አፋር የሰው ዘር መገኛ መሆኗ ዓለም አቀፍ ሃቅ ስለሆነ እንተወው! ‹‹የቅርብ ጸበል ልጥ ይራስበታል›› እንዲሉ አበው፤ የራሳችን የሆኑ ነገሮችን ግን ብዙም ትኩረት አንሰጣቸውም፡፡ እዚህ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ‹‹ከቢሮ እስከ ሀገር የትውልድ አሻራ›› በተሰኘው ዘጋቢ ፊልም ላይ የተናገሩት አንድ ሀሳብ ትዝ አለኝ፡፡ በአገራችን ውስጥ ብዙም የተለመደ ስላልሆነ እና የቤተሰብም አቅም ስለማይፈቅድ ከልጅነታቸው ጀምሮ ትልቅ ሆቴል ውስጥ ገብተው አያውቁም ነበር:: በወታደርነታቸው ሩዋንዳ እንደሄዱ ግን ሆቴል አዩ፤ በዚያ ሆቴል በጣም ተገረሙ፡፡
አገራቸው ውስጥ እንደዚያ አይነት ሆቴል ባለመኖሩ ቅናት ተሰማቸው:: ወደ አገራቸው ሲመለሱ ግን እነ ሂልተን እና እነ ግዮን ሆቴል ሩዋንዳ ውስጥ ከቀኑበት ሆቴል ይበልጡ ነበር፤ ችግሩ አይተዋቸው አያውቁም ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እያሉ አይተዋቸው ስለማያውቁ እንደዚያ አይነት ሆቴል ያለ አልመሰላቸውም ነበር፡፡
ቀጥሎም ሌላ ነገር ተናገሩ፡፡ ላሊበላን አይቶ የማያውቅ ኢትዮጵያዊ፤ ቻይና ውስጥ ባለ ሕንጻ ይገረማል፤ አክሱምን እና ፋሲል ግንብን አይቶ የማያውቅ ኢትዮጵያዊ አውሮፓ እና አሜሪካ ውስጥ ባየው ጥበብ ይገረማል፡፡ ብዙ ኢትዮጵያዊ የባሌን አስደናቂ ተፈጥሮ አያውቅም፤ ሌላ አገር ያለ ተፈጥሮን ግን ያደንቃል፡፡ እነዚህን ሀብቶቻችንን የሚያደንቃቸው ፈረንጅ ነው፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ገጠመኝ ያነሳሁት ከጉዳያችን ጋር ስለሚገናኝ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ መሆኗን ከእኛ ከባለቤቶች በላይ አውሮፓውያን ይገረሙበታል፡፡ዜናውን የሚነግሩን የምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃን ናቸው፡፡ ዘጋቢ ፊልም ሰርተው የሚያሳዩን እነርሱ ናቸው:: አለማፈራችን ደግሞ እነርሱን ምንጭ አድርገን እኛ እንሰራለን (በእርግጥ ከመተው ይሻላል)፡፡
አፋር የሰው ዘር መገኛ መሆኗ ዓለም አቀፍ ሃቅ ሆኖልናል፡፡ ለመሆኑ የሰው ዘር መገኛ እንደመሆኗ የሰው ልጅ ባህሪያትስ በአፋር ፍንትው ብለው እንደሚታዩ ልብ ብለነው ይሆን? የሰው ልጅ ባህሪ ምንድነው? ብዙም ሳይንሳዊ ትንታኔ አይጠይቀንም፤ የሰው ልጅ ከእንስሳት ከሚለይባቸው ባህሪያት አንዱ አሳቢ እና ተግባቦታዊ መሆኑ ነው፡፡ ከፍጥረታት ሁሉ በቋንቋ የሚግባባ የሰው ልጅ ነው፡፡ በቋንቋ ተግባቦት ውስጥ ደግሞ ብዙ አይነት መስተጋብር አለ፡፡ እንግዲህ ለዚህ የተግባቦት መነሻነት አፋር ምስክራችን ነው፡፡
በአፋር ውስጥ ‹‹ዳጉ›› የሚባል ነገር አለ፡፡ በዘመንኛው እንግለጸውና ለአፋሮች ዳጉ ማለት ሰበር ዜና የሚነገርበት ሬዲዮ ወይም ቴሌቭዥን ማለት ነው:: አፋሮች ይህን የዳጉ ሥርዓት ሲፈጥሩ ሬዲዮ ወይም ቴሌቭዥን የሚባል ነገር ፈጽሞ አይታወቅም ነበር:: ማንም ዓለም ስለመገናኛ ብዙኃን ሳያወራ እነርሱ ዜናን በዳጉ ይለዋወጡ ነበር፡፡ ለዚያውም እንደ ዘመኑ የመገናኛ ብዙኃን የአሰራር ውጣ ውረድ የሌለበት!
