አባ መኮንን አንዳርጌ የወልቂጤ ሀገረ ስብከት መስሪያ ቤት የጥበቃ ሠራተኛ ናቸው። የሚኖሩትም በከተማ በሚገኘው ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ግቢ ውስጥ ነው። ከስምንት ዓመታት በፊት የዓይን ሞራ ጋርዷቸው ሁለቱም ዐይናቸው ማየት ያቆማሉ። በዚህም ምክንያት እንደ ልብ መንቀሳቀስና ሥራቸውንም መሥራት ባለመቻላቸው ሳቢያ ተስፋ በመቁረጥ እቤት መዋል የግድ ሆኖባቸው እንደነበር አባ መኮንን ያስታውሳሉ።
በዚህ ችግር ውስጥ እንዳሉ ነው ታዲያ በወልቂጤ ከተማ ጤና አጠባበቅ ጣቢያ የዐይን ቀዶ ህክምና እንደሚደረግ የሰሙት። ጊዜም ሳያጠፉ ወደ ጤና ጣቢያው ያመራሉ። የዐይን ሞራ ቀዶ ህክምና ተደርጎላቸውም የሁለቱም ዐይኖቻቸው ብርሃን ይመለሳል።
ማየት በመቻላቸውም ‹‹ዳግም ውልደት ተሰምቶኛል፤ የማንበብና የመፃፍ ችግሬም ተቀርፏል››የሚሉት አባ መኮንን፣ በዞኑ የዐይን ህክምና ማዕከል ባይኖር ኖሮ የጨለማ ህይወት መግፋታቸውን ይቀጥሉ እንደነበርም ነው የሚናገሩት።
የወልቂጤ ጤና አጠባበቅ ጣቢያ የዐይን ህክምና ነርስ ወይዘሮ ሂሩት ዲልጋሶ ጤና ጣቢያው ለሚያካሂደው የዐይን ህክምና ኦርቢስ ኢንተርናሽናል በርካታ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱን ይናገራሉ። በጣቢያው ውስጥ ባለው የዐይን ህክምና ማዕከል የሁለተኛ ደረጃ የዐይን ህክምና አገልግሎት በበቂ የሰው ኃይልና የህክምና መሳሪያዎች እንደሚሰጥም ይገልፃሉ።
እንደ ወይዘሮ ሂሩት ገለፃ፤ በዞኑ በኦርቢስ ኢንተርናሽናል ድጋፍ የዐይን ህክምና አገልግሎቱ እየተሰጠ ቢሆንም፣ አገልግሎቱን ወደ ተቀሩት አካባቢዎች በማስፋት ረገድ በመንግሥት በኩል ክፍተቶች ይታያሉ። ህክምናው ምን ያህል ህዝቡን ተጠቃሚ እያደረገ ስለመሆኑ በመንግሥት በኩል በበቂ ሁኔታ አይታወቅም፤ አንዳንዴም ሥራው የኦርቢስ ብቻ ተደርጎም ይቆጠራል።
አሁን የዐይን ህክምና ማዕከሉ የተሟላና በቂ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፤ኦርቢስ ድጋፉን ቢያቋርጥ በዐይን ህክምና ማዕከሉ ቀጣይነት ላይ ትልቅ ስጋት እንዳላቸው ወይዘሮ ሂሩት ያስገነዝባሉ። የዐይን ህመም የአጋር ድርጅቶች ችግር ብቻ አለመሆኑን አመልክተው፣እንደ ሌሎች በሽታዎች ሁሉ ለዐይን ህክምናም መንግሥት ትልቅ ትኩረት መስጠት እንዳለበት ያመለክታሉ።
የጤና ጣቢያው የዐይን ሞራ ቀዶ ሐኪም ዶክተር ደረጄ ኃይሉ እንደሚሉት፤በኦርቢስ ኢንተርናሽናል ድጋፍ በተቋቋመው የዐይን ህክምና ማዕከል የዐይን ሞራ ቀዶ ህክምና፣ የትራኮማና ሌሎችም መሰረታዊ የዐይን ህክምና አገልግሎቶች ይሰጣሉ። በመነፅር ሊስተካከሉ የሚችሉ የእይታ ችግሮችንም ለመፍታት የመነፅር ማምረቻ በማዕከሉ ውስጥ ተቋቁሞ አገልግሎት እየሰጠ ነው ፤መሰረታዊ የዐይን ህክምና አገልግሎቱን ለመስጠትም ልዩ ልዩ የጤና ባለሙያዎች ተመድበው እየሠሩ ናቸው።
የጉራጌ ማህበረሰብን ጨምሮ በዞኑ አቅራቢያ የሚገኙ የኦሮሚያ ክልልና የየም ልዩ ወረዳዎች ህዝቦች በማዕከሉ እንደሚገለገሉም ዶክተር ደረጄ ጠቅሰው፤በክረምት ወቅት በቀን በአማካይ እስከ ሠላሳ በበጋ ወቅት ደግሞ እስከ ሰባ የሚጠጉ ሰዎች በማዕከሉ እንደሚገለገሉም ይናገራሉ።
ዶክተር ደረጄ የወይዘሮ ሂሩትን ሃሳብ በማጠናከር ማዕከሉ በተቻለው አቅም መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ አማካኝነት አገልግሎቱ እየተሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፤ለህክምናው ከመንግሥት በኩል እየተሰጠው ያለው ትኩረት አነስተኛ መሆኑን ያመለክታሉ።
በዚህ የተነሳም አገልግሎቱን ለተጠቃሚው እንደ ልብ ተደራሽ ማድረግ እንዳልተቻለ ተናግረው፤በዚህም ምክንያት ህብረተሰቡ አገልግሎቱን ፍለጋ ረጃጅም ርቀቶችን ለመጓዝ ተገዷል ይላሉ። በመሆኑም ህክምናው በመንግሥት በኩል ትኩረት እንዲያገኝ በተለይ የሚዲያ አካላት አጠንክረው ሊሠሩ እንደሚገባም ያመለክታሉ።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 11/2012
አስናቀ ፀጋዬ