አዲስ አበባ፡- ‹‹የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ውህደት በህገ መንግሥቱ የተቀመጠውን የሕዝብን መብት ባከበረ መልኩ የሚደረግ ነው›› ሲሉ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ አባልና የአዲስ አበባ ኢህአዴግ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ቤልጅጌ ገለፁ፡፡
የኢህአዴግ ውህደት ሲታሰብ ምርጥ ተሞክሮ ተደርጎ የተወሰደውም የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ አባልና የአዲስ አበባ ኢህአዴግ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ቤልጅጌ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለፁት፤የኢህአዴግ ውህደት የሚካሄደው የሕዝብን መብት ባከበረ መልኩ ነው፡፡
በውህደቱም ኢትዮጵያ የብዙ ብሄር፣ብሄረሰብና ህዝቦች አገር እንደመሆኗም የሁሉም ቋንቋ፣ ባህል፣ወግና እሴት ይከበራል እንጂ አይጣስም፡፡ ኢህአዴግ ህገመንግሥታዊ መብትን የሚሸረሽር ነገር አያደርግም፤ አይሞክረውምም፡፡
አቶ ተስፋዬ እንደተናገሩት፣ኢህአዴግ የታገለውም ለብሄር ብሄረሰቦች መብት መከበር ነው፡፡ውህደቱ ይህንን የብሄር ብሄረሰብን መብት የበለጠ ለማክበር የሚያግዘው ይሆናል፡፡ ውህደት ይፈጠር የተባለውም የሕዝብን መብት በማክበር ኢትዮጵያን ታላቅ ለማድረግ ፣ ለውጡንም በብቃት በመምራት የህዝቡን ኑሮ ለማሻሻልና የአገሪቱንም ኢኮኖሚ ለማሳደግ ነው፡፡ ከዚህም ባለፈ የህግ የበላይነትን የበለጠ ለማስከበርና የፖለቲካ ምህዳሩንም በማስፋት አገሪቱን የተረጋጋች እንድትሆን ለማድረግ ነው፡፡
‹‹ኢህአዴግ ውህደትን ሲያስብ ምርጥ ተሞክሮ ተደርጎ የተወሰደው ደኢህዴን ነው›› ያሉት አቶ ተስፋዬ፣ደኢህዴን ቀደም ሲል በ17 ድርጅት ተመስርቶ ወደ 21 ደርሶ እንደነበር ገልፀዋል፡፡ይህም አደረጃጀቱ ለመበስበሱ ምክንያት እንደሆነውና አካሄዱም ትንንሽ መንግሥት ወደመፍጠር ለመጓዝ መንደርደሩን ግንባሩ በመረዳቱ ውይይት አካሂዶ ለውህደት መስማማቱን አስታውሰዋል፡፡
ይህም በመሆኑ ግንባር የሆኑት 21ዱ ድርጅቶች በመስማማታቸው ወደ ንቅናቄ መምጣት መቻላቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በዚህም ከ21 ማዕከላዊ ኮሚቴም ወደ አንድ ማዕከላዊ ኮሚቴ መምጣት መቻሉን ገልፀዋል፡፡ ይህም አደረጃጀት በክልሉ ኢኮኖሚያዊና መልካም አስተዳደር ዙሪያ ለውጥ ለማሳየት አስችሏል፡፡
ምንም እንኳ ዛሬም የተለያዩ ጥያቄዎች ቢኖሩም፤ደኢህዴን በክልሉ ወጥ አመራር በመስጠት ክልሉን መምራት ችሏል፡፡ በክልሉ የሥራ ቋንቋ አማርኛ ቢሆንም 25 ቋንቋዎች ትምህርት የሚሰጥባቸው ናቸው፡፡
አቶ ተስፋዬ መደመርን አስመልክተው እንደገለፁትም፣ መደመር ያለፈውን ምርጥ ተሞክሮ ይዞ የሚነሳ ሲሆን፣በተመጣበት መንገድ ደግሞ የተሰሩ ስህተቶችን ማረም እንደሚያስፈልግ የሚገልፅ ነው፡፡ ለቀጣዩ ትውልድም የተሻለች አገር የማስረከብ እሳቤን የያዘ ሲሆን፣ለውጡ የሚታይበት እሳቤም ነው፡፡
አገሪቱ ያላትን መልካም ነገሮችን በመሰብሰብ ወደብልፅግና እንድታመራ የሚያስችላትን ፅንሰ ሐሳብ የያዘ ነው፡፡ ይህን ለማሳካት ደግሞ ሁሉም ካለበት ፅንፍ ወጥቶ ወደ መሃል መምጣትን ይጠይቀዋል፡፡
አቶ ተስፋዬ፣‹‹አሁን የተጀመረው የሪፎርም እንቅስቃሴ በአንድ በኩል ተስፋ በሌላ በኩል ደግሞ ተስፋውን የሚገዳደር ጋሬጣ ስላለበት ይህን ለማለፍ ያስችል ዘንድ በሐሳብ የበላይነት ላይ ማመን አለብን፡፡›› ብለዋል፡፡‹‹የእኔ ከሁሉ ይሻላል የሚለውን አስተሳሰብ በመተው ለአገር በሚጠቅመው አቋም መደመር ይበጃል፡፡ ለዚህም ህዝብም ሆነ ወጣቱ ያለውን ትልቅ አቅም በአግባቡ ቢጠቀም መልካም ይሆናል፡፡›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 3/2012
አስቴር ኤልያስ