• 68 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ለመመስረት ዝግጅት ተጠናቋል
አዲስ አበባ፡- ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በባህርዳር እና አዲስ አበባ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ላይ የተፈፀሙት ጥቃቶች በብርጋዴር ጀኔራል አሳምነው ፅጌ የተመራ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ መሆኑን፤ 68 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ለመመስረት ዝግጅት መጠናቀቁን የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ገለፀ፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ብርሀኑ ፀጋዬ ሰኔ 15 በአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የሥራ ባልደረቦቻቸው እንዲሁም በቀድሞ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንን ላይ የተፈፀመውን ጥቃት አስመልክቶ ሲያካሂድ የነበረውን ምርመራ ማጠናቀቁን አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳመለከቱት፣ በአማራ ክልል ሰኔ 15 ቀን 2011 በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን፣ አቶ እዘዝ ዋሴ እና አቶ ምግባሩ ከበደ ላይ የተፈፀመው ጥቃት በብርጋዴራል ጄኔራል አሳምነው ፅጌና ባልደረቦቻቸው ለመፈንቅለ መንግሥት ተልዕኮ በተሰጣቸው አካላት የተፈፀመ መሆኑን በምርመራ ተረጋግጧል፡፡
ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌ እና ለመፈንቅለ መንግሥት ተልዕኮ በተሰጣቸው አካላት ከክልሉ ልዩ ኃይል የተውጣጡ ሰዎች በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ፅህፈት ቤት ስብሰባ ላይ እንዳሉ ዶክተር አምባቸው መኮንን በጥይት ተደብድበው ህይወታቸው እንዲያልፍ አድርገዋል ብለዋል፡፡ እንዲሁም በአቶ እዘዝ ዋሴ ላይ በተመሳሳይ ጥቃት ህይወታቸውን እንዳለፈ የገለፁት ዓቃቢ ህጉ፤ በወቅቱ ጥቃት የተፈፀመባቸው አቶ ምግባሩ ከበደም ህክምና ላይ በነበሩበት ወቅት ህይወታቸው አልፏል፡፡ ጉዳዩንም በሰው እና በሰነድ መረጃ ማረጋገጥ እንደተቻለ አቶ ብርሀኑ አመልክተዋል፡፡
በጥቃቱ የ15 ሰዎች ሞት፣ በ20 ሰዎች ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት ማጋጠሙን የተናገሩት ዓቃቢ ሕጉ፤ ከዚህ ጥቃት ጋር በተያያዘ 114 ክለሽንኮቭ፣ ሶስት ብሬን እና ሌሎች መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አመልክተዋል፡፡ ሌሎችምለጥቃቱ ጥቅም ላይ የዋሉ መሳሪያዎች ተለይተዋል ብለዋል፡፡ ከተጠርጣሪዎቹ መኖሪያ ቤት፣ መኪና፣ ፍላሽ ዲስክ እና ኮምፒዩተሮች የተገኙ መረጃዎች በኤግዚቢትነት መያዛቸውን ጠቅላይ ዓቃቢ ህጉ ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ላይ በቀድሞ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንን እና ሜጀር ጄኔራል ገዛኢ አበራ ላይ የተፈፀመው ጥቃት በብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌ የተመራው መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ አካል ነው ያሉት አቶ ብርሀኑ፤ ዓላማው ጄኔራል ሰዓረ መኮንን ግድያ ከተፈፀመ በኋላ ጥቃቱን ተከትሎ በስፍራው ይገኛሉ ተብሎ የተገመቱትን ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላን በመግደል በሰራዊቱ ውስጥ መከፋፈል ለመፍጠር የታሰበ እንደነበርም ጠቁመዋል፡፡
በዚህም በባህር ዳር በከፍተኛ ሥራ ኃላፊዎች ላይ ግድያው ከተፈፀመ ከሰዓታት በኋላ ጄኔራል ሰዓረ መኮንን እና አብረዋቸው በነበሩት ሜጀር ጄኔራል ገዛኢ አበራ ላይ በግል ጠባቂያቸው ግድያ ሊፈፀም እንደቻለ ጠቁመዋል፡፡ ይህ ጥቃት ከሚያዚያ 2011 ጀምሮ ዝግጅት ሲደረግበት እንደነበር በምርመራው መረጋገጡን የተናገሩት ጠቅላይ ዓቃቤ ህጉ በብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌ እና በአክቲቪስቶች ዝግጅት የተደረገበት ወንጀል ነው ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ እንዳመለከቱት፤ በአሁኑ ወቅት የሰነድና የሰው ማስረጃ የተጠናቀቀባቸው ከባህርዳር 55 እና ከአዲስ አበባ 13 ክስ ለመመስረት ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ጥቃት ጋር በተያያዘ በባህር ዳር 277 እንዲሁም 140 ተጠርጣሪዎች አዲስ አበባ ላይ በቁጥጥር ስር ውለው እንደነበር አስታውሰዋል:: በእነዚህም ላይ በተካሄደው ምርመራ ከባህርዳሩ 45ቱ የወንጀል ተሳትፎዎቻቸው አነስተኛ መሆኑን ተከትሎ በምስክርነት ተለይተዋል ተብሏል:: ከአዲስ አበባዎቹ 140 ተጠርጣሪዎች 61ዱ በዋስትና መፈታታቸውን የገለፁት ጠቅላይ ዓቃቤ ህጉ 5ቱ ደግሞ ከመፈንቅለ መንግሥቱ መከራ ውጭ ከጦር መሳሪያ ዝውውር ጋር ጉዳያቸው እንደተያያዘ ተጠቁሟል፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ህዳር 4/2012 ዓ.ም