አዲስ አበባ፡- የማንጎ “ዋይት እስኬል” ተባይን ለመከላከል የሚሠራው ሥራ አመርቂ ባለመሆኑ በሽታውን ማዳን አለመቻሉንና ዘላቂ መፍትሔ እንደሚፈልግ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ገለፀ፡፡
የቢሮ ኃላፊው አቶ ሙሳ አህመድ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፤ ግብርና ሚኒስቴር፣ የግብርናና እርሻ ምርምር ማዕከላት፣ በቋሚና ዓመታዊ ሰብሎች ከሚመራመሩ ተቋማት መፍትሔ እንፈልጋለን፡፡ እስከአሁን የተደረጉ ሙከራዎችም ውጤት አላስገኙም ብለዋል፡፡
ማንጎ የክልሉ አርሶ አደር ለምግብ ፍጆታ የሚጠቀምበትና የገቢ ምንጩም ነው ያሉት አቶ ሙሳ፤ የተከሰተው በሽታ ምርቱን ቢቀንሰውም ችግሩን ለመከላከል የሚሠራው ሥራ ግን አመርቂ ባለመሆኑና በንፋስ ስለሚተላለፍ ለዘላቂ መፍትሔ የተቀናጀ ትግበራ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ በዘመናዊ መንገድ የበቀሉና አጫጭር ቢሆኑ ኖሮ በርጭት ለመከላከል ይቻል ነበር፡፡ በባህላዊ መንገድ የሚመረት እና ቁመታቸው ረጃጅም መሆኑ የመከላከል ሥራውን አዳጋች ያደረገው ሲሆን አገር ውስጥ ያሉ ተመራማሪዎችና ተቋማት ትኩረት ማነስ ለችግሩ መባባስ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት እንደ ጊዜያዊ መፍትሔ በበሽታው የተጠቃ የማንጎ ግንድ እየቆረጠ ወደሌላው እንዳይተላለፍ ማድረግ ሲሆን በቀጣይም የኬሚካል ርጭት ለማድረግ ተጽዕኖውን ግምት ውስጥ በማስገባት የሚመለከታቸውን አካላት በማሳተፍ ውይይት ለማድረግ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡
በአንድ ክልል አቅም ብቻ ችግሩ እንደማይፈታና የሚመለከታቸው አካላት እንዲረባረቡም አቶ ሙሳ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሰብል ጥበቃ ምርምር ዳይሬክተሩ ዶክተር መሐመድ ዩሱፍ፤ በሽታው የማይታወቅ በመሆኑ በትግበራ አመርቂ ውጤት በአንድ ጊዜ ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን ተናግረው ሆኖም ስነ ህይወታዊ ጥናት በማድረግ፣ በባዮሎጂካል (ተባይን በተባይ) ለመቆጣጠር የተጀመሩ ሥራዎች መኖራቸውንም ገልፀዋል፡፡
ተባዩን ሙሉ ለሙሉ በቀላሉ ማጥፋት የማይቻል መሆኑን አመልክተው፤ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እንዳያስከትል መቆጣጠር የሚቻልበትን ሥራ መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
እንደ ዶክተር መሐመድ ገለፃ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት፤ ረጃጅም ተክሎችን በተሻሻሉ የማንጎ ዝርያዎች መቀየር፣ አርሶ አደሮችን ማሰልጠን፣ ምርምሮችና የአርሶ አደር ማሰልጠኛ ተቋማት በጋራ መሥራት እንደሚገባቸው፣ ኬሚካሉንና ሌሎች አማራጮችን መጠቀም እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል፡፡
ሊረጩ የሚችሉ ኬሚካሎች ቢኖሩም፤ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማንጎ ዛፍ ትላልቅ በመሆናቸው በአነስተኛ አርሶ አደር አቅም ለርጭት አስቸጋሪ መሆኑን አመልክተው በአሠራር ዘዴ መከላከል የሚደረስበት ከሆነ ዛፎቹ ላይ ኬሚካሉን መርጨት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩልም ተባዩ ሲያጠቃው የሚረግፈውን ቅጠል ማቃጠልም የችግሩ መቀነሻ መንገድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በባዮሎጂካል (ተባይን በተባይ መቆጣጠር) የሚቻልበትን መንገድ ከደቡብ አፍሪካ ቴክኖሎጂውን ለማስገባት ድርድር እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
የማንጎ “ዋይት እስኬል” ተባይ መጀመሪያ የታየው ወለጋ ውስጥ ሲሆን፤ ምንጩ በማንጎ ልማት የተሰማሩ የውጭ አገር ባለሀብቶች የተከሉት ችግኝ ሊሆን እንደሚችል የሚገመት ሲሆን ችግሩ ከ2002 ዓ.ም በኋላ ከሱማሌና ከአፋር ክልሎች በስተቀር በሁሉም ክልሎች መታየቱ ይነገራል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2012
ዘላለም ግዛው