እ.ኤ.አ በ2011 ሰኔ ወር ከሱዳን ተነጥላ ሉዓላዊ አገር የሆነችው ደቡብ ሱዳን ህዝብ ከነፃነት በኋላ ሠላሙንና ነፃነቱን አጣጥሞ ሳይጨርስ ሁለት ዓመት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ወደ ርዕስ በርዕስ ጦርነት መግባት ግድ ሆኖባታል።
በነዳጅ ዘይትና በተፈጥሮ ሀብት የበለፀገች 54ተ ኛዋ አፍሪካዊት አገር እ.ኤ.አ ከ2013 ወዲህ በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር እና በተቀናቃኛቸው የቀድሞው ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንትና የአማፅያኑ መሪ ሪክ ማቸር እንደጠላት መሻኮት፤ መወነጃጀል፤ መታኮስ፤ የስደት፤ የሰቆቃ ዓመታትን አሳልፋለች።
ሁለቱ ተፋላሚ ሃይሎች በሥልጣን ይገባኛል ደጋፊዎቻቸውን አሰልፈው በገጠሙት በጭፍን ጎሰኝነት መርዝ በተነደፈው የርዕስ በርዕስ ጦርነት፣ በመቶሺዎች የሚቆጠሩ ሞተዋል፤ ሚሊዮኖች ተሰደዋል። ከነፃነት በኋላ ከጦርነት በስተቀር ሠላምና መረጋጋት ለማያውቀው ደሀ ሕዝብ ሠላም ለማምጣት የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ)ና ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች አገራትና ተቋማት ብዙ ደክመዋል።
በተቀናቃኞቹ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ተወግዶ ደቡብ ሱዳናውያንን ከሞትና ከስደት ለመታደግ በተካሄዱ ጥረቶች በተለያዩ ጊዜያት በተደጋጋሚ የተኩስ አቁም ስምምነት ቢደረስም፣ ፈራሚዎች ከአንጀት ሳይሆን ከአንገት ፈልገው፤ ተግባብተው ሳይሆን ተጽዕኖን ፈርተው በመፈራረማቸው የሚፈለገውን ሠላም ለማምጣት ሲደረግ የቆየውን ጥረት አስቸጋሪ አድርጎት ቆይቷል።
ፊርማው ገና ሳይደርቅ ሁለቱም ወገኖች መካሰሳቸውም የአገሪቱ የሠላም ጉዞ ሠላም የማስፈንንም ሆነ የአንድነት መንግሥት የመመስረቱን ዕቅድ በተደጋጋሚ አደናቅፎታል። ይሁንና እ.ኤ.አ በ2018 መስከረም በሁለቱ ተቀናቃኝ ወገኖች መካከል የተደረሰው የአንድነት መንግሥት የመመስረት ውሳኔ፣ በተያዘለት ቀነ ገደብ ባይጠናቀቅም፣ ከዚህ ቀደም ከተደረሱት ግን ካልተፈፀሙት የተኩስ አቁም ስምምነቶች የተሻለ በመሆኑ የብዙዎችን ሕይወት ከሞት ታድጓል።
ይህን ስኬት ለማስቀጠልና ነገሩን በመንፈሳዊ ጎኑ ተመልክተው በጋራ በሀገራቸው የማይናወጥ ሰላም ይመጣ ዘንድ በፀሎት ለመትጋት በፈረንጆቹ ሚያዝያ ወር በቫቲካን ተገኝተው መንፈሳዊ ቡራኬ ሳይቀር የወሰዱት ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር እና ሪክ ማቻር፣ ባሳለፍነው ዓመት ጳጉሜን መጨረሻ በጁባ ባደረጉት የፊት ለፊት ውይይት ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመስረት በመርህ ደረጃ ከመስማማት ደርሰዋል።
በውይይታቸውም በሕገ መንግሥቱ ማሻሻያ፣ በፀጥታ ሕጎች እና በአገሪቱ ሊኖር በሚገባው ክልላዊ አስተዳደር ዙሪያ መምከራቸውንና አገሪቱ ከሦስት ዓመታት የሽግግር ጊዜ በኋላም ምርጫ የማካሄድ ዕቅድ እንዳላትም የደቡብ ሱዳን ማስታወቂያ ሚኒስትር ማይክል ማኩዬ ሉዬት ገልፀዋል። ይህም ለደቡብ ሱዳናውያን ታላቅ የሠላም ተስፋ ይዞ የሚመጣ መስሏል።
የስምምነቱ ተፈፃሚነት መቃረቡን ተከትሎም የተለያዩ ተቋማትና አገራት ለደቡብ ሱዳን አፋጣኝ ሠላም ይህ የመጨረሻው ጊዜ ነው ሲሉ ተደምጠዋል። ከእነዚህ አንዱ የሆኑት በደቡብ ሱዳን የአሜሪካ አምባሳደር ቶማስ ሁሼክ ሁለቱም ተቀናቃኝ ወገኖች የሚችሉትን ጥረት አድርገውና መስዋዕትነት ከፍለው በህዳር 2012 ዓ.ም. የአንድነት መንግሥቱን እንዲመሰርቱ ጥሪ አቅርበዋል።
