በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በሚነሱ ግጭቶች ዋነኛ ገፈት ቀማሽ የአገር አቋራጭ ትራንስፖርት ሰጪ ተቋማት ናቸው፡፡ በተጨማሪም በመሰረተ ልማት አለመዘርጋትና በአግባቡ አለመገንባትም ለአገር አቋራጭ ትራንስፖርት መሳለጥ ሌላኛው እንቅፋት ነው፡፡ ችግሮቹ ቢኖሩም የትራንስፖርት ሰጪ ማህበራቱ ግን በአብዛኛው ችግሩን ተቋቁመው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ሆኖም ከፍተኛ የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ከአቅም በላይ በመሆኑ አገልግሎት መስጠት እንዳቆሙ ይናገራሉ፡፡
አስተያየታቸውን የሰጡ የህዝብ ማመላለሻ ማህበራት እንደሚሉት፤ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ባለው የጸጥታ ችግር መስተጓጎሎች ያሉ ሲሆን አንዳንድ ቦታዎች ላይ አውቶቡሶቹ ላይ ጥቃት የማድረስ ሁኔታዎች አሉ፡፡ በመንገድ ብልሽት ምክንያት አውቶቡሶቹ እየተጎዱ ሲሆን በተፈለገው ፍጥነትም መድረሻ ከተሞች ላይ መግባት አልተቻለም፡፡
የሊማሊሞ ባስ ትራንስፖርት አክስዮን ማህበር የስምሪት ኃላፊ አቶ ፋሲል መለሰ እንደሚናገሩት፤ ወደ ሱዳን እየተጓዘ በሚገኝ ሊማሊሞ አውቶቡስ ላይ ጭልጋ አካባቢ በተተኮሰበት ጥይት ሹፌሩ ጉዳት ደርሶበታል፡፡ የተፈጠረውን ችግርም ለሚመለከተው አካል አመክተናል፡፡ በሌላ በኩል በመንገድ ችግር ደግሞ ወደ ጅማ መስመር እና የደብረታቦር መንገድ አካባቢ ባሉ የመንገድ መሰረተ ልማት ብልሽቶች ምክንያት ትራንስፖርት አገልግሎቱ ላይ ችግር ተፈጥሯል፡፡
የሊማሊሞ አውቶቡስ አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ከትኬት መቁረጥ ጀምሮ ተገቢው መስተንግዶ እየሰጠ እንደሚገኝ የገለፁት አቶ ፋሲል፤ በስልክ ደውለው ቦታ እንዲያዝላቸው ለሚጠይቁ ደንበኞችም ቀልጣፋ አገልግሎት እየተሰጠ እንደሚገኝ ይጠቁማሉ፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ያሉት የሰላም እጦትና የመንገድ መሰረተ ልማት ችግሮች ቢፈቱ የተሻለ አገልግሎት መስጠት እንደሚቻል ያመለክታሉ፡፡
የዘመን ባስ ኢትዮጵያ ትራንስፖርት አገልግሎት ስራ አስኪያጅ አቶ መኩሪያ አያሌው በበኩላቸው፤ በአገሪቱ ያለው የሰላም ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን በመጥቀስ፤ የዘመን አውቶቡስ ከመቀሌ ተነስቶ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ላይ እያለ መንገድ ላይ ጉዳት እንደደረሰበት ይገልፃሉ፡፡ በጊዜው ሹፌሩ ተሳፋሪ በመያዙ ከተመታበት ቦታ እንዲወጣ የተደረገ ሲሆን ስለደረሰው ችግር ለሚመለከተው ክፍል ደብዳቤ መፃፉን ይጠቅሳሉ ፡፡ በአሁን ወቅት አፋር አካባቢ ችግሮች አሉ በመባሉ ወደ መቀሌ የሚሄድና የሚመጣ አውቶቡስ አገልግሎት እየሰጠ አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡
‹‹ስራው አስቸጋሪ የሆኑ ነገሮች አሉበት›› የሚሉት አቶ መኩሪያ፤ ድርጅታቸው የተለዩ አውቶቡሶች ያስመጣ ሲሆን ከሃያ አወቶቡሶች እስካሁን አስሩ ሲገቡ ዋይፋይ በመትከል የመንግስት ሰራተኛው ስራውን እየሰራ እንዲጓዝ አገልግሎት እየተሰጠ እንደሚገኝ ይጠቁማሉ፡፡ በሰላም እጦት ምክንያት ነቀምት፣ መቱ፣ አሶሳ፣ ጋምቤላና ጅግጅጋ ብዙ ተሳፋሪዎች ቢኖሩም እዛ አካባቢ አገልግሎት እየተሰጠ አለመሆኑን ያስረዳሉ፡፡
በመንገድ መሰረተ ልማት ምክንያት ደግሞ ሚዛን ተፈሪ አካባቢ፣ ኮምቦልቻ፣ ደሴና ወልድያ መስመር አገልግሎት እየተሰጠ አለመሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ በመንገድ ብልሽት የመኪናዎቹ ቦዲዎች ጉዳት እየደረሰባቸው እንደሚገኝም ያብራራሉ፡፡ ድርጅቱ ትራንስፖርቱን ዘመናዊ ለማድረግ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ በመግለፅ፤ ተሳፋሪዎች በባንክ ትኬት እንዲቆርጡ የማድረግ አሰራር መጀመሩንና በቀጣይ በኦን ላይን ለመስራት እቅድ እንዳለ ያመለክታሉ፡፡
የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ለዝግጅት ክፍሉ በሰጠው መረጃ፤ ለህብረተሰቡ አገር አቋራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት በተቀላጠፈ መንገድ እየተሰጠ ቢሆንም የፀጥታና የመንገድ ብልሽቶች እንቅፋት ሆነዋል፡፡ የመንገድ ብልሽቶቹ አባይ በርሃ፣ ኮምቦልቻ፣ ደሴና ወልድያ መንገድ እንዲሁም የጅማ መስመር ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በመንገዶች ላይ የትራፊክ ምልክቶች አለመኖርም ሌላኛው ችግር ነው፡፡ እንደ ባለስልጣኑ መረጃ ከሆነ በነቀምት እና በጭፍራ አካባቢዎች ባሉ የጸጥታ ችግሮች ትራንስፖርት መቆራረጦች አሉ፡፡ ሆኖም የየአካባቢዎቹ ፀጥታ አካላትና መከላከያ ሰራዊት ጉዳዩን እየተከታተሉት ይገኛሉ፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ መንገድ የመዘጋትና የመከፈት ሁኔታዎች እንደቀጠሉ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 22/2011
በመርድ ክፍሉ