አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ‹ፕላቲኒየም ኮ ብራድድ› የተሰኘ አዲስ የአየር መንገድ የጉዞ ትኬት የክፍያ መፈጸሚያ ካርድ ሥራ ላይ ማዋላቸውን አስታውቀዋል፡፡
አገልግሎት ላይ የዋለውን ካርድ አስመልክቶ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያምና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንትና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ባጫ ጊና በጋራ ትናንት በስካይላይት ሆቴል በሰጡት መግለጫ ደንበኞች የአየር መንገድ የጉዞ ትኬት ለመግዛት እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም እንደተናገሩት፤ በጋራ የተሰየመው አዲሱ የክፍያ ካርድ ለአየር መንገዱ ደንበኞች ጊዜን በመቆጠብ ከፍተኛ ጠቃሜታ ያስገኛል፡፡
ደንበኞች ባሉበት ቦታ ሆነው መመዝገብ፣ ክፍያ መፈጸም፣ ትኬት መቁረጥና ሌሎች አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ያስችላቸዋል፡፡ ካርዱ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት ከማስቻሉ በተጨማሪም አየር መንገዱ አገልግሎቱን ከወረቀት ነፃ ለማድረግ እያደረገ ያለውንም ጥረት እንደሚያግዝ አስረድተዋል፡፡
እንደ አቶ ተወልደ ማብራሪያ አየር መንገዱ ከዚህ ቀደምም ከንግድ ባንክ ጋር በመሆን የተለያዩ አገልግሎቶችን ሲሰጥ ነበር፡፡ አገልግሎቱን ዲጂታላይዝ ለማድረግ እያደረገ ባለው ጥረት ውስጥ ንግድ ባንክ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ውስጥ የትኬት ሽያጭ 40 በመቶ ዲጂታል ሆኗል፡፡ በ10 ወር ውስጥ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ የትኬት ሽያጭ በዲጂታል መንገድ ተከናውኗል፡፡
የንግድ ባንክ ፕሬዚዳንትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ባጫ ጊና በበኩላቸው፤ አገልግሎቱ በተለይም ሼባ ማይልስ ተጠቃሚዎችን ተደራሽ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡ የካርዱ ተጠቃሚዎች ማበረታቻ እንደሚኖራቸው ጠቁመዋል፡፡
ካርዱ ሰዎች የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያበረታታ መሆኑን የተናገሩት አቶ ባጫ፤ ንግድ ባንክ ከዚህ ቀደም በተለያዩ አገልግሎቶች አሰጣጥ ዙሪያ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት ከፍተኛ ሥራዎችን ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 27/2012
መላኩ ኤሮሴ