እንደ አሜሪካ ድምፁ ዋኬ ሲሞን ውዱ ዘገባም አምባሳደሩ ባሳለፍነው ዓመት በሁለቱ ተቀናቃኝ ወገኖች መካከል የተደረሰው መንግሥት የመመስረት ውሳኔ እንዲከበር፣ ሠላም እንዲወርድ አስገንዝበዋል፤ የመንግሥት ምስረታውም የይስሙላ ሳይሆን ሁሉንም ያማከለ ሆኖ በተገቢው መንገድ ተፈፃሚ እንዲሆን አሳስበዋል። የሠላም ሂደቱን ለማደናቀፍ የሚሞክር የማናቸውም ወገን አመራር እንዲሁም ግለሰብ ካለ አገራቸው ተጨማሪ ከባድ ማዕቀብ ለመጣል ፈጥና እንደምትንቀሳቀስ አመልክተዋል።
ስምምነቱ ሊፈፀም የሚገባበት ወቅት መቃረቡን ተከትሎም ባሳለፍነው ሳምንት የአገሪቱ መንግሥትና ተቀናቃኝ ሃይሎች የፊት ለፊት የሠላም ውይይት በጁባ አካሂደዋል። መድረኩም የርዕስ በርዕስ ጦርነቱን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስቆም፣ በሁለቱ ሃይሎች መካከል የተጀመረውን ድርድርና ተግባራዊ በመሆን ላይ ያለውን የተኩስ አቁም ስምምነት ማስቀጠልን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን የቱርኩ የአናዶሉ አጀንሲ ዘገባ አስነብቧል።
ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኬር በመድረኩ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግርም የደቡብ ሱዳን ሠላም መናጋት ጦስ ለቀጠናው አገራት የሚተርፍ መሆኑን አስታውቀዋል። ‹አፍሪካውያን የራሳችንን የቤት ውስጥ ችግር በራሳችን ለመፍታት ፍቱን መድሃኒት የምንፈልግበት ጊዜ መምጣቱን በመጠቆም፣ የቀጠናው አገራት መሪዎችም ለአገሪቱ ሠላም እውንነት እጅ ለእጅ ተያይዘው እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።
‹‹ህዝባችን ከበቂ በላይ ተሰቃይቷል፣ አሁን አበክረን ስለ ሠላም መትጋት አለብን›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ከዚህ በተቃርኖ በሠላሙ መደፍረስ ተጠቃሚ ለመሆን ተቃዋሚዎችን የሚደግፉና የሚያስታጥቁም ሳይውል ሳያድር ከተግባቸው እንዲታቀቡም አሳስበዋል።
በዚህ መደረክ ላይ የተገኙት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም ሁለቱም ወገኖች ስምምነት ላይ ደርሰው የበለፀገች ደቡብ ሱዳንን በመገንባት እንዲያተኩሩ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል። የዩጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ በበኩላቸው፣ ሁለቱ ተፋላሚዎች ወደ አንድነት ጎዳና መራመድ እንደሚገባቸው በማስገነዘብ፣ ‹‹አገራችሁን ማዳን የምትፈልጉ ከሆነ፣ ጊዜ ሳታጠፉ ሠላምን ጨብጡ ብለዋቸዋል።
ሞሴቪኒ መሪዎች ልክ እንደ ዶክተር መሆናቸውንና ሥራቸውን በአግባቡ ካላከናወኑና ስህተት ከፈፀሙ ከመፈወስ ይልቅ ታማሚውን ለተጨማሪ ስቃይ እንደሚዳርጉት በመጥቀስ፣ ዘጎቻቸውን ከሰቃይ ለማውጣት መሪዎቹ ሥራቸውን በአግባቡና በሃላፊነት ስሜት እንዲወጡ አሳስበዋል።
የአሶሸትድ ፕሬሱ ቢይሳም ሜድኒክ በአንፃሩ፣ የመንግሥት ምስረታው ጊዜ ገደብ እየተቃረበ መምጣቱን ተከትሎ ሥጋቶች እያያሉ መጥተዋል ይላል። ይህም በአንዳንድ አካባቢዎች በተለይም በተቃዋሚ ሃይሎቹ ካምፕ አካባቢ ይስተዋል እንደነበር በመጥቀስ፣ በአገሪቱ ያሉት የታጣቂዎች ብዛትና የፀጥታ ሥጋት ከሁሉም በላይ አሳሳቢና ሪክ ማቻር ወደ አገር ቤት እንዳይገቡ ሊያሠጋቸው እንደሚችል አስነብቧል። በዝሆኖች ጠብ ቤተባቸውን በሞት የተነጠቁና በስደትና በረሃብ የሚሰቃዩ ደቡብ ሱዳናውያን ግን አገራቸው ዳግም ሠላም እንድትሆን ከአንገት ሳይሆን ከአንጀት እርቅ የሚያወርዱ መሪዎችን አጥብቀው ይናፍቃሉ።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 11/2012
ታምራት ተስፋዬ