
የተከላካይ ጥብቅና ሂደት ውጤታማ በሆነ መልኩ እየተተገበረ ባለመሆኑ በኢትዮጵያ ትክክለኛ ፍትህ ለህዝቡ እንዲደርስ የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ህግ ትምህርት ቤት ተባባሪ ፕሮፌሰር ፀሀይ ዋዳ የወንጀል ፍትህ አስተዳደር በወንጀል ተጠርጥረው የሚያዙ ሰዎች በሚያልፉበት የህግ ሥርዓት ድጋፍ ማግኘት የሚያስችላቸው ሂደት መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ የፖሊስ፣ የዐቃቤ ህግና የፍርድ ቤት ሂደት ህጋዊ ድጋፍ ማግኘት የተጠርጣሪ መብት መሆኑንና በዚህም የተከላካይ ጥብቅና አገልግሎት የማግኘት መብት እንዳላቸው ያስረዳሉ፡፡
የህግ ባለሙያው እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያ የወንጀል ተሳታፊ የሚሆኑት በአብዛኛው በድህነት የሚኖሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ተጠርጣሪዎች በወንጀል በሚያዙበት ጊዜ የሚጋፈጡት ከሠለጠኑ የህግ አካላት ጋር ነው፡፡ በህግ አሰራርና ትርጉም ላይ ልምድ ካላቸው የህግ አካላት ጋር እኩል የመከራከርና ሃሳባቸውን የማስረዳት የህግ እውቀት ስለሌላቸው ተከላካይ ጠበቃ የማግኘት ሰብዓዊ መብት አላቸው፡፡ ይህም ዜጎች ባላጠፉት ጥፋት አለአግባብ ፍርድ እንዳይሰጥባቸው ለመከላከልና ከተዛባ ፍትህ ለመታደግ የሚረዳ ነው፡፡
መንግሥት በነጻ ተከላካይ ጠበቃ ማቆም አለበት፡፡ የተከላካይ ጠበቃ መብት መከበር በንጹሃን ዜጎች ላይ በምርመራ ወቅት የሚደርሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመከላከል የሚያግዝ መሆኑን ያብራራሉ፡፡
‹‹በኢትዮጵያ የወንጀል ቅጣት ከእድሜ ልክ እስከ ሞት ፍርድ እስካለ ድረስ ተጠርጣሪዎች የተከላካይ ጠበቆችን የማግኘት ሰብዓዊ መብታቸው ሊጠበቅ ይገባል›› ይላሉ ባለሙያው፡፡ ሆኖም ግን በኢትዮጵያ ይህ እየተተገበረ ነው ማለት እንደማያስችል ይጠቁማሉ፡፡ ዜጎች የተከላካይ ጠበቃ እያገኙ ባለመሆኑም በምርመራ ወቅት በመርማሪዎች በማስገደድና በማስፈራራት መብታቸው እንደሚጣስም ያስረዳሉ፡፡ መንግሥት የፍትህ ሥርዓቱን ለማስተካከል የወንጀል ፍትህ አስተዳደርን በትክክል መተግበር እንዳለበት ያስገነዝባሉ፡፡
እንደ ፕሮፌሰር ፀሀይ ገለፃ፤ በህገመንግሥቱ እና በፍትህ አስተዳደር ፖሊሲው የተከላካይ ጠበቃ መብት በአንድ አንቀጽ ብቻ እውቅና መሰጠቱ አግባብ አይደለም፡፡ አንድ ተጠርጣሪ ተከላካይ ጠበቃ የሚያስፈልገው በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ ቢሆንም በፖሊሲው የተጠቀሰው ፍርድ ቤት ለተከሰሱ ተጠርጣሪዎች ብቻ መሆኑ በፍትህ ሥርዓቱ ላይ ሰፊ ክፍተት ፈጥሯል፡፡ መንግሥት እየመደበ ያለው ተከላካይ ጠበቆች የተጠርጣሪዎቹን ክስ ማስረጃና እውነት ለማጣራት ቢሆንም ተጠርጣሪዎችን አያነጋግሩም፣ ማስረጃ አያሰባሰቡም አይደለም፤ በአንድ ክስ ጠበቆቹ ይቀያየራሉ፣ ትክክለኛ ከለላ የሚሰጡበት አሰራር የለም፤ይህ መስተካከል አለበት ይላሉ፡፡
የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያዎች ማህበር የፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አበራ ኃይለማርያም በበኩላቸው፤ ተከላካይ ጠበቃን የሚመለከት የህግ ማዕቀፍ እንደሌለ ማረጋገጣቸውን ይገልፃሉ፡፡ ተከላካይ ጠበቃ በፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ውስጥ እንደሚደራጅ በአንድ አንቀጽ ከመጥቀስ ባለፈ ፍትህ የሚያሰፍን ተቋም ተደርጎ አልተቆጠረም፡፡ ተከላካይ ጠበቆች ለድሆች የሚቆሙ መሆናቸው ከታመነ፣ በወንጀል የሚሳተፉት ደግሞ በአብዛኛው ድሆች መሆናቸውም ከታወቀና ዜጎች ከፍትህ እንዳይርቁ ለማድረግ ከተፈለገ የህግ እውቅና ሊያገኝና እንደ ተቋም ሊቋቋም ይገባል ሲሉ ይከራከራሉ፡፡
አቶ አበራ እንደሚገልጹት፤ በክልሎች የሚገኙ ተከላካይ ጠበቆች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ሥራው እንደ ትርፍ ጊዜ ሥራ ነወ የሚታየው፡፡ የተከላካይ ጠበቃ የሚመደበው በዳኞች ትዕዛዝ የድህነት ማስረጃ ሲያቀርቡ መሆኑ ደግሞ በትክክል ጥቅም ላይ እንዳይውል እያደረገው ይገኛል ብለዋል፡፡
በአሰራር ተከላካይ ጠበቃ የሚመደበው የክስ መዝገቦች ከ15 ዓመት በላይ ቅጣት የሚያስጥሉ ከሆነ ብቻ ነው። ይህም ሌሎች ዜጎች መብታቸውን እንዳይጠቀሙ ማድረጉን አቶ አበራ ይናገራሉ፡፡ በሽብርተኛነት ወንጀል፣ በሐሰተኛ ክስ፣ በማያውቁት ጉዳይ በርካታ ዜጎች የሚፈረድባቸው ጠንካራ የተከላካይ ጠበቃ ተቋም ባለመኖሩ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ ይሄ ቢኖር ኖሮ ዜጎች አይንገላቱም ነበር። በመሆኑም የተከላካይ ጠበቃ መብት ማስከበር ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡
ከፖለቲካና ከመንግሥት ሥልጣን ፍላጎት ላይ የማይመሰረት፤ ለህዝብ የቆመ አገልግሎቱ ለማን፣ እንዴት፣ መቼና በማን ይሰጣል የሚሉትን ጥያቄዎች የሚመልስ፣ ለፍትህ ጉድለቱ መፍትሄ የሚያመጣ የተከላካይ ጠበቃ ተቋም መቋቋም እንዳለበት ይናገራሉ፡፡
በፍትህ አስተዳደር ፖሊሲ የተከላካይ ጥብቅና ራሱን የቻለና ነጻ ሆኖ እንዲቋቋም 2003 ዓ.ም ላይ ቢገለጽም እስካሁን ድረስ በትክክል አልተተገበረም። አንድ ተከላካይ ጠበቃ ከ50 እስከ 700 የሚሆኑ የክስ መዝገቦችን ለመሸፈን እየተሠራ ይገኛል፡፡
እንደባለሙያዎቹ የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ጉዳይ በመንግሥት ቸል ተብሏል። በቀጣይነት በመንግሥት ትኩረት ተሰጥቶ የማይተገበር ከሆነና የተከላካይ ጠበቆች ጉዳይ በህግና ፖሊሲ ተደግፎ የማይጠናከር ከሆነ በተጠርጣሪዎች ላይ አሁን የሚታየው የሰብዓዊ መብት ጥሰት አይሎ ይቀጥላል። ፍትህም ይዛባል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 22/2011
በሰላማዊት ንጉሴ
Your knowledge and expertise on various topics never ceases to amaze me I always learn something new with each post