– l የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዲፒ) ማዕከላዊ ኮሚቴ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ እና አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ስብሰባውን አጠናቋል
የኦዲፒ ማእከላዊ ኮሚቴ ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ ከተማ ያደረገውን ስብሰባ ማጠናቀቁን ተከትሎ በዛሬው እለት መግለጫ አውጥቷል።
በመግለጫውም የኦዲፒ ማእከላዊ ኮሚቴ በስብሰባው አሁን የተደረሰበት የትግል ምእራፍ ጥንካሬዎችን እና ድክመቶችን እንዲሁም የውስጠ ፓርቲ ጉዳዮችን በጥልቀት በመገምገም ውስጣዊ ችግሮችን ለመቅረፍ እና ቀጣይ የትግል ምእራፍን ለማሳካት የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን ማስቀመጡን አስታውቋል።
ፓርቲው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የኦዲፒ ሊቀመንበር ዶክተር አብይ አህመድ የሰላም የኖቤል ሽልማት ማሸነፋቸውን ተከትሎ የኦሮሞ ህዝብ እንዲሁም መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ያሳዩትን ደስታ እና ድጋፍ በልዩ አድናቆት እንደሚመለከት አስታውቋል።
ይህ ዓለም አቀፋዊ እውቅና የህዝቡ ትግል እና የፓርቲው አመራር የስራ ውጤት ነው ብሎ እንደሚያምን በመግለጽ፥ ለድል ምእራፎች በዚህ መልኩ የሚገለጽ ደስታን የፓርቲው ትግል አቅም ለማድረግ እንደሚሰራም ነው ያመለከተው።
ኦዲፒ ትናንት እንደ ፓርቲ እያሸነፈ እዚህ ሊደርስ የቻለው የኦሮሞን ህዝብ በመያዝ እና ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በጋራ በመሆን ነው፤ አሁንም የኦሮሞን ህዝብ እና መላውን የሀገሪቱን ህዝቦች በመያዝ በድል እንደምንሸጋገር ጥርጥር የለንም ብሏል።
የፓርቲው ማእከላዊ ኮሚቴ ባካሄደው ስብሰባም ከላይ እስከ ታች ባለው አመራር ዘንድ የሚስተዋለውን የተግባር አንድነት እና አመለካከት ችግር ከስር በመቅረፍ ለህዝቡ ጥያቄ በተሟላ መንገድ መልስ እየሰጡ መሄድ አሁን የተደረሰበት የትግል ምእራፍ የሚፈልገው ጉዳይ መሆኑን ከስምምነት መደረሱን አስታውቋል።
ከፓርቲ እና ከመንግስት የሚሰጡ ተልእኮዎችን በወገንተኝነት እና በተጠያቂነት መንፈስ ወስዶ መንቀሳቀስ ላይ ክፍተት እንዳለ የገመገመው ማእከላዊ ኮሚቴው፥ ስለዚህም ከከፍተኛ አመራር ጀምሮ እስከ ታች ድረስ በአንድነት ስሜት በመንቀሳቀስ የህዝቡን ጥያቄ እና የትግል ፍላጎት ማሳካት ወሳኝ እንደሆነ አቅጣጫ አስቀምጧል።
የውስጠ ፓርቲ አመለካከት እና የተግባር አንድነትን በማጠናከርም እስካሁን መልስ ያገኙ የህዝቡን ጥያቄዎች እንደ መነሻ በመውሰድ መልስ ያላገኙትን በመለየት በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥያቄዎቹ አንድ በአንድ እየተቆጠሩ መልስ እንዲሰጣቸውም ፓርቲው አቅጣጫ ማስቀመጡን ነው ያመለከተው።
የፌዴራሊዝም ስርዓት አማራጭ የሌለው የፖለቲካ እና የአስተዳደር ስርዓት ነው ያለው ማእከላዊ ኮሚቴው፥ ስለዚህም ኦዲፒ እውነተኛ የፌደራል ስርዓትን ስራ ላይ በማዋል የሀገሪቱን ብሄር ብሄረሰቦች እኩልነት ማረጋገጥ ላይ የማያወላውል አቋም እንዳለው አረጋግጧል።
