አዳማ፡- የተጣለበትን ኃላፊነትና አደራ ከመወጣት አኳያ አደረጃጀትና አቅም ከማጠናከር ጀምሮ ለውጡን በሚመጥን መልኩ ራሱን ወደፊት ለማራመድ እየሠራ መሆኑን የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለሥልጣን ገለጸ፡፡
ባለሥልጣኑ አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ላይ የሚታዩ ተግዳሮቶችና የመፍትሔ አቅጣጫዎች ዙሪያ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከንግድና ኢንዱስትሪ ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር በአዳማ ተወያይቷል፡፡ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አስፋው አበበ በወቅቱ እንደተናገሩት ባለሥልጣኑ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ እንደ አገር የተጣለበትን ተልዕኮ ለመወጣት እየሠራ ሲሆን፣ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን ማቋቋምና ማጠናከር፣ የገበያ ትስስርና የኢንዱስትሪ ሽግግር መፍጠር፣ የኢንዱስትሪዎችን የማሽነሪና የፋይናንስ አቅም ማጠናከርና የገቢ ምርቶችን ከመተካትና ወጭ ምርቶችን ከማስፋፋት አንጻር ሰፋፊ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
እነዚህን ሥራዎች አጠናክሮ ለማስቀጠል እንዲችልም ከወቅታዊ የአገራችን ለውጥ ጋር በሚመጥን አግባብ አደረጃጀቱን እያሻሻለና የክልል መዋቅሮችን አቅም እያጠናከረ በመሄድ እንደ አገር የተቀመጠውን የኢኮኖሚ ሽግግር እውን ለማድረግ የሚያስችሉ እርምጃዎች በመውሰድ ላይ እንደሚገኝም ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡
እንደዳይሬክተሩ ገለፃ ይህ ተግባሩ የባለድርሻዎችን ተሳትፎ የሚጠይቅ በመሆኑ የሚመለከታቸው የዘርፉ ባለድርሻዎች የድርሻቸውን ወስደው መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የአሰራር ጥራትና ቅልጥፍናን ለማሻሻል እንደ ተቋም እያደረገ ካለው መዋቅራዊ አደረጃጀት ጎን ለጎን በ2011 በጀት ዓመት የመቶ ቀናት ዕቅድን በማቀድና በዚህም ላይ ከክልሎችም ሆነ ከባለሥልጣኑ አመራሮችና ባለሙያዎች በቂ ግንዛቤ እንዲይዙ በማድረግ ሰፋፊ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
በዚህም በበጀት ዓመቱ ከተያዙ ዕቅዶች ውስጥ በተለይ ለኢንዱስትሪዎች ከሚደረግ የፋይናንስ ድጋፍ አንጻር ለ4ሽ430 አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች በካፒታል ዕቃ ሊዝ ፋይናንስ አሰራር የአራት ቢሊዮን ብር ማምረቻ መሳሪያዎች እንዲ ቀርቡላቸው ለማድረግ አቅዶ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ለ6 ሽ 14 አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች የ6 ነጥብ 5 ቢሊዮን የሥራ ማስኬጃ ብር ብድር አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ክትትልና ድጋፍ ለማድረግ አቅዶ ነበር፡፡
ይህንን የፋይናንስ አቅም ለማጎልበት ከዓለም ልማት ማህበርና ከአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ በተገኘ የ276 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተር ፕራይዞች ፋይናንስ ፕሮጀክት ተቋቁሞ ወደ ሥራ እንዲገባ መደረጉን ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡ በዚህም እስካሁን ሁለት መቶ ለሚሆኑ ተጠቃሚ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕ ራይዞች ስድሳ ሚሊዮን ዶላር ሊሰራጭ ችሏል፡፡
ይህ መድረክም ባለሥልጣኑ የሚያከ ናውናቸውን ተግባራት ከመደገፍና ዘርፉን ከማሳደግ አኳያ የባለድርሻ አካላትን ድጋፍ ለማግኘት ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 22/2011
በወንድወሰን ሽመልስ