አዲስ አበባ፡- በህዳር ወር በአንዳንድ የሰሜን፣ የምስራቅና የመካከለኛው የሀገሪቱ ተፋሰሶች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሊከሰት እንደሚችል ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
የኤጀንሲው ትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አደራጀው አድማሱ እንዳስታወቁት በአንዳንድ የሰሜን፣ የምስራቅና የመካከለኛው የሀገሪቱ ተፋሰሶች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ አልፎ አልፎ ሊዘንብ እንደሚችል አስታውቋል፡፡ በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ደረቃማ የአየር ፀባይ መኖሩ ተጨማሪ የውሃ አቅርቦት የማይፈልጉ የደረሱ ሰብሎችን ለመሰብሰብ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር እንደሆነም ገልፀዋል፡፡
ዳይሬክተሩ በማብራሪያቸው በአብዛኛው ገናሌ ዳዋ፣ ዋቤ ሸበሌ፣ ኦጋዴን፣ የመካከለኛውና የታችኛው ስምጥ ሸለቆ፣ ኦሞ ጊቤ፣የአባይ ደቡባዊ ክፍል እና በአብዛኛው ባሮ አኮቦ ተፋሰሶች ከመደበኛው የተቀራረበ ዝናብ ይኖራቸዋል ብለዋል፡፡ ጥቂት ቦታዎች ደግሞ ከመደበኛው በላይ የዝናብ መጠን ሊያገኙ እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡ ምስራቃዊ አባያ፣ አዋሽ እና ተከዜ ተፋሰሶች አነስተኛ መጠን ያለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እንደሚኖር ያመለከቱት አቶ አደራጀው ይህ ሁኔታ በአንዳንድ አካባቢዎች የደረሱ ሰብሎች በመሰብሰብ ላይ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ የሚኖረው እርጥበት ጉዳት እንዳያደርስ አስፈላጊው ቅድመ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብና ምስራቅ ወለጋ፣ ጂማ፣ ኢሉ አባቦራ፣ አርሲ፣ ባሌ፣ ምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ፣ እንዲሁም በቦረናና ጉጂ ዞኖች፣ ድሬዳዋ፣ ሐረር፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ ከመደበኛው ጋር የተቀራረበ ዝናብ እንደሚኖር ተገምቷል፡፡
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ወላይታ፣ ዳውሮ፣ ጋሞጎፋ፣ ከፋና ቤንች ማጂ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ጌዲዮና የሰገን ሕዝቦች እንዲሁም ከሶማሌ ክልል ደጋ ሀቡር፣ ፊቅ፣ ቀብሪ ደሃር፣ አፍዴር፣ ሊበንና ጎዴ በአብዛኛው ከመደበኛው ጋር የተቀራረበ ዝናብ እንደሚያገኙ ይጠበቃል ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፡፡
በሌላ በኩል ሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ እና የሸዋ ዞኖች፣ ጥቂት የምስራቅ ጎጃም ዞን፣ ምስራቅና ደቡብ ትግራይ ዞኖች ላይ አነስተኛ መጠን ያለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እንደሚኖር ተተንብየዋል::
የተቀሩት የሀገሪቱ ተፋሰሶች ደረቃማ ሆነው እንደሚቆዩም መረጃዎች አመላክተዋል፡፡ ዝናብ በሚያገኙ ተፋሰሶች ላይ የሚገኘውን ውሃ ማህበረሰቡና በውሃ እንቅስቃሴ ላይ የሚሰሩ ተጠቃሚዎች በተቻለ መጠን በአግባቡ በመያዝ ለሚፈለገው ተግባር ማዋል ይኖርባቸዋል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
በሌላ በኩል የበጋው ደረቅ፣ ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ በአንዳንድ ደጋማ የሀገሪቱ አካባቢዎች ውርጭ ሊያስከትል እንደሚችል ትንበያው ማመላከቱን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ዘግይተው ለተዘረዘሩትና ፍሬ የማፍራት ደረጃን ላለፉ ሰብሎች ተጽዕኖ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅም4/2012
ሙሐመድ ሁሴን