በዳግማዊ አጼ ምኒልክ / ታላቁ / ቤተ መንግስት ቅጥር ግቢ ውስጥ የተሰራው ‹‹አንድነት ፓርክ›› በቅርቡ ተመርቆ ለጎብኚዎች ክፍት ተደርጓል።ፓርኩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዳለው በመጥቀስ ለማስተዋወቅ ስራ ትኩረት መስጠት እንደሚገባም የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አምባሳደር ጥሩነህ ዜና፤‹‹በአሁኑ ወቅት በርካታ ቱሪስቶች ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ፤ነገር ግን በአዲስ አበባ ያን ያህል ሳቢ ሁኔታዎች የሉም›› ሲሉ ይገልጻሉ።ይህ ፓርክ ይህን ክፍተት የሚያጠብና አኮኖሚያዊ አስተዋፅኦ የሚያበረክትም ነው ይላሉ።
እንደ አምባሳደር ጥሩነህ ገለጻ፤የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚያጓጉዛቸው መንገደኞች ቁጥር በጣም እየተበራከተ መጥቷል።መንገደኞቹ ወደ አገሪቱ የሚመጡና ወደ ሌሎች ሀገሮች የሚጓዙ /ትራንዚት የሚያደርጉ/።አየር መንገዱ በአማካይ አንድ ሚሊዮን መንገደኞችን የሚያጓጉዝ ቢሆን ፣አንዱ መንገደኛ በከተማዋ ውስጥ አንድ ቀን እንኳ ቢያድርና አስር ብር ቢያወጣ ብዙ ሚሊዮን ብር ማግኘት ይቻላል።
‹‹አገሪቱ የአፍሪካም መዲና ናት፤የአህጉሪቱም ሆኑ ዓለም አቀፍ ታላላቅ ስብሰባዎች ይደረጉባታል።›› የሚሉት አምባሳደር ጥሩነህ፣የጉባኤው ታዳሚዎች አንዳንዴ የሚሄዱበት ስፍራ እንደሚያጡ ያመለክታሉ።ይህ ፓርክ ሌላ አንድ አማራጭ ሆኖ መምጣቱ የታዳሚው መዳረሻ እንደሚሆንና ለኢኮኖሚውም የራሱን ሚና እንደሚጫወት ይናገራሉ።
‹‹ኢትዮጵያውያን እንደምናስበው አይደለም የውጭ አገር ሰዎች የሚያስቡት።እኛ ከበላንና ከጠጣን እምብዛም ችግር የለብንም፤ እነርሱ ግን ከእኛ ይለያሉ።›› ያሉት አምባሳደር ጥሩነህ፣ፈረንጅ በመብላት ብቻ ላይ እንደማይወሰን ያብራራሉ። ‹‹አሁን ያሉን ሆቴሎች ጠባቦች ናቸው፤የዋና ቦታውም እንዲዚያው ነው።
‹‹ፈረስ መጋለቢያ እንዲሁም ጎልፍ መጫወቻ ቦታዎችም የሉም።በመሆኑም የሚጎበኝ ማብዛት አለብን።››ብለዋል።ፓርኩ ለአገር ውስጥ ጎብኚም ታሪኩን እየተረዳ በኢኮኖሚውም የበኩሉን አስተዋፅኦ ማድረግ የሚችልበት ሁኔታ እንዲኖር እንደሚያስችል ይገልጻሉ።
እንደ አምባሳደሩ ገለጻ፤ፓርኩ የታሰበለትን የኢኮኖሚ ፋይዳ እንዲያመጣ በማስተዋወቁ በኩል ብዙ ሊሰሩ ይገባል። ምክንያቱም አንድን እቃ ማምረት አንድ ነገር ሲሆን፤መሸጥ ደግሞ ሌላ ነገር ነው።የተመረተን እቃ ለመሸጥ ራሱን የቻለ እውቀት ይጠይቃል።የፓርኩ መስራት በራሱ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አያስገኝምና።ስለዚህም ፓርኩ በአግባቡ እንዲጎበኝ ለኮንፈረንስ ወደ አገሪቱ ለሚመጣው ታዳሚ ስለፓርኩ ማሳወቅ ይገባል።እዚህ ላይ የአስተዋዋቂውን ችሎታ የሚጠይቅ ነገር አለ።
ሌላው የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ዶክተር ጉቱ ቴሶ፣ ፓርኩ ኢትዮጵያ ባሏት መስህቦች ላይ የመጣ ተጨማሪ መስህብ መሆኑን ይጠቅሳሉ።በግቢው ውስጥ የኢትዮጵያን ታሪክ እንዲያሳዩ በሚል የተደረጉ ግንባታዎችና የመሳሰሉት ነገሮች የአገር ውስጡም ሆነ የውጭ አገር ዜጎች ለመጎብኘት ጉጉት እንደሚፈጥሩባቸው ይጠቁማሉ። ፓርኩ ከሌሎች ቦታዎች ይልቅ የበለጠ ጉብኚዎችን ሊያገኝ እንደሚችልም ያመለክታሉ።
ዶክተር ጉቱ የአምባሳደር ጥሩነህን ሃሳብ በማጠናከር የውጭ አገር ጎብኚዎችን ለመሳብ የማስተዋወቅ ስራ ሊሰራ እንደሚገባ ይጠቁማሉ። ከተለያዩ አህጉራት ወደ አገሪቱ የሚመጣውን መንገደኛም ሆነ የአገሪቱን ሌላኛውን ክፍል ለመጎብኘት የሚመጣው ቱሪስት በመዲናይቱ በሚያርፍበት ጊዜ ሊጎበኛቸው ከሚችላቸው መካከል አንዱ ሊሆን እንደሚችልም ይናገራሉ።
