የኪነ ጥበብ ሰዎች ‹‹ጥበብ አይን ገላጭ ነው›› የሚል አባባል አላቸው፡፡ጥበብ እያየናቸው ግን ልብ ያላልናቸውን ነገሮች ትኩረት እንድንሰጣቸው ያደርጋል።ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ‹‹70 ደረጃ›› የተሰኘውን ዘፈኑን የለቀቀ ሰሞን ደራሲ በዕውቀቱ ሥዩም አንድ ጽሑፍ ጽፎ ነበር።አንዲት አረፍተ ነገር ብቻ ልውሰድ።‹‹ከዚህ በኋላ 70 ደረጃን በድሮው ዓይናችን አናየውም›› ብሎ ነበር።ብዙ ጊዜ ስንመላለስበት የኖርነውን 70 ደረጃ ቴዲ ከዘፈነለት በኋላ ግን የተለየ ትኩረት ተሰጠው።
በየዕለቱ የምናያቸው ነገሮች በኪነ ጥበብ መልክ ሲቀርቡ እንደ አዲስ ሆነው ይታዩናል።በነባራዊው ዓለም የምናየው ብዙ አሳዛኝ ነገር አለ፤ ኪነ ጥበብ ላይ ሲሆን ግን ያስለቅሰናል።ይሄ የኪነ ጥበብ ባህሪ ነው።ውስጣዊ ስሜት ቀስቃሽ የሚያደርገው ደግሞ አቀራረቡና በውስጡ ያለው ሴራ ነው።በተምሳሌት የሚቀርብ የኪነ ጥበብ አይነት ‹‹ምን ለማለት ይሆን›› ብለን እንድንጠይቅ ያደርገናል።ልክ ነገሩ ሲገባን ያስለቅሰናል ወይም ያስቀናል።
ባለፈው ጥቅምት ወር መጨረሻ አካባቢ በባህርዳር ከተማ ውስጥ የተዘጋጀ ‹‹አማራና ኪነ ጥበብ›› የተሰኘ የኪነ ጥበብ መድረክ ነበር።መድረኩ የመጀመሪያ ሲሆን በየዓመቱ እንደሚደረግም ተነግሯል።በመድረኩም ለውይይት መነሻ የሚሆኑ የዳሰሳ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጓል።ለዛሬው ግን በመድረኩ ላይ ስለቀረበው ቴአትር ነው ልናስነብባችሁ የተነሳነው፡፡
መድረኩ የተጀመረው በሙሉዓለም የባህል ማዕከል በተዘጋጀ ቴአትር ነው።ደራሲው ደሳለኝ ድረስ ሲሆን ቴአትሩ ‹‹ማነው?›› ይሰኛል።ቴአትሩ ርዕሱን በሚገባ ይገልጸዋል።የሚከወኑ ነገሮች ሁሉ ‹‹ማነው?›› የሚል ጥያቄ ያስነሳሉ።የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ በሚገባ ይገልጻሉ፡፡
ቴአትሩ የልብ የልባችንን ስለሚናገር ሰዎች ስሜታቸውን መቆጣጠር እያቃታቸው ጭብጨባ ይበዛበት ነበር።እንግዲህ በአዳራሹ ውስጥ የነበረው ታዳሚ የኪነ ጥበብ ሰው ነበር፤ የቴአትርን ባህሪ ያውቃል ተብሎ ይገመታል፤ ግን የውስጣቸውን ሲናገር አላስችላቸው እያሉ ያጨበጭቡ ነበር።ቴአትሩ ለመረዳት ግልጽና ቀላል ነበር።የሚጠቀማቸው ተምሳሌቶች የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ለመግለጽ ታስቦባቸው የተሰናዱ እንደሆኑ ያስታውቃሉ።ወደ ቴአትሩ!
