ተወልደው ያደጉት በደቡብ ክልል ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ነው። የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በገዜ ጎፋ ወረዳ አማሮ አንደኛ ደረጃ ትምርት ቤት የተከታተሉ ሲሆን፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በሳውላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠናቀዋል። ከዲላ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በታሪክ ትምህርት የያዙ ሲሆን፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ ከሐዋሳ ዩኒቨርስቲ በልማት አስተዳደር አግኝተዋል። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እንዳጠናቀቁ ጎፋ ዞን ውስጥ በቶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ በወላይታ ሶዶ ዞን ደግሞ አረካ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና ሶዶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለአምስት ዓመት ያህል በመምህርነት አገልግለዋል።
ከመምህርነት በኋላ አመራር ሆነው ስራ የጀመሩት በ1994 ዓ.ም ሲሆን፣ ወቅቱም ኢህአዴግ የመጀመሪያ ተሃድሶ በሚያደርጉበት ጊዜ ነው። የመጀመሪያው የአመራር ስራቸውን የጀመሩት ገና በአፍላነት እድሜ ላይ ሲሆን፣ ይኸውም በጎፋ ዙሪያ ወረዳ የትምህርት ፅህፈት ቤት ኃላፊ በመሆን ነው። በዚያው ወረዳ የአቅም ግንባታ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሆነውም አገልግለዋል። እንዲሁም የወረዳ አስተዳደርም በመሆን ሰርተዋል።
የጎፋ ዙሪያ ወረዳ የሚባለው በወቅቱ በነበረው አደረጃጀት በጋሞ ጎፋ ዞን ውስጥ ያለ ሰፊ ወረዳ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ግን ወረዳው ወደ ሶስት ወረዳ ማለትም ገዜ ጎፋ፣ ደምባ ጎፋና ኦይዳ በሚል ተከፋፍሏል። ምርጫ 97 ላይ የጎፋ ዙሪያ ወረዳ አስተዳዳሪ ነበሩ። በዞን ደረጃ የነበራቸው የስራ ድርሻ ደግሞ የጋሞ ጎፋ ዞን አቅም ግንባታ መምሪያ ኃላፊና የዞኑ ደርጅት ፅህፈት ቤት ኃላፊነት ነው። ከ1998 ዓ.ም አጋማሽ እስከ 2001 ዓ.ም አጋማሽ ድረስ የጋሞ ጎፋ አመራር ሆነውም አገልግለዋል።
ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ ደቡብ ክልል ውስጥ በተለያየ ደረጃ ሰርተዋል። 2002 ዓ.ም የደኢህዴን የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ሆነው የሰሩ ሲሆን፣ ከጥቂት ጊዜ ቆይታ በኋላ ደግሞ የዚሁ ንቅናቄ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል። ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ በዚሁ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ደረጃ የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው ሰርተዋል። ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ሆነው በመስራት ላይ ይገኛሉ። በጥቅሉ ወደ አመራነት ከመጡ በኋላ ፈታኝ ሁኔታዎችን አልፈዋል። ይሁንና እነዚህ ፈታኝ ሁኔታዎች ሳያስጎነብሷቸው በጥንካሬ ወደፊት በመገስገስ ላይ የሚገኙ አመራር ናቸው-የዛሬው የዘመን እንግዳችን የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ አባልና የአዲስ አበባ ኢህአዴግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ቤልጅጌ የዛሬው እንግዳችን አድርገናቸዋል። መልካም ንባብ ይሁንልዎ።
አዲስ ዘመን፡- እስኪ በአመራርነት ዘመንዎ ብዙ ፈተናዎች እንዳጋጠመዎ ሲጠቃቅሱልኝ ነበርና ጭውውታችንን በዚሁ እንጀምር፤ለስራዎ ጋሬጣ ከነበሩት መካከል በዋናነት የሚጠቅሷቸው ነገሮች ካሉ ቢያጫውቱን?
አቶ ተስፋዬ፡- በጣም እንጂ፤ የፖለቲካ መዋቅርና የሕዝብ አስተዳደር ስራ ሲሰራ ሁሌም ቢሆን በፈተና የተሞላ ነው። ምክንያቱም አሁን እኛ የምንስራበት የሕዝብ ስራ ለመስራት ያለንበት ወቅት በአንድ በኩል ከፍተኛ የሆነ ድህነት፣ ኋላቀርነት እንዲሁም ካለፈው ረጅሙ ታሪካችን የወረስናቸው የፀረ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰቦች ያለበት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ከፍተኛ የህዝብ የለውጥ ፍላጎት ያለበት ነው። ሁሌም ቢሆን ድህነት፣ ኋላቀርነትና ኢ-ዴሞክራሲ አስተሳሰቦች እንደ ባህል ባደጉበት ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ ስራ መስራት በጣም ከባድ ነው። አንዱ በጣም ትልቅ ፈተና የነበረው ጋሞ ጎፋ ዞን ስራ ስንሰራ እኔ አመራር ሆኜ ወደ ኃላፊነት ከመምጣቴ በፊት ዞኑ ትልቅ ነውና ለአስተዳደር ስለማይመች በሁለት መከፈል አለበት የሚል አስተሳሰብ ነበር። ስለዚህም የጋሞና የጎፋ ዞን በሚል ቢደራጅ መልካም ነው የሚል ሐሳብ ነበረ።
ያኔ በነበረው አስተሳሰብ ደግሞ ‹አይሆንም አንድ ላይ ብንሆን ህዝቡ የበለጠ ይጠቀማል› የሚልም አስተሳሰብ ነበረ። በመሆኑም ለዞኑ አንድ ላይ መቀጠል ጥሩ ነው የሚል በአንድ ወገን፤ ‹አይሆንም ዞኑ በሁለት መከፈል አለበት› የሚል አመለካከት በሌላ ወገን ስለነበር ይህ ሁኔታ ለረጅም ጊዜ ከ90ዎቹ ጀምሮ እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ ብዙ ዋጋ አስከፍሏል። እኔ በዚህ ሁኔታ ላይ በጣም ብዙ ዋጋ ከፍያለሁ።
በእኛ ድርጅት ደግሞ አንድ ነገር አለ፤ ድርጅቱ የሚያስቀምጠውን አቅጣጫ አመራሩም አባሉም ይፈፅመዋል። ልዩነት ቢኖረው እንኳ ልዩነቱን ያስቀምጥና በመጨረሻ የሚወሰነውን ውሳኔ ይዞ የአብዛኛው ሰው ሐሳብ ያስፈፅማል። የእኛ የድርጅት ዲሲፒሊን የሚባለው ይህ ነው። ስለዚህ ጥያቄው የቀረበው ለድርጅት ነው፤ በአንድ በኩል በአንደኛው ወገን ‹ጥያቄያችንን የሚያፋኑት የእኛው ልጆች ናቸው› ይባላል፤ በዚህም ዋጋ ይከፈላል። በሌላ በኩል ደግሞ ‹የጎፋ ተወላጆች የጎፋን ጥያቄ ያቀነቅናሉ፤ ስለዚህም ዞኑን መበተን ይፈልጋሉ›ይሉናል። እኛ ደግሞ በመሃል ድፎ ዳቦ ሆንን። ስለዚም አንደኛው በህይወቴ ያለፍኩት ከባድ ፈተና ይህ ነው። ይህን ለማሳመን ያስቸግራል፤ ለማብራራትም ይከብዳል።
