
የውሃ አካላትን በስፋት እያጠቃ የሚገኘውን የእንቦጭ አረምን ለመከላከል ጥቅም ላይ ከዋሉት ዘዴዎች ባለፈ ሳይንሳዊ አማራጮችን መጠቀም ያስፈልጋል። በመሆኑም ምን አይነት ሳይንሳዊ የመከላከያ መንገዶች መተግበር ይቻላል? ለሚለው ጥያቄ የዘርፉ ባለሙያዎች ምላሽ አላቸው።
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በብሉ ናይል ውሃ ምርምር ተቋም ተመራማሪ እንዲሁም በባዮሎጂ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ጌታቸው በነበሩ፤ እንቦጭን በሳይንሳዊ መንገድ መቀነስ የሚቻልባቸው መንገዶች በርካታ መሆናቸውን ይገልፃሉ። ነገርግን ለየትኛው ቦታ የትኛውን መንገድ መከተል ያስፈልጋል? የሚለውን መጀመሪያ መፈተሽ ይገባል።
አሁን በስራ ላይ ያሉትን የእንቦጭ ማጨጃ ማሽኖች መጠቀሙ ብቻ አዋጭ አይደለም። ምክንያቱም ማሽኖቹ በአግባቡ ሊሰሩ የሚችሉት ሐይቅ ዳር ላይ ብቻ ነው። ከዋጋም አንጻር ውድ በመሆናቸው አዋጭ አይደሉም። በመሆኑም የውሃ አካላት መሃል ላይ በብዛት የሚበቅለውን እንቦጭ ለማጥፋት የስነህይወታዊ መቆጣጠሪያ ዘዴዎች አስፈላጊና አዋጭ መሆናቸውን ይገልፃሉ።
በእንቦጭ አረም ላይ በዓለም ደረጃ የተሰሩ የስነህይወታዊ የምርምር ዘዴዎች አሉ። በስነ ህይወታዊ ዘዴ እንቦጭን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚያስችሉ የተለያዩ ህይወት ያላቸው ተባዮች አሉ። ከነፍሳቱ በተጨማሪ ለእንቦጩ መስፋፋት የሚረዱ ወደውሃ ውስጥ የሚገቡትን ንጥረ ነገሮችም መቆጣጠር እንደሚገባ ያስረዳሉ።
ወይዘሮ ብርሃን መሃመድ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪ ማሟያ ጥናታቸውን በእንቦጭ አረም ላይ በመስራት ላይ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ከማሽን እና ከእጅ ነቀላው በተጨማሪ አሉ የሚባሉትን መንገዶች በመጠቀም እንቦጭን መከላከል ያስፈልጋል።
አረሙ ከ12 እስከ 15 ቀን ድረስ እራሱን በእጥፍ አባዝቶ የውሃ አካላትን ያዳርሳል። በመሆኑም አረሙ ካለው የመዛመት ባህሪ አንጻር አንዱን መንገድ ብቻ ተጠቅሞ ማጥፋት ስለማይቻል የቅንጅት ስርዓቶችን መከተል ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ ከነፍሳት ከመጠቀም በተጨማሪ የፈንገስ እና ኬሚካል መከላከያ መንገዶችን በምርምር አዳብሮ መጠቀም ይገባል።
በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የተቀናጀ አቀንጭራ ቁጥጥር ፕሮጀክት አስተባባሪና የእንቦጭ ተመራማሪ ዶክተር ታዬ ተሰማ በበኩላቸው፤ በሳይንሳዊ መንገድ አረሙን ለመከላከል ሁለት አማራጮች ያስፈልጋሉ። አንደኛው «ዊቭልስ» የተባሉ የጥንዚዛ ዝርያዎችን መጠቀም ሲሆን፤ ዊቭልሶቹ በውሃ ውስጥ የሚኖሩ ነፍሳት ናቸው። በምርምር ሲለቀቁ የእንቦጭ አረምን ያቆስሉታል። ተክሉን ሲበሉት እና ሲያቆስሉት ደግሞ በሽታ አምጪ ተዋህሲያን ገብተው በፍጥነት ያደርቁታል።
እንቦጭ በተፈጥሮው የተክሉ የመሃል ክፍል በአየር የተሞላ እና ውሃማ ግንድ ነው። ይህ ክፍሉ በነፍሳቱ በሚበጣበት ወቅት ንፋስ ስለሚገባ እና ስለሚደርቅ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውሃ ውስጥ ይንሳፈፋል። ውሃ ውስጥ ሲንሳፈፍ ደግሞ በቶሎ በስብሶ እድገቱን እንደሚያቆም ያስረዳሉ።
እንደ ረዳት ፕሮፌሰር ጌታቸው ማብራሪያ ከሆነ፤ ችግሩን ለመቀነስ ከነፍሳት አጠቃቀም በተጨማሪ ለአረሙ መስፋፋት የሚረዱ ንጥረ ነገሮች ወደውሃ ውስጥ እንዳይገቡ የሚረዳ መከላከያ ያስፈልጋል። ወደ ውሃው ውስጥ የሚገባውን ንጥረ ነገር መቆጣጣር ለአረሙ እድገት መቀነስ ምክንያት ይሆናል። በተለይ በውሃ አካላት ዳር ያሉ ለእንቦጭ መስፋፋት አመቺ የሆኑ ፎስፈረስ እና ናይትሮጂን የተባሉ ንጥረነገሮች ወደ ውሃው እንዳይገቡ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል። በመሆኑም በውሃ አካላት ዳር ያለውን የአፈር መሸርሸር መከላከል የሚያስችሉ ተክሎችን በብዛት ማብቀል ያስፈልጋል።
በዚህ ሳይንሳዊ አካሄድ የአረሙን እድገት ለመቀነስ በውሃ ዳር ያለውን የአፈር መሸርሸርን መቆጣጠርም ይገባል።
«የተለያዩ የፈንገስ አይነቶች እንቦጭ አረም ላይ ሲደረጉ ቅጠሉን እና ግንዱን ያጠፉታል» የሚሉት ወይዘሮ ብርሃን፤ የፈንገስ ዝርያዎቹ በተለያዩ የአፍሪካ እና አውሮፓ አገራት ላይ ተሞክረው ችግሩን በመከላከል ረገድ ውጤታማ መሆናቸውን ያስረዳሉ። በኬሚካሎችም በተለያዩ ቦታዎች ላይ እንቦጭን ለመቆጣጠር ጥቅም ላይ ውለዋል። በዋናነት «ዲኳፕ፤ ግላይፎሴት እና ቱ ፎር ዲ» የተባሉ የአረም ማጥፊያ ኬሚካሎች አሉ። ለአብነት ታንዛኒያ ውስጥ የተከሰተ የእንቦጭ አረምን ግላይፎሴት የተባለውን ኬሚካል ተጠቅመው 46 ከመቶ ያህሉን ቀንሰውታል። የኬሚካሎቹ ወጪ ከባድ አለመሆኑንም ያስረዳሉ።
እንደ ዶክተር ታዬ ማብራሪያ ከሆነ፤ የኢትዮጵያ አይነት የአየር ንብረት ላለው አገር በተለይ ኒኦከቲና፣ ኤይኮርኒያ እና ኒኦከቲና ብሩቸሂ የተባሉትን የነፍሳት ዝርያዎች መጠቀም ይቻላል። ነፍሳቱ በእንቦጭ ውጪ ሌላ ሰብል እንደማያጠቁ በዩጋንዳ ናይጄሪያ እና አውስትራሊያ እንዲሁም በበርካታ አገራት ተሞክሯል። በዋጋ ረገድም አዋጭ እና ዘላቂነት ያለው መፍትሄ የሚሰጥ የሳይንሳዊ መከላከያ መንገድ ነው።
ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ነፍሳቱ ከመጡ በኋላ በቆሎ እና የተለያዩ 10 እጽዋት ላይ ተሞክሮ የጎንዮሽ ጉዳት እንደማያመጡ ተረጋግጧል። የበለጠ አስተማማኝነቱን ለማረጋጋጥ ግን ተጨማሪ ሙከራ ያስፈልጋል። ይህ ሲባል ግን ብቸኛ ሳይንሳዊ አማራጭ ይሆናሉ ማለት ባለመሆኑ፤ አረሙ ካለው ተዛማጅነት አንጻር እንደየቦታቸው የሚያስፈልጉ የእንቦጭ ማስወገጃ መንገዶችን በተቀናጀ ሁኔታ ጥቅም ላይ ማዋል ያስፈልጋል።
ስነ ህይወታዊ ዘዴው በአሁኑ ወቅት ተመራማሪዎቹ ነፍሳቶቹ እንቦጩን ከጎዱ በኋላ ወደሌሎች ሰብሎች ላይ ስላለመዛመታቸው ምን ማረጋገጫ ይኖራል? የሚለው ጉዳይ አሳስቧቸዋል። ነገርግን ተባዮቹ በቪክቶሪያ ሐይቅም ሆነ በአውስትራሊያ እንዲሁም በሌሎች አገራት ላይ ተሞክረው ምንም ችግር አላመጡም። በኢትዮጵያ የበለጠ እርግጠኛ ለመሆን ተጨማሪ ሳይንሳዊ ፍተሻ አድርጎ ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላል።
የእንቦጭ አረም በኢትዮጵያ በሚገኙ ትላልቅ የውሃ አካላት ላይ ተዛምቷል። ችግሩ በተለይ በጣና ሐይቅ ላይ በርትቷል። የሳተላይት መረጃ እንደሚያመለክተው የጣና ሐይቅን ከ5 እስከ 10 በመቶ ተቆጣጥሮታል። የአማራ ክልል አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ከዓለምአቀፉ ጣናን መልሶ ማቋቋም ማህበርና ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ጣና ላይ ያለውን እንቦጭ በዘላቂነት ለመቆጣጠር የሚረዳ የስነ ህይወታዊ ዘዴ የአተገባበር መመሪያ አዘጋጅቶ ሰሞኑን ማፅደቁ ይታወቃል። ቪክቶሪያ ሐይቅ በአረሙ ሲጠቃ የስነ ህይወታዊ መንገዶችን በተለይም ነፍሳትን እና የተለያዩ ተጓዳኝ አማጮችን በመጠቀም ከ3 እስከ 4 ዓመት ውስጥ መቆጣጠር ተችሏል።
የአረሙን ማጥፊያ ኬሚካሎች ጥቅም ላይ ለማዋል ተጓዳኝ ችግሮች እንዳይኖሩ መመርመር ያስፈልጋል። ጥንቃቄ እና ተገቢ መጠን ያለው አጠቃቀም ያልተከተለ የኬሚካል አጠቃቀም ውሃ አካላትን የመጉዳት እድል ስላለው ዘዴውን በሳይንሳዊ መንገድ ማከናወን ይገባል። እንቦጭ እንዲስፋፋና እንዲያድግ የሚያደርጉ ንጥረ ነገሮች ወደሐይቆች እና ግድቦች እንዳይገቡ መከላከል ካልተቻለ ግን የእንቦጭ አረም መዛመቱ አይቀርም። አሁን በመስፋፋት ላይ ያለው የእንቦጭ አረም በሳይንሳዊ ዘዴ መቆጣጠር ካልተቻለ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጣናን ጨምሮ ሌሎች ውሃማ አካላትን አደጋ ውስጥ መክተቱ የማይቀር ይሆናል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 21/2011
በጌትነት ተስፋማርያም