16 ዓመታት ወደኋላ እንመለስ። በ1995 ዓ.ም የታተመው የደራሲ በዕውቀቱ ሥዩም ሥራ የሆነው ‹‹ኗሪ አልባ ጎጆዎች›› የግጥም መድብል ጥቅምት 7 ቀን 1996 ዓ.ም በኢምፔሪያል ሆቴል ተመረቀ። በዚሁ ጥቅምት ወር ውስጥ በ‹‹ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ ንባብና ውይይት ክበብ›› ውይይት ተደረገበት። መጽሐፉ ላይ የተደረገውን ውይይት በዜጋ መጽሔት አምስተኛ ዓመት ቁጥር ሁለት ላይ ተሰንዶ አገኘነው። ‹‹የወሩ ገጣሚ›› በተሰኘው ዓምድ ላይ የጥቅምት ወር ተመራጩ የገጣሚ በዕውቀቱ ሥዩም ሥራ ነበር። በያዝነው ጥቅምት ወር ውስጥ ከመመረቁ ጋር ተያይዞ መጽሃፉን ልንዳስሰው ወደድን።
የበዕውቀቱ ሥዩም ሥራዎች የብዙ ሰዎች የሀሳብ ማስጀመሪያ ናቸው። ጋዜጦችና መጽሔቶች ላይ ልብ ብላችሁ ከሆነ ብዙ ፀሐፊዎች ለሀሳብቸው መግቢያ ይጠቀሙታል። ምክንያታቸው ደግሞ ሀሳባቸውን ስለሚገልጽላቸው ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ጋር ባደረጉት ቃለመጠይቅ የበዕውቀቱ ሥዩም ግጥሞችን እንደሚያደንቁ ተናግረው ነበር።
ብዙ የስነ ጽሑፍ ባለሙያዎች እንደሚሉትም የበዕውቀቱ ግጥሞች ለቋንቋ ቀላል ሆነው ሀሳባቸው ግን ጥልቅ ነው። የብዙ ግጥሞቹ መልዕክትም ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ነው። የአይረሴነት ባህሪ አላቸው። አጫጭር ስለሆኑ ማንም ሰው በቀላሉ በቃል ሊይዛቸው ይችላል። በቃል የመያዛቸው ዕድል የሰፋው ግን በአጫጭርነታቸው ብቻ ሳይሆን ሀሳባዊነታቸው ነው። በበዕውቀቱ የግጥም ሥራዎች ላይም ብዙ የመድረክ ውይይቶች ተደርገዋል።
በጥቅምት ወር 1996 ዓ.ም የታተመችውን ዜጋ መጽሔት ዋቢ አድርገን ከ16 ዓመታት በፊት ወደ ተደረገው ውይይት እንመለስ። በግጥሙ ላይ ሂስ እና የውይይት መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት አቶ ጌታቸው ገዛኸኝ የተባሉ የስነ ጽሑፍ ባለሙያ ናቸው። በዜጋ መጽሔት ላይ የገጣሚው ግለታሪክም ስለተቀመጠ እግረ መንገድ በዕውቀቱ ሥዩምን እናስተዋውቃችሁ። ከመጽሔቱ ሪፖርተር ጋር አውርተው ስለነበር ምናልባት ራሱ በዕውቀቱ ነግሮትም ሊሆን ይችላል።
በዕውቀቱ ሥዩም በጎጃም ክፍለ ሀገር በ1972 ዓ.ም ተወለደ። የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በደብረማርቆስ ተማረ። የከፍተኛ ትምህርቱን ደግሞ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሳይኮሎጂ ተመርቋል። በወቅቱም (በ1996 ዓ.ም) ማለት ነው የኔሽን ጋዜጣ ሪፖርተር እንደነበር ተገልጿል። እንግዲህ በዕውቀቱ ሥዩም ጋዜጠኛም ነበር ማለት ነው።
