አዲስ አበባ፡- የኢህአዴግን የውህደት ጉዞ እውን ለማድረግ የተከናወነው የጥናት ሰነድ ወደተግባር እንዲገባ ከህወሓት በስተቀር ሶስቱም የኢህአዴግ ድርጅቶች በየማዕከላዊ ኮሚቴዎቻቸው ማጽደቃቸው ተገለጸ፡፡ አጋር ድርጅቶችም የውህ ደቱን ጠቀሜታ በመገንዘብ ተግባራዊ እንዲሆን መወሰናቸው ተጠቁሟል፡፡
የኢህአዴግ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪክ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በ11ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የኢህአዴግን ውህደት እውን ለማድረግ የተከናወነው ጥናት በየደረጃው ውይይት ተደርጎበታል፡፡ መልካምና ስጋት ናቸው የተባሉ ጉዳዮች በዝርዝር ታይተውም ከህወሓት በስተቀር አዴፓ፣ ኦዴፓና ደኢህዴን በየማዕከላዊ ኮሚቴዎቻቸው አጽድቀውታል፡፡
እንደ አቶ ፍቃዱ ገለጻ፤ ውህደቱ በኢህአዴግ 11ኛ ጉባኤ አራቱም ድርጅቶች አቅጣጫውን የተቀበሉበት፤ በሙሉ ድምጽም የጸደቀ ነው:: እስካሁንም በድርጅት ወስኖና በግንባር ቀርቦ ውህደቱ አያስፈልግም ብሎም የመጣም የተናገረም የለም፡፡ ውህደቱን እውን ከማድረግ አኳያም በኢህአዴግ ሁሉም አባል ድርጅቶች ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር ደረጃ በጥናቱ ላይ አስተያየት ተሰጥቶበታል፡፡ በሥራ አስፈጻሚ እና በማዕከላዊ ኮሚቴ ደረጃም ውይይት ተደርጎበታል ብለዋል:: ከዚህ ባለፈም የአጋር ድርጅቶች ሊቀመናብርት፣ ሥራ አስፈጻሚዎችና ማዕከላዊ ኮሚቴዎችም ተወያይተውበታል፤ ጠቃሚነቱን ተረድተውም ውህደቱ እውን እንዲሆን መወሰናቸውን ገልፀዋል፡፡
እንደ አቶ ፍቃዱ ማብራሪያ፤ በህወሓትበኩል አሁን የሚሰማው ቅሬታና ተቃውሞም ‹‹እኛ ካልመራነውና እኛ የበላይነቱን ካላረጋገጥን በስተቀር፣ እኛ ያልነካነውና ያልቀደስነው ነገር አይሆንም›› ከሚል የሚነሳ ነው እንጂ ምንም አይነት ህጋዊም ሆነ ፖለቲካዊ መሰረት ሊቀመጥለት አይችልም፡፡ ነገር ግን የበላይነቱን ይዞ የነበረው ቡድን እንዳለ መቀጠል ስለሚፈልግ የሚያነሳው ጉዳይ ነው::
በአንጻሩ ግን ለውህደቱ የአጋር ድርጅቶች ድጋፍ መስጠታቸው፣ እስካሁን ዳር ቆመው ተመልካች የሆኑበትን፤ ያልወሰኑትን እንዲያስፈጽሙ ሲደረጉ የነበረበትን አካሄድ የሚቀይር፤ ፍትሃዊ ተሳትፎና ተካታችነታቸው ተረጋግጦ በራሳቸውም ሆነ በአገራቸው ጉዳይ ያለተጽዕኖ መወሰን የሚችሉበት እውነተኛ ፌዴራሊዝም የሚፈጠር መሆኑን መተማመን ላይ ደርሰዋል ብለዋል፤ አቶ ፍቃዱ፡፡
በመሆኑም ሌላ ዓላማና የተደበቀ አጀንዳ ከሌለ በስተቀር ውህደቱ የራስን ጉዳይ በራስ እየወሰኑ በአገር ጉዳይ በእኩል ተሳትፎ አብሮ መወሰን መቻል ለማንም ተነጥሎ የሚሰጥ ጥቅም ሳይሆን የሁሉም ህዝብ ጥቅምም፤ ፍላጎትም በመሆኑ ማንም ሊደግፈው እንጂ ሊቃወመው የሚገባ አይደለም፡፡ ህወሓትም ቢሆን ቀደም ሲል ውህደቱ እንዲፈጸም ሲወተውት ነበረ ሲሉ ወቅሰዋል፡፡ የሀሳብ ለውጥ ያመጣው የአመራር ለውጥ ከተደረገ በኋላ ሲሆን፤ ሀሳቡም ብዙም ውሃ ሊቋጥር የማይችል ስለሆነ ትምህርት ሊወሰድበት ይገባል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 4/2012 ዓ.ም
ወንድወሰን ሽመልስ