ለሚቀጥለው አንድ ዓመት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ብቻ እንዲጎበኙት ቢደረግ ከፍተኛ ገቢ ሊያስገኝ እንደሚችል ጠቅሰው፤ይህም ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ጉልህ መሆኑን ያመለክታል ሲሉ ያብራራሉ።
ዶክተር ጉቱ፣‹‹ማስተዋወቁ ባለቤት ኖሮት ስራዬ ነው ብሎ የሚሰራ ከሆነ በእርግጥም በተለይ ፈረንጆችን አንድ ሁለት ቀን አሳድሮ ትራንዚት ማስደረግ ይቻላል።ይህ መሆኑ ደግሞ የሚጎበኘውን ቦታ አይተው ብቻ እንዲሄዱ አያደርግም፤ከማደሪያ ጀምሮ ለሚበሉትና ለሚጠጡት ሁሉ እንዲከፍሉ ያስደርጋቸዋል።የሚገበያዩት በብር ሳይሆን በዶላር ነው።በመሆኑም በማስተዋወቁ ላይ ጠንከር ያለ ስራ ሊሰራ ይገባል።››ሲሉ ያስገነዝባሉ።
የአንድነት ፓርክ ዳይሬክተር ዶክተር ታምራት ኃይሌም የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎቹን ሃሳብ በማጠናከር ፓርኩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዳለው ያመለክታሉ።ቀጥተኛ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ጎብኚው ገንዘብ ከፍሎ በመግባት ሲጎበኝ የሚያስገኘው ገቢ መሆኑን ጠቅሰው፤ተዘዋዋሪ በሆነ መንገድ የሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ደግሞ ፓርኩን ለመጎብኘት ሰዎች ከተለያየ ቦታ በሚመጡበት ወቅት ወደ ፓርኩ እስከሚደርሱ ለትራንስፖርት፣ለሆቴል እንዲሁም ለምግብና መሰል ጉዳዮች ሲያወጡ የሚያስገኙት ነው ሲሉ ያብራራሉ።
ዳይሬክተሩ በማስተዋወቁ በኩል በመገናኛ ብዙሃን እንዲሁም በድረ ገፅ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ይጠቁማሉ።በጉብኝቱ ወቅት የሚሰጠው መልካም አገልግሎት ከምንም በላይ ዋናው የማስተዋወቅ ስራ ሊሆን እንደሚችልም ያመለክታሉ።
‹‹የውጭ አገር ጎብኚዎች ለዚህ ፓርክ ብለው ሊመጡ ይችላሉ፤ኤምባሲዎችም ጥያቄ እያቀረቡልን ናቸው።››ያሉት ዶክተር ታምራት፣ይህ ፓርክ በመጨመር ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣውን ጎብኚ ጉጉት ጨምረናል።ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋርም እየተነጋገር ነን።››ብለዋል።
ታላቁ ቤተመንግስት በዳግማዊ አጼ ምኒልክና በባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ በ1878 ዓ.ም.የተመሰረተ ሲሆን፤በ40 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።ከ40 ሄክታሩ በ13ቱ ላይ ነው ፓርኩ ያረፈው።የቤተ መንግስት ሙዚየሞች በተለያዩ የዓለም ክፍል እንዳሉ ይታወቃል።ይህ የኢትዮጵያ ግን ከቤተ መንግስት ሙዚየምነት በተጨማሪ የተለያዩ ነገሮችን አንድ ላይ አቅፎ ነው የያዘው። ወደ ስድስት መስህቦች ያሉት ሲሆን፣ታካሪዊ፣ባህላዊና ተፈጥሯዊ መስህቦችንም ያካተተ ነው።
በፓርኩ ለእንስሳት በተዘጋጀው ስፍራ በታህሳስና ጥር ላይ 46 ዝርያዎች ያላቸው ወደ 300 የሚሆኑ እንስሳት እንደሚገቡ ይጠበቃል።በዚህም ፓርኩ ብዝሃነት ያለው ይሆናል ተብሎ ይታመናል።ፓርኩ በቀን በአማካይ ከአንድ ሺ ሰው በላይ እየጎበኘው ሲሆን፤ከትናንት በስቲያ ብቻ ከሁለት ሺ ሰው በላይ ጎብኝቶታል።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎቹ እንደሚናገሩት፤ ከፓርኩ የሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ሰፊ እንደመሆኑ ፓርኩን በተለያየ መልኩ በማስተዋወቅ ተጠቃሚነትን ማጎልበት ይገባል።በስፋት የሚጎበኝበትን መንገድ በማመቻቸትም ጎብኚዎቹ የፓርኩ አስተዋዋቂ ጭምር እንዲሆኑ መሰራት ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 11/2012
አስቴር ኤልያስ