አዲስ አበባ:- በመንግሥት ፤ በባለስልጣናትና በባለሀብቱ መካከል የሚኖረው ግንኙነት በሀገር እድገት እና ብልፅግና ላይ ብቻ ያተኮረ እንዲሆን የአማራና ኦሮሚያ ባለሀብቶች ኮሚቴ ጠየቀ።
በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነው የአማራና የኦሮሚያ ባለሀብቶች የውይይት መድረክ ትናንት በአዲስ አበባ ደሳለኝ ሆቴል ተካሂዷል። በውይይቱ ባለሀብቶች በሀገር ሰላምና አንድነት ብሎም በሁለቱ ህዝቦች ትስስር ላይ ያላቸው ሚና የተዳሰሰ ሲሆን አሁን በሀገሪቱ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች ጉዳይ ተነስቶ ውይይት ተደርጎበታል።
ኮሚቴው በመንግሥት፤ በባለስልጣናትና በባለሀብቱ መካከል የሚኖረው ግንኙነት በሀገር እድገት እና ብልፅግና ላይ ብቻ ያተኮረ እንዲሆን የጠየቀ ሲሆን፤ ባለሀብቱ ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት መሰናክልና እሳት ጫሪ ለሆኑ ግለሰቦች ምንም አይነት ድጋፍ እንዳይሰጥ መግባባት ላይ እንደተደረሰ ገልጿል፡፡ ይህንን ስምምነት በመጣስ ድጋፍ የሚያደርጉ ካሉ ባለሀብቱ በፅናት እንደሚታገልም በውይይቱ ተገልጿል፡፡
የባለሀብቶች ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ታደሰ ጥላሁን በቅርቡ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በተለይም ማንነትን መሰረት አድርገው የተከሰቱ ግጭቶች ባለሀብቱን እጅግ አሳስበውታል ብለው በጉዳዩ ዙሪያ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ጋር መምከራቸውን ገልፀዋል።
ለውጡን ተከትሎ የመጣው የአንድነትና የወንድማማችነት እድል ሁላችንም ለኢትዮጵያ ለወደፊት የብልፅግና ጉዞ ባለን አቅም ሁሉ እንድንሳተፍ በር የከፈተልን ነው ያሉት አቶ ታደሰ፤ ባለሀብቶቹ በሚያስተዳድሩት ድርጅት የሀገርና የህዝብ አንድነት እንዲጠነክር መንቀሳቀስና የሀገር አለኝታነታቸውን ማሳየት ይኖርባቸዋል ብለዋል።
የግል ድርጅቶች ያላቸው የሰው ሀይል ስብጥር የሀገራችንን ብዝሀነት በተምሳሌትነት መያዝ ይኖርበታል ያሉት ሰብሳቢው፤ የንግዱ ማህበረሰብ በገዢውም ሆነ በተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል አላስፈላጊ ወገናዊነትን ከማሳየት መቆጠብ እና ማንኛውንም ግንኙነት ለሀገር ግንባታና ብልፅግና ብቻ ማዋል ይኖርበታልም ነው ያሉት፤
ውይይቱን የታደሙት አቶ በቀለ አብዲ፤ የአማራና የኦሮሞ ህዝብ ለበርካታ ዘመናት አብሮ የኖረ መሆኑንና አሁንም በህዝቡ መካከል ጠብ አለመኖሩን ገልፀው ውይይቱ ግንኙነቱን የበለጠ ለማጠናከር እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
ባለሀብቱ ለወጣቶች የስራ እድል በመፍጠር የሚስተዋለውን ስራ አጥነት የመቅረፍ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ያሉት አቶ በቀለ፤ የሁለቱን ህዝቦች ትስስር ይበልጥ ለማሳደግም በምክክር እንደሚሰራ ገልጸዋል። የባለሀብቱና የባለስልጣናት፤ እንዲሁም የመንግስት ግንኙነት ለሀገሪቱ እድገት አስተዋፅኦ ሊኖረው በሚችል ሁኔታ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ይሰራል ብለዋል።
አቶ ሀይለ ገብርኤል አንዳርጌ በበኩላቸው፤ መሠል ውይይቶች በሁለቱ ህዝቦች መካከል ያለውን ሰላም ይበልጥ በማስጠበቅ ባለሀብቱ ለሀገር እድገት መፋጠን የሚኖረውን ድርሻ የሚያሳድግ ነው ብለዋል። “ባለሀብቱ ስራውን በአግባቡ እንዲያከናውን የሀገሪቱ ሰላም መጠበቅ ወሳኝ ነው” ያሉት አቶ ሀይለ ገብርኤል መንግስት ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ የሰጠውን ትኩረት ባለሀብቱም በያገባኛል ስሜት ሊንቀሳቀስበትና ተግባራዊ ሊያደርገው ይገባል ብለዋል።
የንግዱ ማህበረሰብ በሚሰራው ስራ ሀገር እንድትጠቀምና ልማት እንዲረጋገጥ ሰላም ሰፊውን ድርሻ ይወስዳል ያሉት አቶ ፈይሳ አራርሳ ደግሞ፤ የአማራና የኦሮሞ ህዝቦች በጋራ ሲሰሩና ሲተባበሩ አንዱ ወደሌላኛው ሄዶ የመስራት ስጋት አይኖርበትም። የሀገራችንን ህልውና በሚፈታተኑ ሀይሎች የተፈጠረው መቃቃር ተወግዶ ባለሀብቱ ለሰላምና ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ትኩረት በመስጠት መስራት ይኖርበታል ሲሉ አሳስበዋል።
አንድ ባለሀብት ወደሌላ ክልል ሄዶ በሚያለማበት ወቅት በዚያ ክልል የሚኖር ባለሀብት ጥበቃ በማድረግ ለኢንቨስትመንት መስፋፋት የራሱን ድርሻ እንዲወጣም አቶ ፈይሳ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል። ውይይቱ ‘‘ባለሀብቱ መላ አቅሙን ተጠቅሞ የተጀመረውን ለውጥ ከግብ ያደርሳል’’ በሚል መሪ ቃል የተካሄደ ሲሆን ባለ 10 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣትም ተጠናቋል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 5/2012
ድልነሳ ምንውየለት