አዲስ አበባ፡- የአብዮታዊ ዴሞክራሲ በተፈጥሮው ፀረ ዴሞክራሲ መሆኑ በ‹‹አዲስ ወግ አንድ ጉዳይ››የውይይት መድረክ ላይ ተገለፀ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የተፃፈው የ‹‹መደመር›› መፅሀፍን ይዘቶች አስመልክቶ ትናንት በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት‹‹አዲስ ወግ አንድ ጉዳይ››የውይይት መድረክ በተካሄደበት ወቅት፤የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ስርአት በተፈጥሮው ፀረ ዴሞክራሲያዊ መሆኑ ተጠቅሷል።
መደመርና ፖለቲካዊ እሳቤዎችን በተመለከተ ዳሰሳቸውን ያቀረቡት በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የወቅታዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፍስሀ ይታገሱ፣አብዮታዊ ዴሞክራሲ ከፊውዳሊዝም ወደ ሶሻሊዝም ስርአት መሸጋገሪያ ተደርጎ የተቀረፀ መሆኑን አስታውሰው፤ኢህአዴግ በተለይም ህወሃት በ1983 የሶቪየት ካምፕ መፍረስን ተከትሎ ስርአቱ ብዙ ርቀት እንደማያስኬደው ማወቁን ጠቅሰዋል፤በመሆኑም የተወሰነ ማስተካከያ በማድረግ የመርህና እሳቤ ለውጥ ሳይነካው ወደ ካፒታሊዝም ስርአት እንደቀየረው ተናግረዋል።
‹‹ተቃርኖዎች በስፋት የሚስተዋሉበት አብዮታዊ ዴሞክራሲ በተፈጥሮው ፀረ ዴሞክራሲያዊ ነው።›› ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ስርአቱ ለህብረተሰቡ ትምክህተኛ፣ጠባብ፣አዳሪ፣ኪራይ ሰብሳቢና ሌሎችንም ስሞች እየሰጠ በጎራ የሚከፋፍል መሆኑን ጠቁመዋል።
ለኢኮኖሚ ቅቡልነት ብቻ ትኩረት በመስጠት ዴሞክራሲን አፋኝ ነው የተባለው አብዮታዊ ዴሞክራሲ መንግስትና ፓርቲን በመቀላቀል መዋቅራዊ ችግር ሲፈጥር መቆየቱንም አቶ ፍስሀ በዳሰሳቸው አንስተዋል።
አብዮታዊ ዴሞክራሲ ‹‹የብሄር ማንነትና ሀገራዊ ማንነትን አጣጥሞ የመሄድ ችግር ያለበት ስርአት እና‹‹ብዙ ህዝብን አግላይም ነው›› ተብሏል፤ለዚህም ስርአቱ መሰረቴ አርሶአደር ነው በማለት የአርብቶ አደሩን አካባቢ የዘነጋ ስለመሆኑም ተጠቅሷል።
አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሽግግር ፕሮግራም ቢሆንም፤ቋሚ ስርአት ተደርጎ መተግበሩ አሁን በሀገሪቱ ለሚስተዋሉ ችግሮች መነሻ ምክንያት እንደሆነም አቶ ፍስሀ ተናግረዋል።
‹‹መደመር በዚህ ስርአት የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት ልማታዊ ዴሞክራሲን ተግባራዊ የማድረግ እሳቤ ነው።›› ያሉት አቶ ፍስሀ፤የግለሰብና የቡድን መብትን ብሎም የብሄርና ሀገራዊ ማንነትን አጣጥሞ እንደሚያስኬድ በዳሰሳቸው ጠቁመዋል።
‹‹ጨፍላቂና አሀዳዊነትን የሚመልስ ተደርጎ መቆጠሩ ትልቅ ስህተት ነው።›› ሲሉም ገልፀዋል።የሃሳብ ልዕልና የሚታይበት ዴሞክራሲያዊ አስተዳደርን የሚያሰፍነው መደመር በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ስርአት ሲደርሱ የነበሩ ቀጥተኛና መዋቅራዊ ጭቆናዎችን እንደሚያስወግድም ተናግረዋል።
በአንዳንድ የኢህአዴግ ሰነዶች ውስጥ አብዮታዊ ዴሞክራሲና ልማታዊ ዴሞክራሲ ተመሳስለውና አንደኛው በሌላኛው ቦታ ጥቅም ላይ ሲውሉ እንደነበር ጠቅሰው፤ ‹‹ይህ ፍፁም ስህተት ነው።›› ያሉ ሲሆን፤‹‹ልማታዊ ዴሞክራሲ ብልፅግና፣አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግን ፀረ ዴሞክራሲያዊ ነው።››ብለዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ከፍተኛ የፖሊሲ አማካሪው አቶ ማሞ ምህረት በውይይቱ የመፅሀፉ የመጨረሻ ኢኮኖሚያዊ ግብ ብልፅግናን ማረጋገጥ መሆኑን ጠቅሰው፤በውድድር ላይ የተመሰረተ ነጻ ገበያን በማበረታታት መንግስት በኢኮኖሚው ላይ የሚኖረውን ሚና በማመላከት የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ የሚጎለብትበትን ስልት አመላካች እንደሆነ በዳሰሳቸው ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ የምትገኝበት ቀጣና ከምጊዜውም በላይ ትኩረት እያገኘ ስለመጣ እድሉንና ብሄራዊ ጥቅምን ሊያሳጡ የሚችሉ ሁኔታዎች እንደሚኖሩ በማሰብ የመደመር እሳቤ የውጭ ግንኙነቱን በተሳካ ሁኔታ ማስኬድ የሚቻልባቸውን አቅጣጫዎች እንደሚያመላክት ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የውጭ ጉዳይ ተንታኙ አቶ መሀመድ ራፊን በዳሰሳቸው ገልፀዋል።
ዋልታ ረገጥነት፣ አቅላይነት፣ትናንት ላይ ብቻ ማተኮር፣ሁሉንም ሃሳብ ላለመቀበል መጣር፣አድር ባይነትና መሰል ችግሮች የመደመር ሳንካዎች በመጥቀስ፣ህሊና ቢስነትና ልግመኝነት የመደመር ቀይ መስመሮች መሆናቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ ዲግሪ ተማሪው አቶ ዮናስ ዘውዴ ጠቁመዋል።
ውይይቱ በሌሎችም መድረኮች እንደሚቀጥል የተገለፀ ሲሆን፤የመድረኩ ተሳታፊዎች አስተያየቶችና ጥያቄዎችን በማንሳት ተሳትፈዋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 11/2012
ድልነሳ ምንውየለት