– 100ሺ መለስተኛ ሙያ ያላቸው ዜጎችም የሥራ ዕድሉ ተጠቃሚ ይሆናሉ
አዲስ አበባ፡- በዘንድሮ ዓመት በመስኖ ሥራ ለሚሰማሩ አሥራ ሁለት ሺህ የተማሩ ወጣቶች የሥራ ዕድል እንደሚፈጠር የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ብዙነህ ቶልቻ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ ለወጣቶቹ የሥራ ዕድሉ የሚፈጠረው በተለያዩ ክልሎች ሊካሄድ በታቀደው የመስኖ ልማት ዘርፍ ነው፡፡
መንግሥት የተማሩ ወጣቶችን በመስኖ ልማት ዘርፍ ለማሰማራት በያዘው ዕቅድ መሰረት በዘንድሮ ዓመት ወደ ሥራው የሚገቡ አሥራ ሁለት ሺህ ወጣቶች ተመልምለው በቂ የሚባል ሙያዊ ስልጠና ወስደዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ በመጀመሪያ ዙር ለመስኖ ሥራው በእቅድ የተያዘው ሃምሳ ሺህ ሄክታር መሬት ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜም ሰላሳ አራት ሺህ ሄክታር ያህል መሬት በመገኘቱ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኗል፡፡
በኦሮሚያ፣አፋር ደቡብና ሶማሌ ክልሎች ለመስኖ ሥራው የሚሆን መሬት ተለይቶ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ በአማራ፣ትግራይና ጋምቤላ፣ ክልሎችም ተመሳሳይ ሥራዎች ተጀምረዋል፡፡
በመስኖ ሥራው የሚሰማሩት ወጣቶች በግብርናና መሰል ሙያዎች ዕውቀቱ ያላቸው እንደሆኑ የገለጹት አቶ ብዙነህ ወጣቶቹ በአንድ ሺህ ኢንተርፕራይዞች ሲደራጁ ተያያዥ ሙያ ያላቸው የሂሳብ ሠራተኞች፣ የአስተዳደር ባለሙያዎች፣ኢንጂነሮች፣ በአበባ ልማት ዘርፍ የተሰማሩ ወጣቶችና ሌሎችም የእድሉ ተጠቃሚዎች ይሆናሉ ብለዋል፡፡
አቶ ብዙነህ እንደሚሉት በሃምሳ ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ተሳታፊ የሚሆኑት አስራ ሁለት ሺ ወጣቶች አንድ መቶ ሺህ መለስተኛ ሙያ ያላቸውንና በጉልበት ሥራ የሚሰማሩ ሠራተኞችን በማሳተፍ ተጨማሪ የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅም ይኖራቸዋል፡፡ በተያዘው ዕቅድ መሰረት ሃምሳ ሺህ ሄክታር መሬቱ በአግባቡ ሲለማም አንድ መቶ ሃያ ሺህ የሚሆኑ ወጣቶች የሥራ እድል ያገኛሉ፡፡
ባለፈው ዓመት በአፋር ፣ሶማሌና አሮሚያ ክልሎች ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ስልሳ ሶስት ወጣቶች ተመልምለው ስልጠና የወሰዱ ሲሆን በተመሳሳይም በዘንድሮ የበጀት ዓመት ዘጠኝ ሺህ አንድ መቶ ሰማንያ ስምንት የሚሆኑ ወጣቶች በተመረጡ ክልሎች የሚመለመሉ መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
ወጣቶቹን ወደ መስኖ ሥራው ከማስገባት አስቀድሞ በአካባቢያቸው በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በቂ የሆነ ስልጠና እንደሚሰጥ የተናገሩት አቶ ብዙነህ በተያዘው ዓመትም 2ነጥብ 83 ቢሊዮን ብር በጀት ተመድቦ በአግባቡ የማደራጀት ተግባር ተጀምሯል ብለዋል፡፡
ዳይሬክተሩ አያይዘውም በአሁኑ ጊዜ በአፋርና ኦሮሚያ ክልሎች በሚገኙና ተንዳሆና ጊዳቦ በተባሉ ግድቦች የሚለሙ መሬቶች በመኖራቸው በአካባቢው የሚገኙ የተማሩ ወጣቶች በኢንተርፕራይዞች ተደራጅተው እንዲሰማሩባቸው ለማድረግ ዝግጅቱ መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡
ወጣቶችን በመስኖ ልማቱ ለማሳተፍ አመቺነት ባላቸው ሰባት ክልሎች እንደሚተገበር የገለጹት አቶ ብዙነህ ከስልጠናውና ከማደራጀቱ በተጨማሪም ለሥራ በሚሰማሩበት አካባቢ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያገኙ ከባንኮች ጋር የብድር አገልግሎት እንዲኖር ይደረጋል ብለዋል፡፡
በ2012 የበጀት ዓመት በቀጥታ ወደሥራው የሚገቡት ተለይተው በምልመላ ዝግጅት ላይ የሚገኙ ስለመኖራቸው የጠቀሱት አቶ ብዙነህ መሬትንና ወጣቶቹን ለይቶ ለማሰልጠንና ለማደራጀት ሰፊ ዝግጅትና ትዕግስት የሚጠይቅ በመሆኑ ከሚመለከታቸው አካላትና ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በመቀናጀት በሀገራችን አዲስና የመጀመሪያ የሆነውን ፕሮጀክት የማሳካት ጥረቱ መጠናከሩን ገልጸዋል ፡፡
ቆላማ አካባቢዎችን በመስኖ ሥራ ለማልማት በተደረገው ሙከራ ሶስት ሺህ አምስት መቶ ሄክታር ላይ የሚገኝ የስንዴ ሰብልን የማልማት ጥረት ተደርጎ ውጤት የተገኘ በመሆኑ ለወጣቶቹ ሥራ እንደመነሻ ሊሆን እንደሚችል ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
ከሸንኮራ ፍራፍሬዎችና ከሌሎች ምርቶች ጋር ተያይዞ በአካባቢው በመስኖ መልማት የሚችሉትን በመለየት ለወጣቶቹ ከፍተኛ የገበያ ትስስር የመፍጠር አቅምን ማዳበር እንደሚቻልም ተናግረዋል፡፡
የመስኖ ሥራው ትግበራ ከማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ይዘቱ አኳያ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው የጠቀሱት አቶ ብዙነህ ከዚህ በዘለለም በሀገሪቱ ሀብት ተምረውና ያለምንም ሥራ ተቀምጠው የቆዩ ወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ ከማስቻሉም በተጨማሪ የውጭ ምንዛሪን ለማስቀረት የሚኖረው ድርሻ የላቀ መሆኑን ዳይሬክተሩ አክለው ገልጸዋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት ለመስኖ ሥራ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ተይዞ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 8/2012
መልካምስራ አፈወርቅ