የአዲስአበባ፦ የኳታሩ አልጀዚራ ሚዲያ ኔትወርክ የኢትዮጵያ መገኛና ብዙሃንን አቅም ለማጎልበት ለብሮድካስት ጋዜጠኞች ስልጠና መስጠት ጀመረ። ስልጠናው የጋዜጠኞችን እውቀትና ስነ ምግባር ለማጎልበትና የመገናኛ ብዙሃኑን ተወዳዳሪነት ለማጎልበት ከፍተኛ አቅም እንደሚፈጥር ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በኳታሩ አልጀዚራ ሚዲያ ኔትወርክ የስልጠና ኢንስቲትዩት ጋር በትብብር የተዘጋጀው ለብሮድካስት ጋዜጠኞች የተዘጋጀ ስልጠና ትናንት በሂልተን ሆቴል በተጀመረበት ወቅት እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘንድ ከሚዛናዊነት ይልቅ የወገንተኝነት ችግር ይስተዋላል።አንዳንድ ስህተቶችም በእውቀትና ክህሎት ማነስ ሳይሆን ሆን ተብለው ይፈፀማሉ።
‹‹ሙያዊ ስነምግባርን የተላበሰ ጋዜጠኝነት ባህልን ለማዳበር ከታሰበ መሰል የተሳሳተ አሰራር ቀጣይ መሆን አይኖርበትም››ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ለዚህ ደግሞ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለማስተማር፣እንዲታረሙ ግብረ መልሶችን ለመስጠት ቅድሚያ ቢሰጥም ከዚህ አለፍ ሲል በህጉ የተቀመጡ አስተዳደራዊ እርምጃዎችን ለመውሰድም እንደማያመነታም አስገንዝበዋል።
ህዝቡ ትክክለኛና ሚዛናዊ ዘገባ ተደራሽ እንዲሆን ለማድረግ የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ድክመቶችን ለማረም የተለያዩ ስልጠናዎች እየተዘጋጁ መሆናቸውን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከአልጀዚራ ሚዲያ ኔትወርክ ጋር በመተባበር የተዘጋጀው ስልጠናም፣የጋዜጠኞችን እውቀትና ስነ ምግባር ለማጎልበትና የመገኛኛ ብዙሃኑን ተወዳዳሪነት ለማጎልበት ከፍተኛ አቅም የሚፈጥር መሆኑን አስረድተዋል።
አልጀዚራ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ለጋዜጠኞች የተለያዩ ስልጠናዎች መስጠቱን ጠቁመው፤በአሁኑ ስልጠናም ከተለያዩ ተቋማት የተወከሉ 20 ጋዜጠኞች መታደማቸውን ገልፀዋል።
የአልጀዚራ ሚዲያ ኔትወርክ የመገኛ ብዙሃን ልማት ኃላፊ ሞናታሰር ማራይ በበኩላቸው፤አልጀዚራ ለኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ኩነቶች ሽፋን በመስጠት በተለይም የአገሪቱን መልካም ገጽታ ለአለም በማስተዋወቅ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።
ተቋሙ በዘርፉ ባካበተው የረጅም ዓመታት ልምድ ሌሎች ጠንካራ፣ተወዳዳሪና ነፃ የመገናኛ ብዙኃን ለመገንባት የተለያዩ ስልጠናዎችን እንደሚሰጥ ጠቁመው፤ ይህ ስልጠናም የኢትዮጵያን መገናኛ ብዙሃንን አቅም ለማጎልበት ድክመቶችን ለማረም ከፍተኛ እገዛ እንደሚኖረው አስገንዝበዋል።
የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሎልዋህ ረሺድም፣መሰል የስልጠና አጋርነት የኢትዮጵያን መገናኛ ብዙሃን አቅም ከማጎልበት ባሻገር በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ጠንካራ ሁለንተናዊ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ከፍተኛ እገዛ እንዳለው አስገንዝበዋል።
እ.አ.አ በ1996 የተቋቋመው አልጀዚራ ሚዲያ ኔትወርክ የስርጭት ማዕከሉን በኳታር መዲና ዶሃ ያደረገና በዘገባዎቹም አለም አቀፍ ተጽዕኖ መፍጠር የቻለ መገናኛ ብዙኃን ነው ።ስልጠናው ለአምስት ቀን እንደሚቆይም ታውቋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 11/2012
ታምራት ተስፋዬ