እውነት ለመናገር እኛ ስንንቀሳቀስ የነበረው በጣም በዲሲፒሊን ነው። እንደሚታወቀው ሐሳባችንን ለድርጅቱ እናቀርባለን፤ ድርጅቱ ያለውን ነገር ደግሞ እንወስዳለን። በዚህ አጋጣሚ መናገር የምፈለገው ነገር ደቡብ ክልል ውስጥ በአሁኑ ሰዓት በአምስት መዋቅር የተደራጁ ህዝቦች አሉ። እነዚህም ጋሞ ዞን፣ ወላይታ ዞን፣ ጎፋ ዞን፣ ዳውሮ ዞንና ኮንታ ልዩ ወረዳ ናቸው። የየአካባቢያቸውን ነባራዊ ሁኔታ ማዕከል አድርገው ከመብትም በይው ሌላን ነገር መሰረት አድርገው የተደራጁ ናቸው። በእነዚህ አምስቱም ውስጥ የሚኖሩ ብሄር ብሄረሰቦች አሉ። ይህ ህዝብ በባህል፣ በቋንቋ ሆነ በታሪክ አንድ ነው። በእነዚህ ህዝቦች መካከል የተወለደ የትኛውም ሰው የሚግባባው በአስተርጓሚ አይደለም። ወደፊት እያደግን ስንመጣ ይህ ህዝብ አንድ መሆኑ አይቀርም።
ምክንያቱም በአንድ በኩል በብዙ ነገር አንድ የሆንን ህዝቦች እንደመሆናችን ስለምንድን ነው አንድ ሆነን የማንቀጥለው የሚል አተያይ አለ። በሌላ ጊዜ ደግሞ ለአስተዳደር በሚመች መልኩ ተብሎ ‹የለም በዞን ይደራጅ› ይባላል። ይህ ኋላ ላይ የተተረጎመው የተለያየ ዞን ይኑር ያሉ አካላትን እንደከፋፋይ ተደርገው ነው። አንድ ላይ ይሁኑ የሚሉትን ደግሞ እንደ መብት ጨፍላቂ ተደርገው ነው። እንዳልኩሽ ይህ አይነቱ አካሄድ አንዱ ዋጋ የከፈልኩበት ነገር ነበር። እንዲያም ሆኖ ህዝቡ ዛሬም ቢሆን አንድ ህዝብ ነው።
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ የጠቀሷቸው አምስቱ ብሄሮች አንድ አይነት ቋንቋ ተናጋሪዎች ናቸው ተብሎ እርግጠኛ መሆን ይቻላል?
አቶ ተስፋዬ፡- በእርግጥ በቋንቋ አንድ አይነት ናቸው አይባልም፤ ነገር ግን የተቀራረቡ ናቸው ማለት ይቻላል። በመካከላቸው ሊኖር የሚችለው የዘዬ ልዩነት ነው። የጋራ መግባቢያ አላቸው ሊባል ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ ከሚያለያዩአቸው ነገሮች ይልቅ የጋራ የሚያደርጓቸው ነገሮች ብዙ ናቸው። በጥቅሉ ለእኔ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ፈተና ነበሩ ከምላቸው ነገሮች መካከል ከላይ የጠቀስኩልሽ ጉዳይ ነው። ይሁንና ይህን እኔ የማምነው የስራው ባህሪና ለትውልድ አሊያም በሂደቱ ውስጥ መከፈል የነበረበት ዋጋ ነው ብዬ ነው። በወቅቱ የተከፈለው ዋጋ ግን በጣም የሚያሳምም እንደነበር ግልፅ ነው። ደግሞም ብዙ ልምድም አግኝቼበታለሁ።
ሌላው ለእኔ ፈታኝ ወቅት ነበር ብዬ የምለውና ሁለተኛው ደቡብ ክልል ውስጥ በነበርኩበት ጊዜ ያጋጠመኝን ነው። በደቡብ ክልል ውስጥ ያሉ 56 ብሄር ብሄረሰቦች ከሌሎች የኢትዮጵያ ወንድምና እህት ህዝብ ጋር በጋራ የሚኖርበት ክልል ነው። በአገሪቱ ውስጥ ካሉ ብዝሃነቶች 74 በመቶ የሚሆነው የሚገኘው በደቡብ ክልል ውስጥ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ደረጃ ተመዝግቦ የተያዙ ብሄሮች 76 ናቸው። ሰዎች ግን ይህንን ቁጥር ወደ 86 ያሳድጉታል። ደቡብ ክልል የአንድነትና በጋራ የመኖር ተምሳሌት ነው። በዚህ ደግሞ በጣም እንኮራለን። እኔ ደግሞ የዚህ ታሪክ አካል በመሆኔ በግሌ በጣም እኮራለሁ። ነገር ግን ቀደም ብዬ የጠቀስኩልሽ ኋላቀርነት፣ ድህነትና ኢ-ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ስላለ ይህ ብዝሃነት አንዳንዴ ለስኬት ብቻ ሳይሆን ለተለያዩ ግጭቶችም ሲዳረግ ይስተዋላል። የተለያዩ አካላትም ለተለያየ መንገድ ይጠቀሙበታል። ይህን የሚያመጣው አንደኛ በራሳችን ውስጥ ያለ ውስጣዊ ችግር ነው። ከውስጥ እንዳለ ሁሉ ከውጭም ይጨመሩበታል።
አዲስ ዘመን፡- በቆይታዎ ስኬታማ የሆኑበት ነገር ካለ? እንዲሁም በአመራር በነበሩበት ወቅት ባላደረኩት ብለው የሚፀፀቱበት አሊያም ባይሆን ኖሮ እመርጥ ነበር የሚሉት ነገር ካለም ቢገልፁልን?
አቶ ተስፋዬ፡-በጣም ውጤታማ ሆኛለሁ ብዬ የማምነው በደቡብ ክልል ውስጥ በተለይ የድርጅት ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሆኜ ከመጣሁ በኋላ በክልሉ ውስጥ ያሉ ብሄር ብሄረሰቦች አንድነት እንዲጠናከር ከፍተኛ ኃላፊነቴን መወጣቴ ነው። ጥሩም ስራ ሰርቻለሁ ብዬ አምናሁ። ሁሉንም ህዝብና አካባቢ በእኩል አይን አይቶ ለማስተዳደርና ለመመምራት እንዲሁም እንደሰው ልጅ ለመምራት በተንቀሳቀስንበት ጊዜ ያጠፋናቸው ነገሮች አሉ።በመሆኑም ሰው ከጥፋት ነፃ አይደለም። የክልሉን ህዝብ አንድ ላይ አድርገን ሁሉንም አካባቢ አማክለን ለማስተተዳደር ያደረግነው ጥረት በህይወቴ ትልቁ የስኬት አካል ነው ብዬ የምወስደው ነው።
ለምሳሌ ከ2005 ዓ.ም አጋማሽ እስከ 2009 ዓ.ም ድረስ እኛ ኃላፊ በነብርንበት ጊዜ በተለይ እኔ የፅህፈት ቤት ኃላፊ ሆኜ በሰራሁበት ጊዜ ክልሉ የተረጋጋ ነበር። በአንድ ወቅት እንዲያውም ትዝ ይለኛል፤ በአገሪቱ ለውጥን በመፈልግ የተለያዩ ግጭቶች ባሉበት ጊዜ ደኢህዴን የ25ኛ ዓመት የብር ኢዩቤልዩ በዓል ያከብር ነበር። ጉዳዩን በጋራ በገመገምንበት ወቅት እኔ የድርጅት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ነበርኩ። በወቅቱ ለስራዬ ሙሉ ጊዜዬንም ሆነ አቅሜን በመስጠት ሳገለግል ነበር። በጥቅሉ ሁለመናዬን ለድርጅቱ ሰጥቻለሁ ማለት ይቀለኛል። ያገለገልኩትም በጣም በቅንነትና በኃላፊነት ስሜት ነው። ይህንንም እንደ ትልቅ ስኬት እቆጥረዋለሁ።
ሁለተኛው ደግሞ የጎፋ ዞን ጥያቄ ለረጅም ጊዜ የቆየ ነበር። በዚህም ደግሞ ብዙ ዋጋ የከፈልንበትና ከዚህም ከዚያም በሚደረገው ግፊት ሳንድዊች የሆንን ብንሆንም መጨረሻ ላይ ድርጅቱ ራሱ ገምግሞ ይህ ረጅም ጊዜ የቆየው የህዝብ ጥያቄ ተገቢ ነውና ምላሽ ማግኘት አለበት ብሎ በእኔ የአመራር ዘመን መመለስ በመቻሉ ከዛ በፊት ብዙ ዋጋ ያስከከፈለኝ ቢሆንም፤ እንደ ትልቅ ስኬት ነው የምቆጥረው። እነዚህ ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- በአመራር በነበሩበት ወቅት ባላደረኩት ብለው የሚፀፀቱበት አሊያም ባይሆን ኖሮ እመርጥ ነበር የሚሉት ነገር ካለ ቢገልፁልን?