ቴአትሩ በሙዚቃዊ ተውኔት ይጀምራል።ተዋናዮቹ የአገሪቱን ብሄር ብሄረሰቦች አልባሳት ለብሰዋል።የሶማሌ ብሄር ልብስ የለበሱ ጎንደርኛ ይጨፍራሉ፤ የጎንደር ቀሚስ የለበሱ ሶማሊኛ፣ ኦሮምኛ ይጨፍራሉ፤ የትግራይ ባህላዊ ልብስ ለብሰው ጉራጌኛ ወይም ኦሮምኛ ይጨፍራሉ።ሁሉም የብሄራቸውን ባህላዊ አለባበስ ለብሰው የራሳቸውንም የሌላውንም ይጨፍራሉ።ይሄ ደግሞ የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ነው።የባህል ዘፈን ክሊፕ ላይ አንድን ዘፈን በብሄረሰቡ አለባበስ ብናየውም በነባራዊው ዓለም ግን በራስ ልብስ የሌላውን ብሄር ይዘፈናል።ወለጋ ውስጥ ለሚከፈት ጎንደርኛ ሙዚቃ ልብስ የሚቀይር አይኖርም፤ መቀሌ ላይ ለሚከፈት ጎጃምኛ ሙዚቃ በትግራይ ባህላዊ ቀሚስ የሚጨፍሩ ይኖራሉ።ሁሉም ባለበት የሚወደው ሙዚቃ ከሰማ ባለበት ሁኔታ ይዝናናል፣ ይጫወታል፡፡
ከሙዚቃዊ አቀራረቡ በኋላ፤ አንድ መሶብ በጋራ ተሸክመው ይመጣሉ።መሶቡ ኢትዮጵያ መሆንዋ ነው።መሶቡንም በጋራ ሆነው ከፍታ ቦታ ላይ ያስቀም ጡታል።ግልጽ ተምሳሌት ነው።ኢትዮጵያ የጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤት ገናና አገር ናት፤ ከፍ ያለ ስም ያላት ናት።ይችን የጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤት የሆነች አገር ከፍታ ቦታ ላይ የሰቀሏት መላው የአገራችን ህዝቦች በአንድነትና በፍቅር ሆነው ነው።
እዚህ ላይ ነው የቴአትሩ እንቆቅልሽ የተጀ መረው!
በጋራ ሆነው ከፍታ ቦታ ላይ ያስቀመጡትን መሶብ አንዱ መጥቶ አወረደው፤ አሁንም ሌላው መጥቶ ከፍታ ቦታው ላይ አስቀመጠው።እንዲህ እንዲህ እያሉ አንዱ ሲያወጣ አንዱ ሲያወርድ ቆዩ።የሚገርመው የሚያወጣው ሰውዬ ማን እንደሚያወርድበት አያውቀውም፤የሚያወርደው ሰውዬም ማን እንዳወጣበት አያውቅም።ሁለቱም ማን እንዳደረገው እየተገረሙ ያወጣሉ ያወርዳሉ።የመሶቡ ዕጣ ፋንታ መውጣትና መውረድ ሆነ፤ የኢትዮጵያ ዕጣ ፋንታ መሆኑ ነው፡፡
ሁለቱ ሰዎች እንዲህ ሲያደርጉ ቆይተው በኋላ መሶቡን ፍለጋ ብዙዎች መጡ (የኢትዮጵያ ህዝቦች መሆናቸው ነው)።መሶቡን ሲፈልጉ አጡት! መሶቡን ያጡት ከፍታ ቦታ ላይ ተቀምጦ ነው።የተቀመጠበት ቦታ ከታች ሆኖ ለሚመለከት ታዳሚ ሁሉ በግልጽ ይታያል፤ አጠገቡ ላሉት ፈላጊዎቹ ግን ሊገኝላቸው አልቻለም።የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ይሄው ነው!
አገራችን የሥልጣኔ ባለቤትና የውድ ሀብቶች መገኛ መሆኗን የሚነግሩን የውጭ አገር ሰዎች ናቸው።ለእኛ ሊታየን አልቻለም።አጠገባችን ያለ ሀብትና ሥልጣኔ ርቆናል።
የዚህ ቴአትር ሌላኛው እንቆቅልሽ መሶቡ ከፍታ ቦታ ላይ ሆኖ ለባለቤቶች አለመታየቱ ነው።ኢትዮጵያን ያላወቅናት ገናና አገር ስለሆነች ይሆን? ከአቅማችን በላይ ሆናብን ይሆን? እንዲህ የግጭት አገር ያደረግናት የዓለም የሰላም ተምሳሌት መሆኗን ስላልኮራንበት ይሆን? አዎ! እንደዚያ ይመስላል።አገራችን የዓለም የሰላም ተምሳሌት ሆና ስትጠራ አልዋጥልን ብሎ ነበር፤ በራሳችን አገር አሟርተን ነበር።ያ! ከፍታዋ ስላልታየን አሁን እየጠፋችብን ነው።እዚህም እዚያም የሚታዩ ግጭቶች ምስክሮቻችን ናቸው።
እዚህ ጋ ደግሞ ሌላ ተምሳሌት!