በዳጉ ዜና ለመለዋወጥ ሬዲዮ ወይም ቴሌቭዥን መክፈት አያስፈልግም፡፡ መብራት መጣ ሄደ አያስጨንቅም፡፡ መቅረጸ ድምጽና ካሜራ ፍለጋ መድከም አያስፈልግም፡፡ ማን ዜና ያንብብ ተብሎ አይመረጥም:: ይሄ ይለፍ ይሄ ይቆረጥ የሚባል የአርታኢ (ኤዲተር) ውጣ ውረድ የለም! በቃ! በዳጉ እያንዳንዱ ሰው ጋዜጠኛ ነው:: ዛሬ በማህበራዊ ገጾች ሁሉም ሰው ጋዜጠኛ ከመሆኑ ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት አፋር ውስጥ ሁሉም ጋዜጠኛ ነበር፡፡
ይህን የአፋሮቹን የመረጃ መለዋወጫ ዳጉ ከዘመናዊው ጋር ስናነፃፅረው ምነው ሁሉም በዳጉ ቢተዳደር ያሰኛል:: በዳጉ ፈጽሞ የአሉቧልታ ወሬ አይሰራጭም፡፡ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በአንድ ወቅት ከነዋሪዎቹ ጋር ባደረገው ቆይታ እንደተናገሩት፤ ውሸት የተናገረ ሰው ካለ በዳጉ ህግ ይቀጣል፡፡ ከማህበረሰቡ ይገለላል:: ከማህበረሰቡ ተገለለ ማለት ከባድ ቅጣት ነው፡፡ ይህን በመፍራት ማንም ሰው የውሸት መረጃ አያሰራጭም፡፡
እንግዲህ ይሄን ነገር ከሬዲዮና ቴሌቭዥን ጣቢያዎች ጋር አነፃፅሩት፡፡ ህዝባዊ ኃላፊነት ያለባቸው መገናኛ ብዙኃን የአሉቧልታ ወሬ ሲያስተጋቡ በዳጉ ግን ይሄ ፈፅሞ አይደረግም፡፡ የዳጉ መረጃዎችም ተጨባጭና የአይን እማኞች ናቸው፡፡ በቀጥታ ያዩትን እና የሰሙትን ነው፡፡ አንደኛ ደረጃ የመረጃ ምንጭ የሚባለው ማለት ነው፡፡ በነገራችን ላይ ዘመን የወለዳቸው ድረ ገጾችና መገናኛ ብዙኃን የዳጉን አሰራር እያበላሸባቸው እንደሆነ ነዋሪዎች ሲናገሩ ነበር፡፡
የአፋር ማህበረሰብ የትኛውንም መረጃ የሚለዋወጠው በዳጉ ነው፡፡ የገበያ ዋጋ፣ የሰላም ሁኔታ፣ የማህበረሰቡ ጤንነት… በአጠቃላይ በአካባቢ የተፈጠረ ሁነት የሚነገረው በዳጉ ነው፡፡ አንድ ቦታ ላይ የተፈጠረ ሁነት በብርሃን ፍጥነት ነው ከጫፍ እስከ ጫፍ የሚዳረሰው፤ ለዚያውም ሳይዛባ እና ሳይጓደል፡፡ ጠዋት ሲገናኙ ከሰላምታ በፊት መረጃ ነው የሚለዋወጡት፡፡ መንገድ ላይ የተገናኘ አፋር ሁሉ በውሎ አዳሩ ያየውንና ያጋጠመውን ሁሉ ይናገራል፡፡ በቃ እያንዳንዱ ሰው ዜና ይዞ ነው የሚሄደው፡፡
እንግዲህ አፋር የሰው ዘር መገኛ ብቻ ሳይሆን የተግባቦት (ኮምኒኬሽን) መገኛም ነው ማለት ነው:: ምክንያቱም ይህ አይነት የመረጃ ልውውጥ ከጥንት ጀምሮ ሲጠቀሙበት የኖረ ነው፡፡ ሌሎች የአፋር ማህበረሰብ ማህበራዊ ጥበቦችን እንይ፡፡
የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን በ2009 ዓ.ም የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችን ማህበራዊ ክንዋኔዎችና ሥነ ሥርዓቶች የያዘ መጽሐፍ ለንባብ አብቅቷል:: ከመጽሐፉ ውስጥ ‹‹የአፋር ብሄረሰብ ማህበራዊ ክንዋኔዎችና ስነ ሥርዓቶች ከፊል ገጽታ›› የሚል ይገኝበታል፡፡ መጽሐፉ፤ ስለአፋር ታሪካዊ ዳራ፣ ባህላዊ አስተዳደር፣ የዳኝነት ሂደትና የቅጣት አይነቶች፣ ባህላዊ ጭፈራዎች፣ የጋብቻ አይነቶችና ፍቺ፣ ስም አወጣጥ፣ ግርዛት፣ ለቅሶ እና የቀብር ሥነ ሥርዓት በዝርዝር ይነግረናል፡፡
አፋር በባህላዊ አስተዳደር በሚኖርበት ዘመን መሪውን የሚመርጥበት መስፈርት፤ ጥበብ፣ ተቀባይነት፣ አስተዋይነት፣ ታዋቂነት እና ችሎታ የግዴታ ነበሩ:: መሪውም እንደ በዓላት በመሳሰሉ ዝግጅቶች ላይ በመገኘት ከህዝቡ ጋር ይገናኛል፡፡ መሪያቸውም ሱልጣን ይሰኝ ነበር፡፡ እንግዲህ ይሄ የአፋር ባህላዊ የአስተዳደር ሥርዓት የዴሞክራሲ ፈጣሪ ናቸው ከሚባሉት አገሮች ቀድሞ የተፈጠረ ነበር ማለት ነው፡፡ መሪ የሚመርጡበት መስፈርት ዛሬ ላይ የዴሞክራሲ ዘመን በሚባለው እንኳን የማይተገበር ነው ማለት ነው፤ ብቃትንና ችሎታን መሰረት ያደረገ!
ዛሬ ላይ ‹‹ማህበር፣ ሊግ፣ ፓርቲ…›› የሚባሉ ነገሮች ከመኖራቸው በፊት አፋር ውስጥ የተለያዩ ማህበራዊ ሁነቶች የሚከወኑባቸው ሥርዓቶች ነበሩ፡፡ ከእነዚህም አንዱ ‹‹ፋኢማ›› የሚባለው ነው፡፡ ፋኢማ ማለት የወጣት ወንዶችና ሴቶች አደረጃጀት ነው፤ የወጣቶች ማህበር እንደማለት ነው፡፡
ፋኢማዎች የራሳቸው መሪ አላቸው፡፡ እነዚህ ፋኢማዎች የማህበረሰቡ ወግና ባህል እንዳይጣስ ኃላፊነት አለባቸው፤ ጥሶ የተገኘንም በመተዳደሪያቸው መሰረት ይቀጣሉ፤ ይገስጻሉ፡፡ የሽማግሌዎችን ውሳኔ ያስፈጽማሉ:: በአካባቢው ጥፋተኛ ካለ ተይዞ ወደ ሽማግሌዎች የሚቀርበው በፋኢማዎች በኩል ነው፡፡
የወንጀል መቅጫ ህጎቻቸውም ዘመናዊው ከመኖሩ በፊት የነበሩ ናቸው፡፡ ምናልባት ከዘመናዊው ጋር የሚመሳሰሉና የማይመሳሰሉ ሊኖሩ ቢችሉም ግን የአፋር ማህበረሰብ በባህላዊ አስተዳደር ዘመኑ የቀመራቸው አሰራሮች ነበሩት፡፡ ለምሳሌ ሕጻን ልጅ የገደለ ሁለት ሰው እንደገደለ ተደርጎ ነው የሚቀጣው:: የግድያ ወንጀሉ ሳይታሰብ (ድንገተኛ) ከሆነም የቅጣት መጠኑ ቀለል ያለ ይሆናል፡፡ ድርጊቱ በአላህ ትዕዛዝ እንደተፈጸመ ስለሚቆጠር ሰውየውን መቅጣት ሀራም ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ አስገድዶ መድፈር ደግሞ ቅጣቱ ከግድያ ቅጣት ጋር እኩል ነው፡፡