አቶ ተስፋዬ፡-እንደገለፅኩልሽ በርካታ ፈተናዎችን እያለፍኩ መጥቻለሁ። በሂደት ደግሞ ደስ የማይሉ ግጭትና መሰል ነገሮች ይከሰቱ ነበር። ለምሳሌ አንዱ
በቆይታዬ በጣም ያዘንኩበት ግጭት የ2010 ዓ.ም ሐዋሳ ላይ የተፈጠረው ግጭት ነው። እንደዛ ይሆናል ብዬ በህይወቴ አስቤ አላውቅም። ኋላ ላይ ደግሞ እኔ በተወለድኩበትና ባደኩበት አካባቢም ከለውጡ በኋላ ተመሳሳይ ግጭቶች ተከስተው ነበር። በግጭቱ የሰው ህይወት መጥፋቱና ንብረት መውደሙ ያሳዝነኛል። ልቤ በጣም ከተሰበረባቸው ጉዳዮች ውስጥ እነዚህ የጠቀስኩልሽ ናቸው። ነገር ግን በዚህ ሂደት ውስጥ እኔ ባላደረኩት ብዬ የምፀፀትበት ነገር የለም። እንደ ግለሰብ ይህን በማድረጌ ተሳስቻለሁ የሚያስብለኝ ነገር የለም። እንደ ድርጅት ስርዓት የፈጠርናቸው ስህተቶች አሉ። እንደ ድርጅት ማረም ሲገባን ፈጥነን ያላረምናቸው ስህቶች ግን ነበሩ። ፈጥነን ባለማረማችንም ዋጋ አስከፍለውናል።
አዲስ ዘመን፡- ለአብነት መጥቀስ ይቻል ይሆን?
አቶ ተስፋዬ፡-ለምሳሌ በሰዎች አዕምሮ ይመላለሱ የነበሩ ጥያቄዎችን ፈጥኖ መፍታትና መመለስ ይቻል ነበር። ለምሳሌ አንዱ የመዋቅር ጥያቄ ሲሆን፣ ቶሎ ከህዝብ ጋር በመወያየት መፍታት ይቻል ነበር። ድርጅቱ ምን እንደሚያስብና ለምን አቋም እንደወሰደም ከህዝቡ ጋር መወያየትና ለህዝብ ማሳወቅ ይቻል ነበር። ህዝቡ ለሚያነሳውም ጥያቄ ‹ይሆናል› አሊያም ‹አይሆንም› በማለት ምላሽ መስጠት ያስፈልግ ነበር። እነዚህ አነዚህ አይነት ነገሮች እኛ ገና ያኔ ለውጡን ስንጀምር በጥልቅ ተሃድሶ ገምግመን ለይተናቸዋል። እነዚህን በድርጅት ከተፈጠሩ ስህተቶች ውሰጥ የኔም ድርሻ ይኖርበታል። እንደ አንድ የክልሉ ከፍተኛ አመራርና እንደ ስራ አስፈፃሚ አካል ማለቴ ነው። በዛ ውስጥ የፈጠርናቸው ስህተቶች ይኖራሉ እንጂ በግለሰብ ደረጃ ይህንን ባልፈፀምኩ፤ አሊያም ያንን ባላደረኩ የሚል ፀፀት እንኳ የለብኝም።
አዲስ ዘመን፡- ከሰሞኑን ውህደትን በተመለከተ በብዙ ይወራልና ይህን ውህደት በተመለከተ የሚሉት ነገር ካለ ቢያብራሩልን?
አቶ ተስፋዬ፡- ውህደትን በተመለከተ በተለያየ ጊዜ ጥያቄ ሲነሳ ቆይቷል። እኔ የድርጅትም ሆነ የመንግስት አመራር የሆንኩት ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩልሽ ከመጀመሪያው ተሃድሶ ከ1994 ዓ.ም በኋላ ነው። የኢህአዴግ መድረኮች ላይ መሳተፍ የጀመርኩት ደግሞ ከምርጫ 97 በኋላ ነው። ወደ ኢህአዴግ ከመጣሁ በኋላ ለምሳሌ በ2000 ዓ.ም ጀምሮ የውህደቱ ጥያቄ ይነሳል። በእኔ እይታ ጥያቄው የሚነሳበት ሁለት ምክንያት ነው። አንደኛው ጥያቄ ኢህአዴግን የመሰረቱ አራቱ ክልሉን እየመሩ ያሉ እህት ድርጅቶች በፕሮግራም ተመሳሳይ ናቸው። እንዲሁም አንድ አይነት ዓላማ አላቸው። ለምሳሌ ደኢህዴን፣ አዴፓ፣ ኦዴፓ እና ህወሓት እንደየክልላቸው ነባራዊ ሁኔታ ነገሮችን አጣጥመው የመጠቀም ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር በመሰረታዊነት በአንድ ዓላማ ዙሪያ የተሰበሰብንና አንድ አይነት ዓላማ ያለን እንዲሁም ለአንድ ፕሮግራም የምንታገል ድርጅቶች ተከፋፍለን ስለምንድን ነው ረጅም ጊዜ ግንባር ሆነን የምንቆየው።ለምን ወደ አንድ አንመጣም የሚል ጥያቄ ይነሳል።
ሁለተኛው ደግሞ አጋር ብለን የሰየምናቸው ድርጅቶች አጋር ሆነው የሚቆዩትስ እስከመቼ ነው፤ ለምንድን ነው የኢህአዴግ አካል ሆነው በባለቤትነት ከአጋርነት አልፎ ወደ ባለቤትነት የማናመጣቸው የሚል ጥያቄ ይነሳል። ሌላው ደግሞ ከዚህ ጥያቄ ጋር ተያይዞ የሚነሳው የድርጅቱን አደረጃጀት ብንቀይር በህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጡ ሐሳቦች አሉ። አንድ የጋራ ኢኮኖሚ ማህበረሰብ፤ አንድ የጋራ ፖለቲካ ማህበረሰብን ማዕከል ያደረገ የማህበረሰብ ግንባታ እናሳካለን ተብሎ ነው የተቀመጠው። አንድ አገራዊ የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመገንባት ያግዘናል፤ ስለዚህም ለምን አንዋሃድም ተብሎ ይነሳል። ጉዳዩ በዚህ መልኩ ሲነሳ የነበረው ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ እንደሆነ የሚነገር ሲሆን፣ እኔ ደግሞ ድርጅቱን ከተቀላቀልኩ ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ ነው በጆሮዬ የሰማሁት።
ይህም ሆነ በየጉባኤው ይሰጥ የነበረው ምላሽ ደግሞ ሁሌም አንድ አይነት ነበር። ይኸውም ሲባል የነበረው የሚነሳው ጥያቄ ትክክል ነው፤ ጥናት ተደርጎ ምላሽ የሚሰጠው ይሆናል የሚል ነው እንጂ ውህደት የሚባል ነገር አያስፈልግም ተብሎ ምላሽ የተሰጠበት ጊዜ የለም።
አዲስ ዘመን፡- የኢህአዴግ ውህደትን በተመለከተ ችግሩ ከአደረጃጀት ሳይሆን የመስመርና የውስጥ መበስበስ ስለመሆኑ በአንዳንድ ወገኖች ሲነገር ይደመጣል፤ችግሩ ይህ ከሆነ የኢህአዴግ ውህደት ለምን አስፈለገ?