ለመሆኑ ግጥም ለበዕውቀቱ ምን ይሆን? ለመጽሔቱ ሪፖርተር እንዲህ ብሎት ነበር። ‹‹ዝም ብሎ በቃ የኪነ ጥበብ ስሜት ስላለኝ ይመስለኛል። ሌሎችንም እጽፋለሁ፤ ግጥም ግን ከሌሎች የስነ ጽሑፍ ዘርፎች የተሻለ ቅኔ አዘል ነው ብዬ ስለማስብ፤ እኔም ደግሞ ትንሽ የመቀኘት መንፈስ ካለኝ ልሞክር ብየ ተነሳሁና ተጠቀምኩበት። እኔና ግጥም የተዋወቅነውም ሆነ የተገናኘነው የሆነ ነገር ስሜቴን በነካኝ ቁጥር ያንን ወደ ወረቀት በማስፈር ነው››
በግጥም መድብሉ ላይም ስለግጥም ዘርዘር ያለ ነገር አስቀምጧል። በመጽሐፉ መግቢያ ላይ እንዲህ ይላል።
‹‹ግጥም የሕያው ስሜቶች ምስክርነት ምናባዊ መገለጥ ነው። ግጥም ለአያቶቻችን ከመለኮት ጋር የሚያገናኝ መሰላል፣ ለአባቶቻችን የአብዮትን ሰይፍ የሚስሉበት ሞረድ፣ ለእኛ ደግሞ ፍለጋ (ኅሰሳ) ነው። ግጥም ያልተንዛዛ ለቅሶ፣ ያልቆረፈደ ተረብ፣ ያልተዝረከረከ ፍልስፍና፣ ለገጣሚው ብቻ የተሰጠ መክሊት ነው›› ይላል በዕውቀቱ።
ይህ ገለጻው ራሱ ልክ እንደ ግጥሞቹ ሌላ ስሜትን ይፈጥራል። ለአያቶቻችን ከመለኮት ጋር የሚያገናኝ መሰላል ነው ሲል ምን ማለቱ ይሆን? የበዕውቀቱን አያት ዕድሜያቸውን እንገምት። በአጼው ሥርዓት ዘመን የነበሩ ነው የሚሆን። በዚያ ሥርዓት ውስጥ ሥርዓቱም ሃይማኖታዊ ስለነበር እንጉርጉሮዎችም በዚያው ነው የሚቃኙት። አባቶቻችን ያለው ደግሞ ምናልባት የደርግ ሥርዓትን ይመስላል። ‹‹የአብዮትን ሰይፍ የሚስሉበት ሞረድ›› ማለት እንግዲህ የደርግ ሥርዓትን ይመስላል። እሱ ያለበትን ዘመን ደግሞ (የአሁኑን ሥርዓት ማለት ነው) ፍለጋ (ሀሰሳ) ላይ ያለ ነው ብሏል።
ይህን ለመገመት የሚያግዘን አንድ ነገር አለ። በ2010 ዓ.ም ባሳተመው ‹‹የማለዳ ድባብ›› የግጥም መድብሉ ላይ ሰው ያየውንና የኖረበትን ነው የሚጽፈው ሲል ሀሳቡን አስቀምጧል። ጠዋት ማታ በቡልዶዘር የሚፈርስ ቤት እያየሁ የምጽፈው ነገርም በዚያው ላይ ነው የሚሆን ብሏል።
ወደ ውይይቱ ስንመለስ፤ ሀያሲው ከግጥሙ መግቢያ ጀመሩ። ‹‹ግጥም ለገጣሚ ብቻ የተሰጠ መክሊት እንደሆነ እናምናለን›› የሚለውን አልተቀበሉትም። ምክንያታቸው ደግሞ ግጥም ለገጣሚው ብቻ የተሰጠ መክሊት ሳይሆን ለአንባቢውም የተሰጠ መክሊት ነው የሚል ነው። አንባቢ ግጥም የሚወደው፣ ግጥም አንብቦም የሚረዳው ገጣሚው ውስጥ ያለው ስሜት በአንባቢው ውስጥም ስላለ ነው። ‹‹አንድ የግጥም መጽሐፍ ታትሞ ከአንባቢው ዘንድ ከደረሰ በኋላ የገጣሚው ሚና ያበቃል›› ይላሉ። አንባቢ በራሱ ዜማ የማንበብ፣ በራሱ አረዳድ የመተርጎም መክሊት አለው። ይህን የሚያደርገው ጥበባዊ ስሜት በውስጡ ስላለ ነው።
