አዲስ አበባ፡- በወለጋ ዩኒቨርሲቲ በተማሪዎች መካከል ምንም አይነት ችግር እንዳይፈጠር መዋቅሩን ተከትለው እየሰሩ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ሀሰን ዩሱፍ ተናገሩ፡፡ በዩኒቨርሲቲው እስካሁን የሰላም መደፍረስ አለመኖሩንም ገልጸዋል፡፡
ዶክተር ሀሰን በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ በዩኒቨርሲቲው የሰላም ፎረም፣ የተማሪዎች ህብረት፣ የሴት ተማሪዎች ማህበርና ሌሎችም አደረጃጀቶች በመኖራቸው ምንም አይነት ችግር እንዳይፈጠር መዋቅሩን ተከትለው በመስራት ላይ ናቸው፡፡
ከከተማውና ከዞን መስተዳድር ጋር በመሆንም ነገሮች ሰላማዊ እንዲሆኑ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ ተማሪዎችም በየክፍለ ትምህርታቸው አማካይነት ውይይት እንዲያደርጉና ጥያቄ ቢኖራቸው እንኳ ትምህርታቸውን በአግባቡ እየተማሩ እንዲያቀርቡ እየተደረገ ይገኛል፡፡
በአሁኑ ወቅት መምህራኑም ሆኑ ሌሎች ሠራተኞች በሥራ ላይ ናቸው ያሉት ዶክተር ሀሰን ሁሉም ተማሪ በግቢው ውስጥ ነው፡፡ተማሪዎች ትምህርት የማቋረጥ ፍላጎት የላቸውም፡፡ የመማር ማስተማሩ ሥራ እንዳይታወክና በተማሪዎችም መካከል ምንም አይነት ግጭት እንዳይፈጠር ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ነው፡፡
ዶክተር ሀሰን ለተማሪዎች ባስተላለፉት መልዕክት ፤ ችግር የትም ቦታ ዛሬም ወደፊትም ሊታይ ይችላል፤ ነገር ግን እንዲህ አይነት ነገር ሲከሰት ቆም ብሎ መረጃዎችን ማጣራት ፣ አንዳንዴ በሚከሰቱ ጉዳዮች የሚጨማመሩ እኩይ የሆኑ ሐሳቦች ስለሚኖሩ ተማሪዎች ለእነዛ በማህበራዊ ድረገፅ ለሚከሰቱ የተሳሳቱ አመለካከቶች ስሜታዊ ሆነው ምላሽ ከመስጠታቸው በፊት አስተውሉ፡፡ ስህተትን በስህተት ማረም አግባብ አለመሆኑንም መረዳት ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
‹‹ማንም ከዚህኛው አሊያም ከዚያኛው ብሄር መወለድ ይሻለኛል ብሎ ፈልጎ የተወለደ የለም፡፡ ስለዚህም ይህን አውቆ አንዱ በሌላው ላይ አላስፈላጊ ድርጊት ማድረግ አይገባም፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሲሆን፣ ተምሮ ራሱንና አገሩን ለመቀየር ነው ትኩረት ማድረግ የሚጠበቅበት፡፡
ስለዚህም ከጎናቸው ያለ ወንድማቸው አሊያም እህታቸው ሊጎዱ አይገባም፡፡ በአንድ ዩኒቨርሲቲ አንድ ነገር ሲከሰት ያንን የማዛመቱ ነገር ትርፉ ኪሳራ መሆኑንም ማወቁ ተገቢ ነው፡፡ ችግሩን ለማዛመት አጋዥ ከመሆንም መታቀቡ መልካም ነው፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ በትጋት በመስራት ላይ ነው፡፡›› ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 3/2012
አስቴር ኤልያስ