– 731 ሺህ ብር ያለ አግባብ የተከፈለ ገንዘብ አስመልሷል
– 20 ሚሊዮን ብር ዕዳ መንግሥት እንዲሰርዝ
ውሳኔ አሰጥቷል
አዲስ አበባ፡- አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ላለፉት ዘመናት የነበረበትን የሂሳብ አያያዝ ችግር በከፍተኛ ሁኔታ ለማሻሻልና ከመንግሥት የሚጠበቅበትን ግልጽነትና ተጠያቂነት ለማስፈን እየሰራ መሆኑ ተገለጸ፡፡ 731 ሺህ ብር ያለ አግባብ የተከፈለ ገንዘብ አስመልሷል፡፡ 20 ሚሊዮን ብር ዕዳ በመንግሥት እንዲሰረዝለት ይሁኝታን አግኝቷል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሐና ዩኒቨርሲቲው በኦዲት ግኝት አስተዳደራዊ የእርምት እርምጃ መወሰዱን አስመልክተው ትላንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ተቋሙ ከሚከተለው ያልተማከለ የአስተዳደር ዘይቤ አኳያ ኃላፊነትን ከተጠያቂነት ጋር ያወረደ የሂሳብ አሰራር ሥርዓትን ለማስተካከል በውክልና ያልተማከለ የሂሳብ አሰራር ስርዓትን እየተከተለ መሆኑን፤ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የሂሳብ ስርዓት እንዲኖር የተቀናጀ የፋይናንስ አስተዳደር መረጃ ስርዓት በሁሉም ኮሌጆች ተግባራዊ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፤ ዩኒቨርሲቲው በ2007 ዓ.ም ከዋና ኦዲተር የተሰጠውን፤ ‹‹አስተያየት መስጠት የማይቻል›› የሚል የኦዲት አስተያየትን ተከትሎ በወሰደው አስተዳደራዊ እርምጃ፤ ‹‹አውት ሶርስ›› በተደረጉ አገልግሎቶች ላይ ክትትልና ቁጥጥር በማካሄድ በኦዲተር እንዲገመገም በማድረግ 731ሺ ያለ አግባብ የተከፈለ ገንዘብ ማስመለስ ችሏል፡፡ ተመን የሌላቸው ክፍያዎችና በሲቪል ሰርቪስ መስሪያ ቤት ህግ ያልተደገፈ የተለያዩ የኮሚቴ ክፍያና የማበረታቻ ክፍያም እንዲቆም ተደርጓል፡፡
ከ1998 ዓ.ም በፊት የነበረው በግለሰብ ስም፣ በድርጅት ስም በዓመተ ምህረትና በገንዘብ መጠን ተዘርዝሮ በህጉ መሠረት 20 ሚሊዮን 333ሺ 662 ብር መንግስት እንዲሰርዘው ጥያቄ ቀርቦ በውስጥ ኦዲት ተረጋግጦ ይሰረዝ የሚል ውሳኔ ማግኘቱንም አስታውቀዋል፡፡
ከመደበኛ ሥራ ሰዓት ውጭ ሠራተኞች ለሚሰጡት ተጨማሪ አገልግሎት በህጉ መሠረት ታስቦ እንዲከፈላቸው መደረጉን እንዲሁም የውስጥ ገቢ አጠቃቀምን በተመለከተ በመመሪያ ቁጥር 39/2006 እና የዩኒቨርሲቲው ቦርድ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ለእያንዳንዱ ክፍያ ተመን አውጥቶ እየከፈለ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡
አሁን በሥራ ላይ ያለው የተቋሙ አመራር ሥራውን ከተረከበበት ጊዜ ጀምሮ የተሻለ የሂሳብ አሰራር እየተከተለ መሆኑን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፤ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የሂሳብ ስርዓት እንዲኖር የተቀናጀ የፋይናንስ አስተዳደር መረጃ ስርዓት በሁሉም ኮሌጆች ተግባራዊ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በኦዲት ግኝት የተስተዋሉ ችግሮች ዩኒቨርሲቲው በተለያየ ጊዜ ሲጠቀምባቸው የነበሩ የውስጥ መመሪያዎችና አሰራሮች በቅርብ ዓመታት ከወጡ የመንግስት መመሪያዎችና አዋጆች ጋር የማጣጣም ሥራ ስላልተሰራ እንዲሁም ለዩኒቨርሲቲው የሥራ ባህሪ አስፈላጊ የሆኑ ተግባራት ሙሉ በሙሉ በደንቦች ስላልተካተቱ መሆኑንም ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 5/2012
አዲሱ ገረመው