አቶ ተስፋዬ፡- ባለፈው በሐዋሳ በተካሄደው የድርጅቱ 11ኛው ጉባኤ ላይ የኢህአዴግ የውህደት ጥያቄ እንደተለመደው ተነሳ። በአሁኑ ወቅት በጥልቅ ሪፎርም ውስጥ ስላለን ይህንኑ ለውጥ ለማስቀጥል ስለሚያግዘን ጉባኤው ለኢህአዴግ ውክልና ይስጥና ጥናት ተጠንቶ ይታይ በሚል በጉባኤው የጋራ አቅጣጫ ተያዘበት።
በነገራችን ላይ አገራዊ የለውጥ እንቀስቃሴ ውስጥ ለመግባት ዋና መነሻ የነበረው ኢህአዴግ ጊዜ ወስዶ ግምገማ ያካሄደው የታህሳስ ወሩ የ17 ቀን ግምገማ ነበር። በዛ በ17ቱ ቀን ግምገማም በጣም ትልልቅ ነገሮች ነበሩ የተነሱበት። በኋላ ላይ የአመራር ለውጥ ካደረግን በኋላ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር በአቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ኃላፊነታቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለቀቁ። በደኢህዴን በኩልም ውሳኔያቸውን ተቀብለን ለኢህአዴግ አቀረብን። በወቅቱም ደኢህዴን የአቶ ኃይለማሪያምን አቋም የተመለከተው በታላቅ አክብሮት ነው። ክቡር አቶ ኃይለማርያም አቋም የወሰዱት አገር ለማዳን ሲሉ የአመራር ለውጥ መደረግ አለበት ብለው ነው። የእርሳቸውን አቋም ደግሞ ድርጅታቸው ተወያይቶ ተቀባይነት እንዲያገኝ አደረገ። ይህም ደግሞ ለኢህአዴግ መድረክ ቀርቦ እንደ ኢህአዴግም ተቀባይነት አገኘ። ይህ በኢትዮጵያ ታሪክ ልዩ ነው፤ ልዩ ስፍራም የሚያሰጥ ነው። በኢትዮጵያም ብቻ ሳይሆን በአፍሪካም ልዩ ስፍራ የሚያስገኝ ነው።
በጣም ብዙ ኃይሎች አፍሪካ ውስጥ ለስልጣን ሲባል ህዝብ ሲያጫርሱ ይስተዋላል። የወቅቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርና የኢህአዴግ እንዲሁም የደኢህዴን ሊቀመንበር ክቡር አቶ ኃይለማሪያም የወሰዱት አቋም ታሪካዊ ነው። ታሪክ ሁሌም በትልቅነታቸው ያስታውሳቸዋል። ደኢህዴንም ታሪክ የሰራ የኢህአዴግ እህት ድርጅት ነው። ለውጥ ያስፈልጋል ብሎ አምኖ ኃላፊነትን ለቋል፤ ይህ ከ17 ቀን ግምገማ በኋላ የተወሰደ ርምጃ ነው።
ከዚያን በኋላ የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን መጥተዋል። እርሳቸው ከመጡ በኋላ በኢህአዴግ ውስጥ ለረጅም ጊዜ በሽታ የነበረው የተወሰነ ውሳኔ ወደ መሬት አለመውረዱ ነበር። እርሳቸው ደግሞ የራሳቸውን ፈጠራ ጨምረው በ17ቱ ቀናት ውስጥ የወሰንናቸውን ውሳኔዎች በከባድ ኃላፊነት ወደ መሬት አውርደዋል። ለዚህም ደግሞ ለውጡ በጣም የተቀጣጠለው እርሳቸው ኃላፊነት ወስደው ተጨባጭ ርምጃዎችን መውሰድ ሲጀምሩ ነው። እንዳልኩሽ ለዚህ ሁሉ መነሻ የሆነው የታህሳስ ወር ግምገማችን ነው።
በዚህ በታህሳስ ወር ግምገማችን አንዱ ያየነው ነገር አገራዊ ማንነትና ብሄራዊ ማንነት መሃከል ያለው ሚዛን መዛባት ነው። ኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰቦች አገር ናት። አገሪቱ ውስጥ ኢትዮጵያዊ የሆኑ በርካታ ቋንቋዎች፣ ታሪኮች፣ ባህሎችና ወጎች አሉ። እነዚህ መኖራቸው ብቻ ሳይሆን በህገ መንግስት እውቅና አግኝተዋል። ነገር ግን ኢትዮጵያዊነትን የሚሸረሽሩ መሆን የለባቸውም። ስለዚህ ያኔም የገመገምነው ነገር ቢኖር በአገራዊ አንድነትና በኢትዮጵያ ማንነትና ብሄራዊ አንድነት መካከል የሚዛን መዛባት አለ። ስለዚህ አንድ የፖለቲካ የጋራ ማህበረሰብ እንገነባለን ያልነውን ነገር በደንብ አላሳካነውምና እዚህ ላይ ችግር አለ።
አንዱ ችግር ምናልባት የኢህአዴግ አደረጃጀት ነው። ስለዚህ የኢህአዴግ አደረጃጀት የበለጠ አገራዊ ማንነታችንንና ብሄራዊ ማንነታችንን ሚዛን በጠበቀ መልኩ መሄድ አለበት፤ ስለዚህ ሁለት ነገሮች ተነስተዋል። እንዱ በውስጣችን ያለው የአስተሳሰብ ችግር ነው። የህዝብ ውግንና ማነስም ተጠቃሽ ነው፤ሌላው ደግሞ ይህ አስተሳሰብ እያደገ እንዲሄድ የራሱ አስተዋፅኦ የሚያበረክተው አደረጃጀታችን ነው። ስለዚህ አደረጃጀታችን መፈተሽ ይኖርበታል በሚል ጉባኤው አቅጣጫ በማስቀመጡ በአሁኑ ሰዓት ሂደት ውስጥ ተገብቷል። ነገር ግን አላለቀም። ወደ ሂደቱ እንዲመጣ ግን የተወሰደበት መንገድ ድርጅቱ ባስቀመጠው አቅጣጫ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የኢህአዴግ ውህደትስ አገራዊም ሆነ ዓለምአቀፋ ምን አይነት ተሞክሮና አስቻይ ሁኔታዎች አሉት?