እንግዲህ በማህበራዊ አኗኗርም፣ በአስተዳደራዊ ሥርዓትም፣ በመረጃ ለውውጥ ሥርዓትም የአፋር ማህበረሰብ ቀድሞ የሰለጠነ ነበር ማለት ነው፡፡ ብዙ ዘመናዊ ነገሮችንና አሰራሮችን ስናይ መነሻቸው ሁሉ አፋር ይመስላል፡፡ ለዚያውም በሰለጠነ እና ሥርዓቱን በጠበቀ መንገድ የሚተገበር ማህበራዊ መስተጋብር ያዳበሩ ናቸው፡፡ በመዝናኛውና በባህላዊ ክዋኔዎችም ካየን እንደዚሁ ነው፡፡
በአፋር ባህላዊ ጨዋታ ወንዶችና ሴቶች የተለያዩ ጨዋታዎችን ይጫወታሉ፡፡ ‹‹ካሶው›› የሚባለው ጭፈራ ወንዶች የሚጫወቱት ሲሆን ክብ ሰርተው በሰርግ ወይም በጾም መፍቻ ጊዜ የሚጫወቱት ነው:: በዚህ ጨዋታ ውስጥ ሌሎች ታዳሚዎች በእልልታና በጭብጨባ ያጅባሉ፡፡
‹‹ሰደአ›› ደግሞ ሴቶችም ወንዶችም ማታ ማታ አንድ ላይ ሆነው የሚጫወቱት ነው፡፡ ወንዶች እና ሴቶች በረድፍ ሆነው ክብ በመሥራት አንዴ ወደፊት አንዴ ወደኋላ እያሉ የሚጫወቱት ነው፡፡ ሴቶች ብቻቸውን ሆነው የሚጫወቱት ከሆነም የሴቶች ሰደአ ይባላል፡፡ በዚህ ጊዜም ወንድሞቻቸውን፣ ጀግኖቻቸውን፣ ጎሳቸውን እና የቤት እንስሶቻቸውን የሚያወድሱ ሲሆን ወንዶች ታዳሚ ብቻ ይሆናሉ፡፡
ሌላው የአፋር ባህላዊ ጨዋታ ‹‹ትርትራ›› የሚባለው ነው፡፡ ትርትራ ሽለላ እና ፉከራ እንደማለት ነው፡፡ ወደ ጦር ሜዳ ለመሄድ ሲነሱ እና በጀግንነት ለሚታወቁ ሰዎች የሚከወን ነው፡፡ አከዋወኑም አካላዊ እንቅስቃሴ ያለው ነው፡፡ አደገኛና አስፈሪ የሆኑ የዱር እንስሳትን ገድለው ሲመጡ ቤት አካባቢ ሲደርሱም ይፎክራሉ፡፡
ባህላዊ ጨዋታዎችና ስነ ቃሎች በሁሉም አካባቢ ይኖር ይሆናል፤ የዳጉ ነገር ግን አስደናቂና በአፋር ብቻ የሚተገበር ነው፡፡ የባህላዊ አስተዳደር ሥርዓታቸውም ከሌላው አካባቢ ለየት ያለ ነው፡፡ እንግዲህ እነዚህ ነገሮች ለአፋር የሰው ልጅ መገኛነት ተጨማሪ ምስክሮች ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ ዛሬ ላይ ውስብስብ የቴክኖሎጂ መረቦች ቢኖሩም ከእነዚህ የቴክኖሎጂ ውጤት መፈጠር በፊት ግን አፋር እንዲህ አይነት የተግባቦት ሥርዓት ነበረው፡፡
እንዳለመታደል ሆኖ ግን የራሳችን ለሆነ ነገር ትኩረት አንሰጥም፡፡ ጠዋት ማታ የአሉቧልታ ዜናዎች የሚያሰራጩ ማህበራዊ ገጾች በየሬዲዮ ጣቢያው ብዙ ይወራላቸዋል፤ ስለፈረንጆች የውሻ ሰርግና የድመት አልጋ ላይ መተኛት ጠዋት ማታ የሚያደነቁሩን የአገራችን የመገናኛ ብዙኃን ስለዳጉ ግን የሚያውቁም አይመስሉም፡፡ እስኪ ዳጉ ላይ በምሁራን ስንት ጥናት ተሰርቷል? በመገናኛ ብዙኃን ስንት ፕሮግራም ተሰርቷል? እንዲህ አይነት የሥልጣኔ መነሻ ሀብቶቻችንን ልናስተዋውቅ ይገባል!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 15/2012
ዋለልኝ አየለ