ይሁን እንጂ ባለፉት ጊዜያት የፌዴራል ስርዓትን የሚያፋልሱ ተግባራት ሲከናወኑ ነበር ያለው ማእከላዊ ኮሚቴው፥ በግምገማው ላይም ከዚህ ቀደም በተከናወኑ ጥናቶች የኢትዮጵያ ፌደራሊዝም ሁሉንም ህዝብ ፍትሃዊ በሆነ መልኩ እንዳላሳተፈ እና በውስጡም እውነተኛ ዴሞክራሲ ያልተረጋገጠበት እንደሆነ ማመላከቱን ገልጿል።
ኦዲፒ እነዚህ ክፍተቶች ተስተካክለው እውነተኛ ህብረ ብሄራዊ ፌደራሊዝም ተግባራዊ እንዲሆን እና ኢትዮጵያን ሁሉም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች በእኩልነት፣ በነፃነት እና በወንድማማችነት የሚኖሩባት ሀገር ለማድረግ የጀመረውን ትግል አጠናክሮ እንደሚቀጠል አረጋግጧል።
በሌላ በኩል ትናንት እውነተኛ የፌደራሊዝም ስርዓት ተግባራዊ እንዳይሆን ይዘውት በነበረው ስልጣን የፌደራሊዝም ስርዓትን ሲያፋልሱ የነበሩ ህዝቡን የማይወክሉ ጥቂት ቡድኖች ዛሬ ላይ ራሳቸውን ለህገ መንግስቱ የቆሙ እና የፌደራሊዝም ዋስ በማስመሰል የሚያቀርቡ አካላት የሚያሰራጩት መሰረተ ቢስ መረጃ ተቀባይነት የሌለው መሆኑንም ማእከላዊ ኮሚቴ አስታውቋል።
በኢህአዴግ ውስጥ እየተካሄደ ያለው ሪፎርም የፓርቲው የትግል ጉዞ እንዲሁም የህዝቡን ፍላጎት እና ጥያቄ መሰረት ያደረገ ነው ያለው ማእከላዊ ኮሚቴው፥ በተለይም በሀዋሳ በተካሄደው 11ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ ላይ በምሁራን ተጠንቶ ቀርቦ ውሳኔ እንዲያገኝ በአቅጣጫ እና በውሳኔ የተደገፈ መሆኑንም አንስቷል።
የህዝቡ ጥያቄ እና የፓርቲው የውስጠ ውሳኔ የሆነው መደመር የፓርቲው አፈጣጠር፣ ዴሞክራሲነት እና አቃፊነቱ ላይ ራሱን እንዲመለከት እድል የፈጠረ መሆኑንም አስታውቋል።
የተካሄደው ጥናትም ኢህአዴግ ዴሞክራሲያዊ እና አቃፊ እንዳልሆነ፣ የሀገሪቱን ህዝቦች በከፊል የገፋ እና በተወሰኑ ሀይሎች ብቻ ውሳኔ የሚሰጥ መሆኑን ለይቷል ያለው ማእከላዊ ኮሚቴው፥ የኢህአዴግ አወቃቀር እና ሲመራበት የነበረው አብዮታዊ ዴሞክራሲ የህዝቡን ውሳኔ ሰጪነት የሚገድብ በመሆኑ አሁን የተደረሰበትን የትግል ምእራፍ አይመጥንም ብሏል።
በተለያዩ ችግሮች የተከበበው የኢህአዴግ አደረጃጀት የኦሮሞ ህዝብና የኢትዮጵያ ህዝቦች ጥያቄን ለመመለስ የማይመች መሆኑ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ውይይት ካደረገበት በኋላ ስምምነት ላይ መድረሱንም አስታውቋል።
በዚሁ መሰረት የኢህአዴግን አደረጃጀትን በማዘመን በዘመናዊ አሰራር የሚመራ ፓርቲ ለመመስረት የአብዮታዊ ዴሞክራሲን በመደመር ሀሳብ ለመተካት ውይይት እየተደረገበት መሆኑን ያስታወቀው ማእከላዊ ኮሚቴው፥ ኦዲፒም የመደመር ሀሳብ ከዚህ ቀደም የነበሩት ስኬቶችን ይበልጥ ማጠናከርና የሚታዩ ችግሮችን መፍታት የአዲሱን ትውልድ መብትና ጥቅም ያስከብራል ብሎ እንደሚያምን ገልጿል።
ይህንን መሰረት በማድረግም የኢህአዴግ ሪፎርም እውነተኛ የፌደራል ስርዓት ያላት ህብረ ብሄራዊ ሀገር በመገንባት የህዝቡን ጥቅም እና ፍላጎት ለማስጠበቅ ተመራጭ ዘዴ በመሆኑ ለስኬታማነቱ መስራት ወሳኝ እንደሆነም አስታውቋል።
ኦዲፒ ሲያሳልፋቸው የነበሩ ውሳኔዎች እና አቅጣጫዎች ህዝቡን ድል እያጎናፀፉ አሁን ላለበት የትግል ምእራፍ አድርሰውታል ያለው ማእከላዊ ኮሚቴው፥ አሁን የተቀመጡ አቅጣጫዎችም ህዝቡ መስዋእትነት ከፍሎ ያገኛቸውን ድሎች ለማቆየት እና ተጨማሪ ድሎችን ለመጎናፀፍ የሚያስችሉት በመሆኑ ህብረተሰቡ ለተፈፃሚነቱ ትብብር እንዲያደርግም ጥሪ አቅርቧል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 8/2012