አቶ ተስፋዬ፡- የኢህአዴግ ውህደት ሲጀመር አገር ውስጥ ካሉ ተሞክሮዎች ውስጥ በጣም ምርጡ ተሞክሮ ተብሎ የተወሰደው የደቡብ ክልል ነው። የዛሬው ደኢህዴን ይህንን ስያሜውን ያገኘው 1996 ዓ.ም ነው። 1985 ዓ.ም ደኢህዴግ በመባል ነበር የሚታወቀው። ይህ መሪ ድርጅት ሲመሰረት በ17 የብሄረሰብ ድርጅቶች ነበር፤ ቀጥሎ እያደገ በውስጡ 21 የብሄረሰብ ድርጅቶችን ያዘ። ይህ ማለት እንግዲህ በደቡብ ክልል ውስጥ ያሉ ሁሉም ዞኖች የየራሳቸው ድርጅት አላቸው ማለት ነው። እንዲህም ሲባል ሁሉም የየራሳቸው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴና ማዕከላዊ ኮሚቴ አላቸው ማለት ነው።
እንደሚታወቀው የመጀመሪያው የተሃድሶ ጊዜ ደቡብ ውስጥ ግጭት ሰፋ አለ። ደኢህዴን የሚባው ድርጅት ከአንድ ማዕከል ሆኖ ብቃት ያለው አመራር መስጠት ላይ ብዙ ተግዳሮቶች ገጠሙት። በአመራሩ መካከል የሚፈጠረው ጥርጣሬ ወደ ግጭትና ጠብ እየተጓዘ መጣ። እናም ድርጅቱ የልማት ስራዎችን በአግባቡ መስራትና መምራት እያቃተው ሄደ። ከዚህም የተነሳ ግጭት የሚያስተናግድ ክልል እንዲሆን ሁኔታዎች አስገደዱት።
ይህ ሲሆን፣ ኢህአዴግ በ1994 ዓ.ም ተሃድሶ ሲያደርግ ደቡብ ክልል ደግሞ ከራሱ ሁኔታ ተነስቶ በክልሉ ስላሉ ችግሮች ግምገማ አካሄደ። የአስተሳሰብና የአመለካከት መበስበስ በድርጅት ውስጥ መኖሩ አንድ ችግር ሲሆን፣ ለዚህ የአስተሳሰብና የአመለካከት መበስበስ ምክንያት የሆነው አሊያም ያባባሰው አደረጃጀታችን ነው በሚል ደረጃ ተወሰደ። እንዴት ሲባል ቀደም ሲል ስለኢህአዴግ እንደገለፅኩልሽ አንድ አይነት ፕሮግራምና ዓላማ ኖሮን (እንደሚታወቀው ደቡብ ክልል የተለያዩ ቋንቋዎችና ማንነቶች ያሉበት ክልል ነው። የዞኖች አደረጃጀትም ከሌሎች ክልሎች ይለያል።) ሲያበቃ በቋንቋ ብቻ የምንለያይ ሆነን ነገር ግን የተለያየ 21 ድርጅት መስርተናል። (በእርግጥ 21ዱም ድርጅቶች በወቅቱ የራሳቸውን ስራ ሰርተው አልፈዋልና ስራቸው መጥፎ ነው ማለት አይደለም)። ነገር ግን እነዚህ 21ዱ ድርጅቶች የበለጠ የህዝቦችን ትስስር እና አንድነት አጠናክረው የክልላዊ አንድነትን ደግሞ ከፍ አድርገው ከመስራት ይልቅ በየራሳቸው የየራሳቸውን ትንንሽ መንግስታት ወደመሆን ሄደዋል። ስለዚህ ይህን አደረጃጀት ለምን አናስተካክልም በሚል ዝርዝር ውይይት ተካሄደ።
ከዚያን በኋላ ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ 21 የድርጅቶች፣ 21 ማዕከላዊ ኮሚቴ፣ 21 ስራ አስፈፃሚ እንዲሁም 21 የራስን ዞን የሚያስተዳድሩ ድርጅቶች ተስማሙና ግንባርነታቸውን አፍርሰው ወደ ንቅናቄ መጡ። ከዚህም የተነሳ ከመስከረም 1996 ዓ.ም ጀምሮ የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ሆነ። ይህ ሲሆን ከ21 ማዕከላዊ ኮሚቴ ወደ አንድ ማዕከላዊ ኮሚቴ፣ አንድ የድርጅቱ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ፣ አንድ ክልላዊ የድርጅት ማዕከል በመሆን ሌሎቹ ከዞን እስከ ህዋስ ድረስ ያሉት ቅርንጫፍ እንዲሆኑ ተደረገ። በዚህም በደቡብ ታሪክ በኢኮኖሚ በጣም ከፍተኛ ለውጥ መታየት ጀመረ፤ ጉድለቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው።
ግጭቶች ደግሞ ወሳኝ በሚባል መልኩ ቀነሱ። በህዝቦች መካከልም እኛ በሰራነው ልክ ትስስሩ የተጠናከረ ሲሆን፣ ባልሰራነው ልክ ደግሞ ተቀዛቅዟል። ደኢህዴን ወጥ አመራር በመስጠት ክልሉን መምራት ቻለ። ምንም እንኳ ዛሬም የተለያዩ ጥያቄዎች ቢኖሩም የቀደመውን ስኬት ደግሞ መካድ ተገቢ አይሆንም። ምክንያቱም ተግዳሮቱን ማየት ያለብን ለብቻ ነው። ስለዚህ ምንም እንኳ በውስጡ ፈተናዎች ያልጠፉ ቢሆንም ደኢህዴግ ወደ ደኢህዴን ከመጣ በኋላ ደቡብ ክልል በጣም አድጓል ማለት ነው። በመሆኑም ይህ በአገር አቀፍ ደረጃ መልካም ተሞክሮ ነው ማለት የሚያስችል ነው።
አዲስ ዘመን፡- ውህደቱን እውን ለማድረግ የተጀመረውን እንቅሰቃሴ ተከትሎ ‹‹ውህደቱ ለምን ዛሬ ላይ እንዲሆን ተፈለገ››የሚል ጥያቄ ይነሳል። ለዚህ ምላሽዎ ምንድን ነው?