ሕጻናቱ የልጆች ጨዋታ ይጫወታሉ።በኋላ ግን አንድ ችግር አጋጠማቸው።የሚጫወቱበት ገመድ ተቆጣጠረባቸው።ማፍታታት አልቻሉም።ለመፍታት ሲሞክሩም አልቻሉም።ልጆቹ ‹‹አንተ ነህ የቋጠርከው! አንቺ ነሽ የቋጠርሽው!›› ተጣሉ።እየተጨቃጨቁም ሰው እንዲፈታላቸው መንገድ ዳር ወጡ።
በአጠገባቸው ያለፈውን ሁሉ ‹‹ጋሼ መጫወ ቻችን ተቆጣጥሮብን ነው ፍታልን›› እያሉ ይጠይቃሉ። አንደኛው ተጠያቂ ‹‹አሁን ይሄን አቅቷችሁ ነው!›› ብሎ በመገረም ሊፈታ ሲሞክር አልቻለም።በኋላ ‹‹የስብሰባ ሰዓት ደረሰብኝ›› ብሎ ትቶት ይሄዳል።እንዲህ እንዲህ እያሉ ብዙ ሰዎችን ይጠይቃሉ።በእያንዳንዱ ተጠያቂ ውስጥ የሚነገር መልዕክት አለ።ለምሳሌ አንዱ ተጠያቂ፤ ‹‹የእናንተ ሥራ እኮ መጫወት እንጂ ይሄን መተብተብ አልነበረም›› ይላቸዋል።ብዙ ሰዎች የማይመለከታቸውን ነገር በመሥራታቸው ነው ብዙ ነገሮች የሚበለሻሹት የሚል መልእክት ለማስተላለፍ ተፈልጎ ነው።የማንችለውንና ያልታዘዝነውን ነገር ስናደርግ ነገሮች ይበለሻሻሉ።‹‹የስብሰባ ሰዓት እየደረሰብኝ ነው ያለው ሰውዬም የሚነግረን መልዕክት ስብሰባ የሥራ መሰናክልና ችግርን መፍታት የማይችል መሆኑን ነው፡፡
ሌላኛው ተጠያቂ ደግሞ ‹‹ዞር በሉ! ማን የተበተበውን ማን ይፈታል!›› ብሏቸው ይሄዳል።ይሄም የአገራችን ግልጽ ነባራዊ ሁኔታ ነው።ብዙ ‹‹ምን አገባኝ!›› የሚሉ ሰዎች አሉ።ይሄ ብቻ አይደለም።የተከሰቱ ጥፋቶችን ‹‹የእገሌ ነው›› ብሎ የመተው ነገር ብዙ ጉዳት አስከትሏል።ማንም በሚችለው አቅም መርዳት ሲገባው እነ እገሌ ናቸውና እንዲህ ያደረጉት ራሳቸው ይወቀሱበት እንጂ እኔ አላግዝም ባይነት በዝቷል።የአገሪቱ ፖለቲካዊ ሁኔታም ይሄው ነው።የአንዱን ጥፋት ለሌላው መስጠት።ከዚህም ሲብስ ደግሞ አብረው ያጠፉትን ጥፋት ጠቅልሎ ለአንዱ የመስጠት፤ አብረው ባያጠፉትም አንዱ ያጠፋውን ጥፋት ይቅር እንደመባባል እሱ ይጠየቅበት እንጂ እኔ ምን አገባኝ ማለት ነው።
