አዲስ አበባ፡- የአፍሪካ ሴት መሪዎች ኔትወርክ ምዕራፍ በኢትዮጵያ ተመሰረተ። ኔትወርኩ ሌሎች ሴት መሪዎችን እየተደጋገፉ ለማፍራት እንደሚያስችል ተገለጸ።
የኔትወርኩ ምዕራፍ በኢትዮጵያ መመስረት ትናንት በሸራተን አዲስ ይፋ በሆነበት ወቅት የተገኙት ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ እንደተናገሩት፤ የምዕራፉ መመስረት ለኢትዮጵያ ሴቶች ትልቅ ስኬት ነው።ኔትወርኩን በምሳሌነት መምራት ይገባል።
ፕሬዚዳንቷ በኢትዮጵያ ጠንካራ የሴት መብት የሚያስከብር ድርጅት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ወደ አመራርነት ሲመጡ ድርብ ኃላፊነት እንዳለባቸው አመልክተዋል።የተሰጠንን ኃላፊነት ከመወጣት በተጨማሪ ሌሎችንም ማፍራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
አሁን መልካም አጋጣሚ መፈጠሩን በመጥቅስም፤ሴቶች ዕድሉን በመጠቀም ስኬት ሲያስመዘግቡ ከመፎካከር ይልቅ ቢደጋገፉ መልካም መሆኑን አስታውቀዋል። ኔትወርኩ ሌሎች መሪዎችን ለማፍራት በሚደረገው ጥረት ውስጥ በመደጋገፍ ለመስራት እንደሚያስችል ጠቁመዋል።
የኢፌዴሪ ሴቶች፣ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር ወይዘሮ ያለም ፀጋዬ፤ የኔትወርኩ በኢትዮጵያ መመስረት ተሳስሮ ለመስራት እንደሚያግዝ አስታውቀዋል።የሴት
መሪዎች ተሳትፎ እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰው፤ ይህን ዘላቂ ለማድረግ የኔትወርኩ መመስረት ፋይዳው የጎላ መሆኑን አመልክተዋል።
አፍሪካ ውስጥ ሴቶች ያላቸው የአመራርነት እድል የተገደበ መሆኑን በማመልከት፤ ለወጣት ሴቶች አርአያ የሚሆኑ እስከማጣት በመደረሱ ሁኔታው ባለበት እንዲረግጥ ማድረጉን ተናግረዋል፤ አሁን በኢትዮጵያ የተሻለ ተስፋ መታየት መጀመሩን አመልክተው፤ የዘመኑ አመራሮችም እርሳቸውን ጨምሮ ለትውልድ የሚቀርብ ህያው ታሪክ መፃፍ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ሚኒስትሯ እንደተናገሩት፤አመራሮቹ ሴቶችን ወደ ኃላፊነት ቦታ ለማምጣት የተሰራው ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በመስራት፤ወጣት ሴቶችን በማዘጋጀትና የስኬታማ ሴቶች ታሪክ በመፃፍ ሚናቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል።
በመድረኩ ላይ እንደተጠቆመው፤ የኔትወርኩ መመስረት በሴቶች ዘርፍ በ2030 የዘላቂ ልማት ግቦች የተቀመጠውን እቅድ እንዲሁም የ2063 የአፍሪካ አጀንዳን ለማሳካት ፋይዳ አለው።የአፍሪካ ሴት መሪዎች ኔትወርክ ምዕራፍ ሲመሰረት ኢትዮጵያ 26ኛዋ አገር ናት።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 11/2012
ምህረት ሞገስ