አቶ ተስፋዬ፡- ቀደም ብዬ እኮ የጠቀሰስኩት ነው፤ የውህደት ሐሳብ የተጀመረው ዛሬ ሳይሆን የቆየ ነው። ሌሎች እንደሚናገሩት በ1996 ዓ.ም ጀምሮ ነው። በነገራችን ላይ አንዱ የታህሳሱ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ከወሰናቸው ጉዳዮች አንዱ ኢህአዴግ እንደገና መታደስ አለበት፤ ራሱን እያደሰ ተሃድሶን መመምራት አለበት። ራሱን እየለወጠ ለውጡን መምራት አለበት ተብሎ ነው የተወሰነው። በዚህ አጋጣሚ እንደ ኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ለኢትዮጵያ ህዝብ ማለት የምፈልገው ትልቅ ከበሬታና ምስጋና ማቅረብ ነው። ኢህአዴግ ‹እኔ እየታደስኩ እመራለሁ› ብሎ አቋም በወሰደበት ጊዜና በአጠፋኋቸው ጥፋቶች ይቅርታ እጠይቃለሁ ባለበት ጊዜ የኢትዮጵያ ህዝብ እድል ሰጥቶታል። ይህ ይቅርታው እጅግ በጣም የበሰለ ህዝብ መሆኑን የሚያሳይ ነው።
በጣምም ታጋሽ ህዝብ ነው። ኢትጵያውያኑ እውነትም ችግርን ለማለፍና በሰከነ መንገድ ነገሮችን ለመሻገር ፍላጎትና ችሎታ ያለው ህዝብ ለመሆኑ ማረጋገጥ ይቻላል፤እግረመንገዴን አኔ የኢትዮጵያን ህዝብ ማድነቄን መግለፅም እወዳለሁ።
ስለዚህም የውህደቱ ጥያቄ መመለስ የነበረበት ዛሬ ሳይሆን ትናንት ነበር። ትናንት ካልተመለሰ ደግሞ ዛሬ ይታያል ማለት ነው። ኢህአዴግም ራሱን መልሶ ለማደስ ከሰራቸው ስራዎች መካከል አንዱ ይህ ነው። ስለዚህ በዚህ ሁኔታ ራሳችንን ማየት ተገቢ ነው። እንዲሁም አደረጃጀቱንም መፈተሽ ተገቢ ነው። ከዚህ ቀደም የፈጠርናቸውን ስህተቶች ላለመፍጠር አሊያም ለመቀነስ አደረጃጀት መፍጠር ጠቃሚ ነው ብሎ መወያየት በእኔ እምነት ትክክለኛ ነው። ችግርም የለብትም።
ነገር ግን ጥያቄ ያለው አካል ካለ አሁንም በሩ ክፍት ነው። አጀንዳው ገና ያልተዘጋ በመሆኑ እንወያይበታል። በዚህ ጊዜ መሆን የለበትም ከሚሉ አካላት ጋር ማለትም
በድርጅት ውስጥም ሆነ ከድርጅት ውጭ ካሉት ጋር መወያየት ይቻላል። ጉዳዩ የተቋጨ አይደለምና። በመሆኑም አጀንዳው በዚህ ወቅት እንዴት መጣ መባሉ አግባብነት የለውም ማለት ነው። አያስፈልግምም ያስፈልጋል የሚሉ አካላት የየራሳቸውን ሐሳብ ያቀርቡና በመጨረሻም እንደማንኛውም ዴሞክራያዊ ድርጅት አብዛኛው ያመነበት ጉዳይ በጋራ ይወሰንበትና መግባባት ላይ የተደረሰበትን ጉዳይ ወደማስፈፀም የሚገባ ይሆናል። ጥቂቶቹ ምንም እንኳ በውይይቱ ሐሳባቸው የበላይነት የማያገኝ ቢሆንም በአብላጫው ውስጥ ይካተታሉ።
ይህ አይነት አካሄድ ነው በፖለቲካ ድርጅት ውስጥም ሆነ ተቋም ውስጥ የሚደረገው። ለዚህ ነው ዴሞክራሲ ሃምሳ ሲደመር አንድ የሚለው። ስለሆነም መቶ በመቶ የሚባል ነገር በዓለም የለም። በእርግጥ ውህደቱን በተመለከተ የተለያየ ሐሳብ መኖሩና መምጣቱ እንደ ተዓምር መቆጠር የለበትም። መጨረሻ ሐሳብ ላይ የምንደርሰው ሁሉም ሐሳብ መጥቶ የተሻለው ልዕልና ሲያገኝ ነው።
ስለዚህ በእኔ እይታ ሁለት ፅንፍ የወጡ ነገሮች መታረም አለባቸው ብዬ አምናለሁ። አንደኛው በዚህ ሰዓት የውህደት ጥያቄ መነሳት የለበትም የሚሉ አካላት ልክ አይደሉም። ምክንያቱም በዚህ ሰዓት ካልተነሳ መቼ ሊነሳ ነው ታድያ። አገር ውስጥ በገባ ጊዜ አገሩን ከችግሩ ያወጣል የሚል እምነት ስላላ ነው ይህ ጥያቄ የሚነሳው። ስለሆነም ጥያቄው የቆየ ስለሆነና ጉባኤው ያስቀመጠውም አቀጣጫ ስለሆነ እንዴት ይነሳል አይባልም። ምክንያቱም ጉዳዩ በጉባኤው በተነሳ ጊዜ በወቅቱ ማንም የተቃወመ የለም። ሁለተኛው ደግሞ በዚህ ሐሳብ ላይ ለምን ተቃራኒ ሐሳብ ማለቱም አግባብነት የለውም። ምክንያቱም ተቃራኒም ሆነ ደጋፊ ሐሳብ ሊነሳ ይችላል። በመጨረሻ ግን አብዛኛው የሚደግፈው አቋም ይወሰድበታል።
አዲስ ዘመን፡- ውህደቱ በአጋር ፓርቲዎች ደስታን፣ በህወሓት ደግሞ ቅሬታን ስለማሳደሩ ከሚነገሩና ከሚወጡ መግለጫዎች መረዳት ይቻላል። ይህ ከምን የመነጨ ይሆን?
አቶ ተስፋዬ፡- በኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ደረጃ ውይይት ስናደርግ እስካሁን ውህደቱን የተቃወመ አካል መኖሩን አላስታውስም።በጉባኤም ደረጃ ውህደቱ የፀደቀው በሙሉ ድምፅ ነው። ውህደቱ አያስፈልግም ብሎ አቋም የወሰደ እህት ድርጅት የለም። በአጋር ድርጅቶች ውስጥ ደስታ ፈጥሯል የተባለው ልክ ነው። ምክንያቱም ውህደቱ ከአጋርነት ወደ ባለቤትነት ይቀይራቸዋልና። ኢህአዴግ ባለቤት መሆን አለባቸው ብሎ ብዙ ጊዜ ሲያነሳ የቀየ ነው። ስለዚህ የበለጠ በአገራቸው ጉዳይ ላይ የመወሰን ኃላፊነትን ይጨምርላቸዋል። ኢህአዴግ ለዚህ እኮ ነው ውህደቱ የዘገየ አጀንዳ ነው የሚለው።
አዲስ ዘመን፡- ውህደቱን ወደ ውሳኔ ለማስገባት የሚያችሉ ምን ምን ስራዎችስ እንደ ኢህአዴግም ሆነ እንደእህት ድርጅቶች ተሰርቷል?
አቶ ተስፋዬ፡- አንዱ ውሳኔው በጉባኤ ከተቀመጠ በኋላ በአገር ደረጃ ጥናት ተካሂዷል፤ በየብሄራዊ ድርጅቶችም ውይይት ተካዷል። በኢህአዴግ ጉባኤ መድረክ ላይም ይቀርባልና ሂደት ላይ ነው። ቀጥሎ በኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚና በኢህአዴግ ምክር ቤት መድረክ ይታይና ከዚያ በኋላ ወደአባል ይሄዳል። ስለሆነም እስካሁን የቆየበት ምክንያት ጥናቱ ባለማለቁ ነበር። በአሁኑ ወቅት ጥናቱ አልቆ ውይይት መጀመሩ እንደ መልካም የሚታይ ነው።
አዲስ ዘመን፡-የኢህአዴግ ውህደት በአንድ በኩል ህዝብን ውክልና የሚያሳጣ፤ በሌላ በኩል አሃዳዊነትን ለመመለስ የሚደረግ ጉዞ ነው የሚሉ አካላት ፅንፍ ይዘው ሲሞግቱ ይደመጣል። ይህ ደግሞ ኢህአዴግ ውህድ ፓርቲ ሲሆን የብሄሮችን በቋንቋ የመጠቀምና ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ማስጠበቅ አይችልም የሚል ሐሳብን የያዘ ነው። በዚህ ላይስ ምን ይላሉ?