በመጨረሻም፤ ሌላኛው ተጠያቂችግሩን ፈታው። ‹‹ጋሼ ፍታልን›› ሲሉት ‹‹ማነው እንዲህ ያደረገባችሁ?›› አላቸው፤ ‹‹እሱ ነው! እሷ ናት›› ሲጨቃጨቁ፤ ሁለቱንም ዝም አሰኝቶ እንዲህ አላቸው።‹‹አያችሁ! እስካሁን ያልፈታችሁት እኮ ለዚህ ነው፤ መጀመሪያ ተደማመጡ፤ ብትደማመጡ ኖሮ ትፈቱት ነበር።በሉ አሁን እዚሁ እያየኋችሁ ራሳችሁ ፍቱት›› አላቸው።ልጆቹም ከመጨቃጨቅ ይልቅ እየተወያዩ፤ ‹‹አንቺ ይሄኛውን ያዢ፣ አንተ ይሄኛውን ያዝ›› እየተባባሉ የተተበተበውን ገመድ ራሳቸው ፈቱት።ፈተውም በደስታ ጨዋታቸውን ቀጠሉ።
የልጆች ጨዋታ ቀጥሏል።ልጆቹ ድብብቆሽ እየተጫወቱ ነው።አንድ ልጅ ይደበቃል ሌሎች ይፈልጋሉ፤ በየተራ ይደበቃሉ፤ ይፈላለጋሉ።ድብብቆሽ ሲጫወቱ ሰዋራ ቦታ እየፈለጉ የሚደበቁትን ሲያገኙ ቆይተዋል።እንዲህ እንዲህ እያሉ ተራው ‹‹ሰላም›› የምትባለዋ ልጅ ሆነ።አኩኩሉ ተባብለው ሰላም እንድትደበቅ ተጨፈኑ።ነጋ አልነጋ ተባብለው ሰላምን ለመፈለግ ከተጨፈኑበት ተገለጡ።ልጆች ሁሉ ለመደበቅ ሰዋራ ቦታ እየፈለጉ ነበር።ሰላም ግን ያን ያህል አልደከመችም።ልጆቹ ሲጨፈኑ እዚያው አጠገባቸው ሜዳው ላይ ቁጭ አለች።ተገለጡና ፍለጋ ጀመሩ።በቀላል ሊያገኟት አልቻሉም።ወጡ፣ ወረዱ፣ ብዙ ለፉ! ሊያገኟት አልቻሉም።
በመጨረሻም ሰላም ተገኘች።ልጆቹ በጣም ተገረሙ።ያንን ሁሉ ሰዋራ ቦታ ሲያስሱ ቆይተው እዚያው አጠገባቸው ሆና አለማግኘታቸው አስገረ ማቸው።ተበሳጭተውም ጠየቋት።‹‹አንች እንዴት ትጫወችብናለሽ? ? ሳትደበቂ ነው እንዴ እዚሁ አጠገባችን ሆነሽ የምታለፊን?›› አሏት።‹‹ታዲያ አጠገባችሁ ከሆንኩ ለምን አላገኛችሁኝም ?›› አለቻቸው።
የገጸ ባህሪዋ ስም ‹‹ሰላም›› የተባለው ነባራዊውን ሰላም ለመወከል ነው።ተውኔቱም ነባራዊውን ሁኔታ ይገልጻል።‹‹ሰላም ጠፋ! ሰላም ራቀን!›› ሲባል ይሰማል።ግን ሰላም የትም አልጠፋም፣ የትም አልራቀም።ሰላም ያለው በእያንዳንዳችን እጅ ነው።ማንም የራሱን ኃላፊነት ሳይወጣ ነው ፈራጅ ሲሆን የሚገኘው።በማህበራዊ ገጾች የሀሰት ዜና ሲቀባበል እየዋለ ነው ‹‹መንግሥት ሥርዓት ያስከብርልን!›› የሚለው።ራሱ ባሰራጨው የሀሰት ዜና ነው ‹‹ይቺ አገር ወዴት እየሄደች ነው!›› እያለ ራሱ ጠያቂ የሚሆነው።
‹‹ኪነ ጥበብ ዓይን ገላጭ ነው›› የተባለው እንግዲህ ለዚህ ነው።ይህ ሲሆን ታዲያ ዓይን ገላጭ የሚሆነው ማስመሰልና አድርባይነት ያልበዛበት ኪነ ጥበብ ሲሆን ነውና እንዲህ አይነት ዓይን ገላጭ የኪነ ጥበብ ሥራዎች ይብዙልን!
አዲስ ዘመን ጥቅም6/2012
ዋለልኝ አየለ