዙ የህግ ማዕቀፎችንና አዋጆችን እንዲሁም ደንብና መመሪያዎችን እየከለሰ መሆኑንም ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 22/2011
በይበል ካሳ