አቶ ተስፋዬ፡- በዚህ ምርጡ ተሞክሮ ደኢህዴን በመሆኑ እሱን ብቻ እጠቅስልሻለሁ። ድርጅቱ ወደ አንድ ግንባር ከመጣ በኋላ ዞን ላይ ሌላ ስራ አስፈፃሚ አልነበረም። ያሉት የድርጅቱ ቅርንጫፎች ብቻ ነበሩ። ነገር ግን ሁሉም የክልሉ ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው ያስተዳድራሉ፤ በርካቶቹም በራሳቸው ቋንቋም ይማራሉ። የሌላው ባህልም ሆነ ቋንቋ አልጫነባቸውም።ባህላቸውን ያሳድጋሉ፤ታሪካቸው እንዲታወቅ ያደርጋሉ። በቋንቋቸው ይዳኛሉ። በክልሉ ለምሳሌ 25 ቋንቋዎች የትምህርት ቋንቋዎችም ናቸው። በዚህ መልኩ በርካታ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል ማለት ነው።
በአገሪቱ በታሪካችን ሁለት ነገሮች ዋጋ እያስከፈሉን መጥተዋል። አንደኛው ኢትዮጵያዊ ማንነትን በጣም አጉልቶ ብሄራዊ ማንነት የሚባል ነገር መጠቀስ የለበትም የሚለው አስተሳብ ነው። ይህም እውነታን ይስታል። ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የብሄራዊ ማንነት፣ የተለያዩ ቋንቋዎች እና እሴቶች ባለቤት የሆኑ ህዝቦች መኖሪያ ከሆነች እነዚህን ማንነቶች ሁሉ መቀበል ማለት እውነታን መቀበል ነው፤አለመቀበል ደግሞ እውነታን እንደመካድ የሚቆጠር ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ የቋንቋዎች፣ የባሎች፣ የታሪኮችና በጥቅሉ የማንነቶች አካሄዶች በጣም ተቀንቅነው ኢትዮጵያዊ አንድነታችን ላይ ደግሞ ዝቅ እንዲል ተደርጓል። ይህኛውም አካሄድ ትክክል አይደለም፤ምክንያቱም እኛ ብዙ ቋንቋ፣ ባህልና ታሪክ ቢኖረንም ያለችን አንድ አገር ናት። የሁሉም ተጠራቅሞ ነው ኢትዮጵያ የሚለውን ምስል የሚሰጠው። ስለዚህ የበለጠ ሊያቀራርበንና ሊያጠናክረን እንጂ ለልዩነታችን አሊያም ላለመግባባታችን መነሻ ሊሆን አይችልም፤ የለበትምም። ለዚህ ደግሞ ህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጠው ነገር ማክበር ነው። የፓርቲው ውህደት ህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጡ የህዝብ መብት ጋር አይገናኝም። ለማክበር የበለጠ አቅም ይፈጥራል እንጂ።
አዲስ ዘመን፡- ከፓርቲ ውህደት ጋር ተያይዞ በሐዋሳ የተካሄደው ጉባኤ ለኢህአዴግ ውህደት ከስምም ሆነ ከርዕዮተ ዓለም አንፃር ያስቀመጠውም አቅጣጫ አለ? የመደመር ሐሳብስ ከውህደቱ ጋር የሚተሳሰርበት ሂደት ይኖር ይሆን?
አቶ ተስፋዬ፡- ቀደም ሲል በጥቂቱም ቢሆን የሐዋሳውን ጉባኤ ለመግለፅ ሞክሪያለሁ። ከርዕዮተዓለም ጋር በተያያዘ በወቅቱ የተነሳው እኛ የምንመራት አቅጣጫ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ አቅጣጫ ነው። ለጊዜው ጉባኤው ላይ የልማታዊ መንግስት አቅጣጫን ያገለለ ነገር የለም። ለውጡም የሚመራው በዚህ አቅጣጫ እንደሆነ በግልፅ ተቀምጧል። ነገር ግን ርዕዮተዓለምም ሆነ ማኛውም አስተሳሰብ ያድጋል፣ ይጎለብታል፣ ይሻሻላል።
በወቅቱ ጉባኤው ሲያስቀምጥ የምንመራበት ልማታዊ ዴሞክራያዊ እንደሆነ ነው። ይህም ለውጡን በመንግስት አቅጣጫ ለመምራት ያስችላል ነው የተባለው። በዚህ ዙሪያ አንዳንድ ጥያቄዎች ተነስተው ነበር፤ ኢህአዴግ በሂደት ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ወዴት ይለወጣል? እንደገና መጠናት አለበት ወይ? ኢህአዴግ በሂደት አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚለውን ፕሮግራም ቀርፆ በተለይ ከ2001 ዓ.ም በኋላ የምንመራት አቅጣጫ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ አቅጣጫ ነው፤ ይህ አቅጣጫ ኢትዮጵያን ያሻግራል የሚል ነገር አስቀምጧል።በመሆኑም ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ አቅጣጫ ለውጡን መምራት ያችላል በሚለው ጉባኤው ላይ አብረን ተስማምተናል።
ሁለተኛው ርዕዮተ ዓለምን በተመለከተ የሚሻሻልና የሚቀየር ነገር ካለ እንደማኛውም የብረተስብ ሳይንስ ጥናት ሊጠና ይችላል እንጂ በጉባኤው ውስጥ ተቀምጠን ምንም ጥናት ባልቀረበበት ሁኔታ ይቀየራል፤ ይሻራል፤ ይቀራል ማለቱ ተገቢ አይደለም። እሱን በተመለከተ በቀጣይ በድርጅቱ ውይይትና ምክክር እንደሚቀጥልና በወቅቱ በነበረው ጉባኤ ግን ባለው አቅጣጫ እንደሚሄድ ነው አቋም የታያዘበት።
አዲስ ዘመን፡- የመደመሩስ ሁኔታ? ከውህደቱ ጋር የመተሳሰር ነገር ይኖረው ይሆን?
ከአቶ ተስፋዬ፡- የመደመሩ ሁኔታ ከውህደቱ ጋ ይሄዳል ወይስ አይሄድም የሚለው ነገር ከመግለፄ አስቀድሜ ስለመደመር አጭር ነገር ለመግለፅ ያህል መደመር ዓላማ አድርጎ የሚነሳው አንደኛ ባለፉት ጊዜያት የነበሩትን ምርጥ ልምዶች፣ ስኬቶችና ተሞክሮዎች ጠብቀን ካልንበት ወቅታዊ ሁኔታ ጋር አጣጥመን ይዘን መጓዝ አለብን ነው። ሁለተኛ መደመር ዓላማ አድርጎ የሚነሳው ባለፉት በመጣንባቸው መንገዶች የተሰሩ ስህተቶችን ሳንሸፋናቸው ማረም አለብን የሚል ነው። ሶስተኛው መደመር እነዚህ ሁለት ነገሮችን በማድረግ ለሚቀጥለው ትውልድ ጥሩ አገር፣ ጥሩ ስርዓትና ጥሩ አስተሳሰብ ማውረስ አለብን ነው።ከዚህ ተነስተን መደመርን ስንመለከት አጠቃላይ የአገራችንን ለውጡን የምንመራበት እሳቤ ነው።
ለውጡን የምንመለከትበት እይታ ነው። በዚህ እሳቤ ውስጥ ፓርቲን ሪፎርም የማድረግ እሳቤም ይታያል። ስለዚህም በፓርቲው ውስጥ እስካሁን ይዘናቸው የመጣናቸው ምርጥ ተሞክሮዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ ሲሆን፣ የተሳሳትናቸው ነገሮች ያለምንም ማመንታት እንዲታረሙ እናደርጋለን። ይህን በማድረግም ኢህአዴግ የቀጣዩ ዘመን ምርጥ ፓርቲ እንዲሆን በርካታ ተግባራትን እናከናውናለን። ኢህአዴግ በባህሪው ራሱን የማረም ብቃት ያለው ድርጅት በመሆኑ የነገም ፓርቲ እንዲሆን ነው በመስራት ላይ ያለነው።
አዲስ ዘመን፡-ኢህአዴግ እስከ ምርጫ 2012 ድረስ ውህደቱን እውን ያደርግ ይሆን? ምናልባት ውህደቱን የማይቀበሉ ድርጅቶች ቢኖሩ አጠቃላይ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ላይ ምን ተፅዕኖ ይፈጥራል?
