ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ 60ዎቹን የአጼ ኃይለሥላሴ ዘመን ባለስልጣናትን ያለፍርድ የረሸነው ከ45 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ህዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም ነበር።
ሐምሌ 11 ቀን 1966 ዓ.ም የንጉሱ ከፍተኛ ሚኒስትሮች ፤ ጄኔራሎችና ከፍተኛ ሃላፊዎች ከያሉበት እንዲያዙ ትዕዛዝ መሰጠቱን ተከትሎ ሁሉም በሚባል ደረጃ በፈቃዳቸው እጃቸውን ሰጡ። ከዚያም እስረኞቹ ፈጽመውታል የተባለውን ወንጀል እንዲያጣራ የተቋቋመው መርማሪ ኮሚሽን ስለ ወሎ ድርቅ ፣ ረሃብና እልቂት ምርመራ አድርጎ በእስር ላይ በሚገኙት የቀድሞ ባለሥልጣናት ላይ የወንጀል ክስ እንዲቀርብባቸው ውሳኔ አሳለፈ። ውሳኔውን ተከትሎ እስረኞቹ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ሲጠበቅ ከፀሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ በመጀመር 59 የፖለቲካ እስረኞች ላይ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ ያለፈ እርምጃ ተወሰደ።
በመርማሪ ኮሚሽኑ የምርመራ ውጤት መሠረት ያለፍርድ የተገደሉት ባለሥልጣኖች ይጠየቁበታል የተባለው ወንጀል በ1949 ዓ.ም በወጣው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ቁጥ 412 የሥራ ግዴታን ተግባር መጣስና ቁጥር 509 ችግር ወይም ረሃብ እንዲመጣ ማድረግ የሚል ነበር። የመጀመሪያው ወንጀል በሦስት ወር ፣ ሁለተኛው ደግሞ ከሦስት እስከ አስር አመት በሚደርስ እሥራት የሚያስቀጣ ነበር።
የኮሚሽኑ ምርመራ ውጤት የታሠሩትን ባለሥልጣናት በከባድ ወንጀል የማያስቀጣቸው መሆኑን የተረዳው ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ህዳር 10 ቀን 1967 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ሌላ ውሳኔ አስተላለፈ። በጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ሁለተኛ ምክትል ሊቀመንበር ሌተናል ኮሎኔል አጥናፉ አባተ ፊርማ በወጣ ደብዳቤ መርማሪ ኮሚሽኑ ክስ እንዳይመሰረት ትዕዛዝ ተሠጠ።
ከሶስት ቀናት በኋላ ህዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ አባላት “ለፖለቲካ እስረኞች የፖለቲካ ውሣኔ ለመስጠት” በሚል ጠቅላላ ስብሰባ አድርገው እስረኞቹ እንዲረሸኑ ወሰኑ። ውሣኔውን እንዲያስፈፅሙም ለአስረኛ ኮሚቴና ለደርግ አባላት ትዕዛዝ አስተላለፉ። አስረኞቹ ላይ በተከፈተ የተኩስ እሩምታም 59 ሚኒስትሮችና ጄኔራሎች ያለፍርድ ተገደሉ።
በደርግ ዘመን በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ያገለገሉትና በመጨረሻም የአገሪቱ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት ሌተናል ኮሎኔል ፍስሀ ደስታ ከ20 ዓመታት እስር በኋላ በፃፉት “አብዮቱና ትዝታዬ” በተሰኘ መፅሐፋቸው የተረሸኑት የንጉሡ ባለሥልጣናት ቁጥር 60 ሳይሆን 54 መሆኑን ይገልጻሉ።
በመጽሐፉ ምረቃ ወቅት በተደረገ ወይይት በቁጥሩ ልዩነት ዙሪያ ለቀረበላቸው ጥያቄ ኮሎኔሉ ሲመልሱ፤ “እንዲያውም 54 ሳይሆኑ ትክክለኛ የንጉሡ ባለሥልጣናት 47 ብቻ ናቸው” ሲሉ መልሰዋል። ኮሎኔል ፍስሀ 60ዎቹ የንጉሱ ባለሥልጣናት በተረሸኑበት ቀን ኮሎኔል መንግሥቱ እንዲረሸኑ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው በደብዳቤ መረጋገጡን ጠቅሰው ጽፈዋል።
አዲስ ዘመን ኅዳር 10/2012
የትናየት ፈሩ