ሀያሲው አሁንም ከግጥሙ መግቢያ ላይ ሌላ ሀሳብ አንስተው ገጣሚውን ሞግተዋል። ‹‹ገጣሚ በጭብጨባ ብዛት የማይለመልም፤ በእርግማን ብዛት የማይከስም መሆኑን እናምናለን›› ይላል በዕውቀቱ በመግቢያው ላይ። ሀያሲው ደግሞ በጭብጨባ ብዛት ይከስማል የሚል ሙግት አላቸው። የጭብጨባን ተፅዕኖም በሚከተለው ቀልድ አስረድተዋል።
በአንድ አፓርትመንት ውስጥ እሳት ተነሳ። በውስጡ የነበሩ ሰዎችም ፈጥነው በመውጣት ከእሳት አደጋው አመለጡ። ከአፓርታማው የመጨረሻው ፎቅ ላይ ግን አንድት እናት ሕጻን ልጅ ይዘው ነበርና ፈጥነው መውረድ አልቻሉም። እናትም ከራሷ በላይ ለልጇ በማሰብ ‹‹ልጄን አድኑልኝ›› እያለች የድረሱልኝ ጩኸት አሰማች። ከታች ያሉ ሰዎችም አንድ ዘዴ መጣላቸው። በአቅራቢያቸው አንድ ግብ ጠባዊ የእግር ኳስ ተጫዋች ነበርና ተጠራ። እናት ከፎቅ ላይ ሆና ሕጻኑን ልጅ ወደታች እንድትወረውረውና ግብ ጠባቂው ሕጻኑን በአየር ላይ እንዲይዘው ተስማሙ።
እናት ሕጻኑን ልጅ ስትወረውር ግብ ጠባቂው በአየር ላይ ተወርውሮ ሕጻኑን በእቅፉ አስገባ። የአፓርታማውን ዙሪያ የከበበው ህዝብ በጣም ተደሰተ፤ አድናቆቱን በፉጨትና ጭብጨባ ገለጸ። ይህኔ ነው እንግዲህ ጭብጨባ አደጋ ያስከተለው! አድናቆትና ጭብጨባ ያሰከረው ግብ ጠባቂው ያለበት ቦታ ስቴዲየም መሰለው፤ ያቀፈው ልጅም ኳስ መሰለውና በአየር ላይ ወርውሮ በእግሩ ለጋው።
ቀልዱ የተፈጠረም ይሁን እውነተኛ የሚነግረን እውነት ግን የአድናቆትና የጭብጨባ ብዛት እንደሚያሰክር ነው። ይሄን ደግሞ በወቅታዊ ሁኔታዎቻችንም ማስተዋል እንችላለን። በተለይም በማህበራዊ ገጾቻችን ብዙ አድናቂና ተከታይ ያላቸው ሰዎች የሚያደርጉትንና የሚናገሩትን ሁሉ ይስታሉ። ፖለቲከኞችም ምን ቢናገሩ ከፍተኛ ጭብጨባ እንደሚያስገኝላቸው ታሳቢ በማድረግ ልክ ያልሆነ ነገር ይናገራሉ። ሀያሲውም ማለት የፈለጉት ገጣሚ አድናቆትና ጭብጨባ ከበዛበት ይቸገራል ነው። ይሄ ገጣሚ ሄዶ ሄዶ እርግማን ያጋጠመው ዕለት ቅስሙ ሊሰበር ይችላል። በዕውቀቱ ሥዩምም ማለት የፈለገው በጭብጨባ ብዛት ገጣሚነቴ አያድግም፤ በእርግማን ብዛትም ገጣሚነቴ አይቀንስም ነው። እንግዲህ ሀያሲው ደግሞ ተፅዕኖ አለው ብለዋል።
የበዕውቀቱ ሥዩም ግጥሞች አጫጭር ናቸው። አጫጭርነታቸውን በተመለከተ ሀያሲው አንድ ነገር ብለዋል። የገጣሚ ሀብት የሆነውን ቋንቋ እንደልብ እንዳይጠቀም ያደርጋል። ይሄን ነገር ገጣሚው አያምንበትም። ግጥም ማጠርና መርዘሙ የሚያስተላልፈውን መልዕክት እንደማያዛባው በዛፎች ምሳሌ ይሰጣል። ከዛፍ ትልቁ ዋርካ ነው፤ ትንሽ ደግሞ ችፍርግ ነው። እነዚህ ትልቅ እና ትንሽ ዛፎች ፍሬያቸው ቢቆጠር ግን ተመጣጣኝ ነው። ግጥምንም ከዚሁ ጋር ነው የሚያነፃፅረው በዕውቀቱ።