አቶ ተስፋዬ፡- ውህደቱ ሂደቱን ጀምሯል፤ እንዋሃድ ሲባል አገሪቱን የበለጠ ለመጥቀም ነው። በመሆኑም በውህደቱ ላይ ብንወያይ እንጋባባለን የሚል አተያይ ነው ያለኝ። ስለዚህም ተግባብተን ለውጡን በጋራ የመምራት እድል አለን የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡-ታድያ እስከ ምርጫ 2012 ድረስ ውህደት ይደረጋል ወይስ አይደረግም ማለት እንችላለን?
አቶ ተስፋዬ፡- እንግዲህ እንጀምራለን፤ ሂደቱን ደግሞ በጋራ የምናየው ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- ውህደቱ ፓርቲው ከስሞ እንደአዲስ እንዲደራጅ የሚያደርገው ነውን? ከከሰመስ መንግስት የመሆን ህጋዊነቱ እንዴት ይታያል? አደረጃቱስ በምን መልኩ ይከናወናል?
አቶ ተስፋዬ፡- ይህ አባባል በጣም የፈጠነ ድምዳሜ ይመስለኛል። አቅጣጫው ፓርቲያችንን እንደገና እናድስ ነው። በአደረጃጀትም ሆነ በአስተሳሰብ እንሻሻል ነው። ይህን በማድረግም ለውጡን የሚመራ ፓርቲ እንሁን ነው።በነገራችን ላይ የመንግስት ስርዓትን ሪፎርም እናደርጋን ብለናል። የፓርቲንም ስርዓት ሪፎርም እናደርጋን ብለናል። በዚህም ሪፎርሞቹን ሁሉ በስርዓት እንመራለን ብለናል። ስለዚህም መዳራሻው ምንድን ነው የሚለውን ነገር በጋራ እየተስማማን የምንመለከተው ይሆናል።
በአሁኑ ወቅት ሁሉንም አካል ማግባባት ይችላል ብዬ የማምነው ፓርቲው ሪፎርም ማድረግ አለበት የሚለው ነው። ይህ ሲሆን ከስም ጭምር መታየት ካለበት የሚታይ ይሆናል። ስሙስ ማን ሊሆን ይችላል የሚለው የሚታይ ይሆናል። ሁሉም ግን ዴሞክራሲያዊ ስርዓትና ህጋዊ ስርዓትን ተከትሎ ነው የሚከናወነው።
አዲስ ዘመን፡- ምናልባት ውህደቱ እውን ከሆነ ከአዲሱ ውህድ ፓርቲ ህዝቡ ምን ይጠብቅ? እርሱስ ከህዝቡና ከአባላቱ ብሎም ከአመራሩ ምን ይጠበቃል?
አቶ ተስፋዬ፡- ፓርቲ እናዋህድ ስንል ማዕከሉ ምንድን ነው የሚለው ልብ ሊባል ይገባል። ማዕከሉ መልካም ነገሮች እንደ አገር እናስቀጥል፤ ስህተቶችን እናርምና የተሻለች አገር እንገንባ ነው። ህዝብም የተሻለ ኑሮ የሚኖርባት ዴሞክራያዊት አገር እንዳርግ ነው። አትዮጵያን ታላቅ አገር እናድርጋ ነው። ያላትን ጥሩ ገፅታ በማጠናከር የምትነቀፍበትን ነገር እንቀየር ነው፤ ለዚህ ደግሞ የተለወጠ አመራር ያስፈልጋል። ድርጅታችንም እንዋሃድ ሲል ከዚህ በመነሳት ነው።
ኢህአዴግ ከተዋሃደ ከእርሱ ምን ይጠበቃል የሚባል ከሆነ ለውጡን በብቃት መምራት ነው። አሁን እየተንገራገጨ ያለውን የኢኮኖሚ ችግር መፍታት፣ የጠበበውን ምህዳር ማስፋት፣ የሕግ የበላይነትን ማስከበር፣ ዜጎቿ የሚኮሩባት አገር ማድረግ፣ በጥቅሉ አገሪቱ የተረጋጋች እንድትሆን ማድረግ፣ ለህዝቧ የተመቸች አገር እንድትሆን ማድረግና ለውጡን ማሳከትና የመሳሰሉት ከድርጅቱ የሚጠበቁ ተግባራት ናቸው። ይህንን ዕውን ለማድረግ ደግሞ የኢህአዴግ አመራር፣ አባላትና ደጋፊው ሁሉም በተቻለው መጠን ጥረት ማድረግ አለበት።
እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ ውስጥ ያልተመለሱ ብዙ ጥያቄዎች አሉ። ለውጡን ይዘን የምንሄድ ከሆነ ብዙ ጥያቄዎችንም መመለስ እንደምንችል ተስፋ ፈንጥቋል። እኔነትን በመተው አገር የሚጠቅመውን አቋም ለመያዝ መዘጋጀት ያስፈልጋል። ሌላው ብዙ ጊዜ ሐሳብ እናፈልቃለን፤ ሰርቶ ውጤታማ በማድረጉ በኩል ግን ጉድለት ይታያል። ስለዚህ ሁሉም በተሰማራበት ውጤታማ መሆን ይጠበቅበታል። በኢህአዴግ ያለው ውስጥ ዴሞክራሲ እያደገና እየጎለበተ መሄድ አለበት።
የኢትዮጵያ ህዝብ በጣም ታጋሽ ነው። ስለዚህ አሁን እየታዩ ያሉ ነገሮችን በጋራ ለመቀየር መንግስትና ድርጅት የሚሰሯቸውን ስራዎች ህዝቡ መደገፍ ይጠበቅበታል። መንግስትና ድርጅት የሚሰሯቸው ስህተቶች ካሉ መገሰፅ አለበት።ነገር ግን ወደ ግጭትና ወደውድመት እንዳይሄዱ ማድረግ። ሆነ ብለው በህዝቡ ውስጥ ያለውን ቁስል ቀስቅሰው ግጭትና አለመረጋጋት እንዲፈጠር የሚያደርጉ አካላት መኖራቸውን መረዳት። በለውጥ ደጋፊ ስምም ሆነ በለውጥ ተቃዋሚ ስም የሚመጣውን አካል ለይቶ ማወቅ አለበት። ስለዚህ የትኛውም አማራጭ በግጭት፣ በጦርነትና በውድመት መሆን የለበትም ብለው ግልፅ መልዕክት ማስተላለፍ ይኖርበታል። በዚህም ያለውን ትልቅ አቅሙ በሚገባ መጠቀም ተገቢ ነው።በዚህ ረገድ ህዝቡ እስካሁንም ላደረገው አስተዋፅዖ ትልቅ አክብሮት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ሰፋ ያለ ማብራሪያ ከልብ አመስግናለሁ።
አቶ ተስፋዬ፡- እኔም ለተሰጠኝ እድል በጣም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ጥቅም6/2012
አስቴር ኤልያስ