ቅዳሜ ታህሳስ ሶስት ቀን 1963 ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ 30ኛ አመት ቁጥር 286 እትም አንድ ትዳር ፈላጊ “የህግ ሚስት እፈልጋለሁ” በሚል ርዕስ ስለራሱ ዝርዝር መረጃዎችን በመስጠት ለጋዜጣው የላከውን ጽሑፍ አስነብቦ ነበር፡፡
የህግ ሚስት እፈልጋለሁ
ስራዬ ሁለገብ ደሞዜ 420 ብር (መነሻ)፡፡ የአዲስ ስራና የገንዘብ ምንጭ ዘዴኛና መቶ በመቶ ጤናማ ነኝ፡፡ የትዳር ጓደኛዬ ለምትሆነው ፍቅር ፣ አክብሮት ፣ እምነት ፣ ጨዋነት ፣ ትህትናና ደስታን አብሮ ለመካፈል መቶ በመቶ ዝግጁ ነኝ፡፡ ብቸኝነት ሰለቸኝ፡፡ ዕድሜዬ 35 ነው፡፡ ሁልጊዜ ብቸኛ ነኝ፡፡ አግብቼ አላውቅም፡፡ ልጅ የለኝም፡፡ተጣጥሮ አዳሪ ነኝ፡፡ የመጠጥ አመል የለኝም፡፡ ሲጋራ አጤሳለሁ፡፡ ለዳንስ ለሲኒማ ለልዩ ልዩ ደስታና ጨዋታ አልሰንፍም፡፡ ስራዬን አከብራለሁ፡፡ ከተቀጠርኩ ሁለት ዓመት ተኩል ቢሆነኝም በህመምም ሆነ በፍቃድ ከስራ ቀርቼ አላውቅም፡፡ ወደስራ ቀድሞ ከመግባት በስተቀር አንዲት ደቂቃ አሳልፌ አላውቅም፡፡ ውጪ ማምሸት አልወድም፡፡
ትምህርቴ ሶስት የውጭ አገር ቋንቋ ነው፡፡ በሁለቱ እሰራበታለሁ፡፡ ቁመቴ አንድ ሜትር ከ 66 ሳ.ሜ ፣ ክብደቴ 65 ኪሎ ፣ ቀለሜ ጠይም ፣ በአካሄዴና በንግግሬ ፈጣንና አልፎ አልፎ ቀልደኛ ነኝ፡፡ ሁልጊዜ ሳቅና ጨዋታ እወዳለሁ፡፡ ኩርፊያ ፣ ኩራትና ትዕቢት አልወድም፡፡
ስለዚህ እውነተኛ ዕድሜዋ ከ24 እስከ 32 ዓመት የሆነች ጨዋ ፣ ባለሙያ ፣ ቆንጆ (በተለይ ጥርስና እግር) ፣ ቁመቷ ከአንድ ሜትር ከ65 እስከ 70፣ ቀይ ወይም የጠይም ቆንጆ ፣ ቤተሰቧ የታወቀ ፣ ሙሉ ጤናማ የሆነች (ስራና ሀብት ቢኖራት ባይኖራት የራሷ ጉዳይ ነው፡፡ እኔ ግድ የለኝም፡፡ ካላትም አይንን ጨፍኖ ፤ ጆሮን ደፍኖ መቀበል ነው፡፡) ፣ ኩርፊያ የማታውቅ ፤ የትምህርት ደረጃዋ የራሷ ፈንታ ነው ፤ ሃይማኖትና ዘር ግድ የለኝም፡፡ እኔን ማግባት የምትፈልግ ኢማ. ፍ.አ.ኃ.ማ ፖስታ ሳ.ቁ- 3201 አዲስ አበባ ብላ ትጻፍልኝ፡፡
*****************
ሐሙስ ታህሳስ ስምንት ቀን 1963 ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ 30ኛ አመት ቁጥር 290 እትም ደግሞ “የህግ ሚስት እፈልጋለሁ” በሚል ርዕስ ቅዳሜ ታህሳስ ሶስት ቀን 1963 ዓ.ም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጽሑፍ ያወጣውን ግለሰብ የተቃወመ ሌላ አንባቢ “ማስታወቂያ በሾርኒ” በሚል ርዕስ ለጋዜጣው የላከውን ጽሑፍ አስነብቦ ነበር፡፡
ማስታወቂያ በሾርኒ
ታህሳስ 3 ቀን 1963 ዓ.ም ቅዳሜ በወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ትዳር ፈላጊው ደሞዙን መግለጹ የወር ገቢው ከ420 ብር በታች የሆነ አባወራ ሚስት ጋዜጣውን ካየች እንዳትሸፍት ያሰጋል፡፡ እንደዚህ ያለው ራስን ማዋደጃ ያልተከፈለበት የእጅ አዙር ማስታወቂያ በጋዜጣ ሲጠየቅ የመጀመሪያ ጊዜ ባይሆንም እየበዛ መሄዱ አስፈላጊነት የለውም፡፡ ሴቶቻችንን በማስታወቂያ ጠርቶ ለትዳር በማወዳደር ትዳርን ችርቻሮ ማድረግን እቃወማለሁ፡፡
ማንም ሰው ባህሪው አካባቢውንና እድሩን ከመሰለና ከተግባባ አዛውንቱ ፣ ጓደኞቹና ሌሎች ወዳጆቹ ሚስት በማምጣት ይረዱታል፡፡ “ወላድ በድባብ ትሂድና ኧረ ምን ጠፍቶ ?” የሚለው አያጣም፡፡ ከአካባቢው ካልተግባባና ካልተቀላቀለ ግን የጠባይ ጉድለት አለበትና ለትዳርም አይሆንም፡፡ የሾርኒው ማስታወቂያ ሚስት ቢያስገኝለትም በማይግባባ ጸባዩ መፋታቱ ስለማይቀር አዲስ ዘመን ጋዜጣ ባመጣለት ሚስት ምክንያት “አማጭ ረማጭ” ሊባልብን ነው፡፡ ያን ጊዜ በአዋጅ ማስታወቂያ ያገባው እንደገና በማስታወቂያ አፋቱኝ ቢል አያስደንቅም፡፡ ምናልባትም አዲስ ዘመን ያን ጊዜ በማስታወቂያ አምዱ ላይ አስፍሮ ክፍያ ይጠይቀው ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅም10/2012
የትናየት ፈሩ