አዲስ አበባ፡- በኢህአዴግ ድርጅቶች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት መፍትሄ አግኝቶ አንድ የሚሆኑት ሲዋሀዱ መሆኑን መንግሥት አስታወቀ፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ከትናንት በስቲያ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ በሰጡበት ወቅት የኢህአዴግ ውህደትን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ በአንዳንድ የኢህአዴግ ድርጅቶች መካከል ያለው አለመግባባት የሚፈታውና አንድ የሚሆኑት ሲዋሀዱ ነው ብለዋል፡፡
ውህደቱ እንዲፋጠን የኢህአዴግ እህትና አጋር ድርጅቶች በጋራ እየሰሩ መሆኑን የተናገሩት አቶ ንጉሱ በሀሳብ አለማስማማት የሚወገዝ አይደለም፤ ምክንያታዊ ሙግቶች በድርጅቱ መርህ መሰረት ይስተናገዳሉም ብለዋል፡፡
የኢህአዴግ ውህደት በዓለም ላይ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ልምድ ተቀምሮ ለኢትዮጵያ በሚበጅ መልኩ የተራጀበት፣ ከ10 ዓመት በፊት አጀንዳ የነበረና ኢህአዴግም ሲታገልለት ቆይቶና አቅጣጫ አስቀምጦለት ውሳኔ ያሳለፈበት መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው ሀዋሳ ላይ በተካሄደው 11ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ በተጠናከረ ሁኔታ ውሳኔ የተላለፈበት እንደሆነም አስታውሰዋል፡፡
አንዱ አጋር ተብሎ ተሰይሞ ኢህአዴግ የወሰነውን ውሳኔ ለመፈፀም የሚገደድበት፣ ተፈጭቶ፣ ተቦክቶ እና ተጋግሮ እንካ ብላ ተብሎ የሚሰጥበት እንዲሁም ‘’ኢህአዴግ ምን ይሰጠኝ ይሆን ?’’ ተብሎ የሚጠበቅበት ሂደት እንዲያከትም ውህደቱ ከፍተኛ ሚና እንዳለው አቶ ንጉሱ በመግለጫቸው ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያዊ አንድነት ላልቶ የብሄር ማንነት ላይ ጠንክሮ በመሰራቱ ትውልድ እንደተራራቀ በግምገማ የተደረሰበት እንደነበር አቶ ንጉሱ አስታውሰው ለዚህ ፍቱን መድሀኒቱ ደግሞ የኢህአዴግ ድርጅቶች ውህደትን እውን ማድረግ ነው ብለዋል፡፡
በአንዳንድ አካላት የፓርቲ ውህደት አሀዳዊ ስርዓት የመገንባትና የብሄር ብሄረሰቦችን መብት የመጨፍለቅ ሀሳብ እንደሆነ አድርጎ እየተሰራ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ንጉሱ ይህም ህብረተሰቡ እንዲደናገርና ወደ ግጭት እንዲገባ ለማድረግ የታሰበ እንጂ ሀቁ ውህደቱ ፌዴራላዊ ስርአቱን የሚያጠናክርና ጠንካራ ህብረ ብሄራዊነትን የሚገነባ ነው ብለዋል፡፡
በውህደቱ አለመስማማት ግን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን መጉዳት የለበ ትም ያሉት አቶ ንጉሱ ለትውልድ ቂም በቀልና ቁርሾ የሚያስተላልፍ እንዳይሆን ስምምነት ላይ መድረስ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በኢህአዴግና በአመራር ደረጃ ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ትግል የተደረገው የአንድ ወገን የበላይነት እንዲያከትም ነው፤ የበላይነት እንዲያከትም የተደረገ ትግል ደግሞ የበላይነት እንዲመጣ በፍፁም እድል አይሰጥም፤ የበላይነትን ለማምጣት ህልም ቢኖር እንኳን ኢትዮጵያውያን ይህን የሚሸከም ትከሻ የላቸውም ብለዋል አቶ ንጉሱ በመግለጫቸው::
እኩልነት፣ አንድነት፣ ህብረት፣ መቻቻልና መከባበር ላይ በኢህአዴግ ደረጃ የተግባባንበት፣ በውል የምንረዳውና የምንታገልለት አጀንዳ ነው ያሉት አቶ ንጉሱ በዚህ ረገድ ማንኛውም ህብረተሰብ ስጋት ሊገባው አይገባምም ብለዋል::
ጉዳዩ የፓርቲ ጉዳይ ሆኖ ሳለ አንዳንዶች ወደ ህዝብ በመውሰድና በማደናገር ለግጭት መነሻ የማድረግ አዝማሚያ ሊታረም የሚገባው ነውም ተብሏል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 22/2012
ድልነሳ ምንውየለት