ከሀያሲውም ሆነ ከአስተያየት ሰጪዎች ገጣሚው አምኖ የተቀበላቸው ነገሮችም አሉ። ለምሳሌ ከግጥሞቹ ጋር የቀረቡ ሥዕሎች የግጥሙን መልዕክት ቀድመው ስለሚናገሩ አስፈላጊ አልነበሩም የሚል አስታየት ተሰጥቶት አምኖ ተቀብሏል። ለዚህም ይመስላል ‹‹ኗሪ አልባ ጎጆዎች›› እና ሌሎች ግጥሞችን ይዞ ‹‹ስብስብ ግጥሞች›› በሚል የታተመውና አሁን በገበያ ላይ ያለው ግጥም ሥዕል የለውም። የተሰጠውን አስታየት አምኖበት ነው የተወው ማለት ነው።
ሀያሲው ስለግጥም ሲያብራሩ፤ ግጥም እያደር የሚሞረድ፣ እያደር የሚሻሻል እንደሆነ ተናግረው ነበር። ይሄ ነገር እውነት መሆኑን በበዕውቀቱ ሥዩም አንድ ግጥም ላይ ማየት እንችላለን። በፌስቡክ ገጹ ላይ የጻፈው አንድ ግጥም በ2008 ዓ.ም ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጄንሲ በራሱ በበዕውቀቱ መጽሐፍ ላይ በተደረገ ውይይት ተነስቶ ነበር። ያ ፌስቡክ ገጹ ላይ የጻፈው ግጥም በ2010 ዓ.ም ባሳተመው የግጥም መጽሐፍ ውስጥ ግን አንደኛው ስንኝ ተቀይሯል። ግጥሙ ይህ ነበር።
እንደ አገው ጃንጥላ ሰማይ ተሽከርክሮ
እንደ ጎፋ ፈረስ መሬቱ ደንብሮ
ሁሉ ሲያዳልጠኝ፤ ሁሉ ሲያዳክመኝ
ቀሚስሽን ይዤ መትረፌ ገረመኝ
‹‹የማለዳ ድባብ›› የግጥም መድብሉ ላይ ግን ‹‹እንደ ጎፋ ፈረስ›› የሚለው ‹‹እንደ አይናፋር ፈረስ›› በሚል ተቀይሯል። ምናልባት ግን ‹‹እንደ አይናፋር ፈረስ›› የሚለው የበለጠ ገላጭ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም መሬት ዞረብኝ ለማለት የአይናፋር ፈረስ መደንበር ሊቀርበው ይችላል። ‹‹እንደ ጎፋ ፈረስ›› የሚለው ደግሞ ከላይ ‹‹እንደ አገው ጃንጥላ›› ስላለ አካባቢዎች በሚታወቁበት ማድረጉ ነው። የአገው ባህላዊ ዘፈን ውስጥ ጃንጥላ ሲሽከረከር ይታያል፤ የጎፋ ፈረስ ሲባልም ይሰማል። በእነዚህ መጠቀሙ ነው።
የበዕውቀቱ ግጥሞች ባልጠበቅነው መንገድ የሚጠናቀቁም ናቸው። ‹‹አዳም እና ጥበቡ›› በሚለው ተከታዩ ግጥም እንሰናበት።
በመጀመሪያ አዳም ሳተ
ከገነትም ተጎተተ
አዳም ከገነት ሲባረር
እነሆ እርቃኑን ነበር።
ብርዱ፣ ውርጩ አንዘፈዘፈው
ዶፉ፣ ጠሉ ወረደበት
ያንዠረገገውን አይተው
አእዋፍ አራዊት ሳቁበት
ይሄኔ አዳም ተማረረ
ተማረረና ተመራመረ
ተመራምሮም አልቀረ
ጋቢ መስራት ጀመረ
ጅማሬውን ወደደ
ተጀምሮ እስኪፈጠም
የእድሜውን ግማሽ ወሰደ
ያሳዝናል!
ጋቢውን ጨርሶ ሲቋጭ
ገላው ብርዱን ለመደ።
አዲስ ዘመን ጥቅምት22/2012
ዋለልኝ አየለ